የአዕምሮ ህሙማን ከየትኛውም የህብርተሰብ ክፍሎች ይበልጥ ለፆታዊ ጥቃት እና ለኤች አይቪ ኤድስ ተጋላጭ መሆናቸውን የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤደኦ ፈጆ 13ኛውን የነጭ ሪቫን ቀንን አስመልክቶ ሕዳር 28 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ በተካሄደው ፕሬስ ኮንፍረንስ አመልክተዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ የአዕምሮ ህሙማን የፆታዊ ጥቃት አካላዊ ስነ – ልቦናዊ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ያደርስባቸዋል። በተለይ በፆታዊ ጥቃትና በኤች አይቪ ኤድስ መከላከል ላይ የሴቶች ተሳትፎ ማነስ የአደንዛዥ እፆች መብዛት ችግሩን እንደሚያባብሰው ጠቁመው፤ የሚዲያ አካላትም ችግሩን ለመቅረፍ የላቀ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሳይካትሪስት የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ላቀው፣በበኩላቸው የጾታዊ ጥቃትን እየተባባሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት በፆታዊ ጥቃት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰዓት ሰባት ሴቶች ይሞታሉ የፆታዊ ጥቃት የሰዎችን አስተሳሰብ፣ ከሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ ስሜትና ፀባይ ይለውጣል፡፡ ይሁን እንጂ የሚገባውን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ፆታዊ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ሌሎች ሰዎች የሚናገሯቸው ነገሮች የበለጠ የሚጎዱ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ሊደረግ የሚያስፈልገው ዕርዳታዎች ውስጥ የመጀመሪያው ማዳመጥ ሲሆን፤ ቅርብ ሆኖ ሃሳባቸውን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡
ከዚሁ በመቀጠል ተጎጂዋን ፍላጎቶቿንና ስጋቷን በመጠየቅ፡፡ ችግሮቹ አካላዊ፣ ስነ ልቦናዊ፣ ማህበራዊ መሆናቸውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም እንደ ተረዳናትና እንዳመንናት ማሳየት፤ ጥፋተኛ እንዳልሆነች ማስረገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ የተጎጂዋን ደህንነትን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ሲባል ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ እንዴት መከላከል እንደሚቻል መወያየትን ያካትታል፡፡ ከዚሁ ጋር የመረጃ፣ አገልግሎት እና ማህበራዊ ድጋፍ የምታገኝበትን መንገድ ማፈላለግ አስፈላጊ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚያውቋቸው ሰዎች ላይ ፆታዊ ጥቃት ሲደርስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ሊጋቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነርሱን ለመርዳት ቀላሉ ዘዴ ተጎጂዎቹ ከዕርዳታ ሰጭው ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጊዜ መስጠት፣ ስለ ፆታዊ ጥቃት መረጃ መስጠትና የስነ ልቦና ባለሞያ ወይም የአዕምሮ ሀኪም ምክር እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
መዘንጋት የሌለበት አንድ ቁልፍ ነገር ሁሌም የተጎጂዋን ፍላጎት ማክበር ነው፡፡ ፆታዊ ጥቃት መንስኤው ሴቶችን እኩል በሆነ መልኩ ክብራቸውንና ሰብዓዊነታቸውን ያለመቀበል ነው፡፡ ፆታዊ ትንኮሳ፣ አካላዊ ጥቃት፣ የቅርብ አጋር ጥቃት፣ አላግባብ የሆነ ቁጥጥር ሁሉም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው፡፡
ፆታዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት ላይ አንተም ተው አንቺም ተይ በማለት በቀላሉ ማለፍ ተገቢ አለመሆኑንና ቀጣይ ሁኔታ በአግባቡ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል፡፡
በባህላዊ ስርዓቶች እና በተሳሳተ አመለካከት የፆታዊ ግንዛቤ መውሰድ ሌላው ሰፊ ችግር መሆኑንም ተናግረዋለ፡፡ በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነትን በተመለከተ በተለይ ሴቶች እንዲሳተፉ በማድረግ እስከታች ድረስ ማውረድ በመንግሥት በኩል ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት የሀኪም መመሪያ የሚለውን ምንጭ በማድረግ አያይዘው እንደተናገሩት የአስታማሚነት ሚና እና የአዕምሮ ህመም በማህበረሰብ አስተሳሰብ ላይ የሚገነባ ሲሆን፤ ይህም ሰዎች ሲታመሙ ከማህበረሰቡ የሚያገኟቸው መብቶችና የሚሰጣቸውን ኃላፊነትን ያመለክታል፡፡
በሀገራችን ሰዎች ሲታመሙ ዕረፍት እንዲያደርጉ፣ የሚፈልጉትን ምግብ እንዲያገኙ እንደ ህመሙ ዓይነት ጋቢ እንዲለብሱ ይደረጋል፡፡ የታመሙ ሰዎች ሥራ ባይሠሩ ማንም ካለመቀየሙ ባለፈ እንደውም ጭራሽ ሊከለከሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ የታማሚነት ሚና ናቸው፡፡
የታማሚነት ሚና ለታመሙ ሰዎች ሁለት መብቶች እና ሁለት ኃላፊነቶች ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው መብት አንድ ሰው በመታመሙ ምክንያት እንደጥፋተኛ አለመታየትና አለመወቀስ ሲሆን፤ ሁለተኛው በመታመሙ ምክንያት ሊወጣው ያልቻላቸው ኃላፊነቶች ላይ ጫና አለማድረግ ነው፡፡ መብቶቹን ተከትሎ ሁለት ኃላፊነቶችም ይመጣሉ፡፡ ግለሰቡ የጤንነቱን ጉዳይ ከሌሎች ጉዳዮች ቅድሚያ እንዲሰጠው እና ጤንነቱ እንዲመለስ ተገቢውን ህክምና እንዲያደርግ ኃላፊነት ይሰጠዋል፡፡
የታማሚነት ሚና ለአዕምሮ ህመምም ተመሳሳይ ነው፡፡ ታማሚዎች የአዕምሮ ጤንነታቸውን ቅድሚያ እንዲሰጡትና ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ የአዕምሮ ህመም የነሱ ጥፋት እንዳይደለ መቀበል እና ወቀሳን መተው በተጨማሪም በህመሙ ምክንያት የሚፈጠረውን ጫና መቀነስ ነው።
ወ/ት ቤቴል አብርሃም በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስነ-ልቦና ህክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ ፆታዊ ጥቃትን አስመልክተው ሲገልጹልን ማንኛውም የፆታ ልዩነት ላይ የተመሰረተ የግለሰቡን ፈቃድ ያላካተተ ጎጂ ድርጊትን ይጨምራል ብለዋል፡፡
ጥቃት ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ወሲባዊ ጥቃት ፣አካላዊ ጥቃት፣ስነ-ልቦናዊ ጥቃት ወይም ስሜታዊ ስድቦች፣ጎጂ ልማዶች፣ የሴት ልጅ ግርዛት ጠለፋ፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ ወ.ዘ.ተ. ይገኙበታል፡፡
በሌላ በኩል ፆታዊ ጥቃት በሥራ ሁኔታ አጋላጭ ምክንያቶች እንዳሉት እነዚህም ግለሰባዊ ወይም አስተዳደግ ከቤተሰብ፣ ከማህበረሰብ የሚማሩት፣ ሱሰኝነት፣ ማህበራዊ ግንኙነት (የአቻ ግፊት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡ ለፆታ ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ ፆታዊ ጥቃቱ እንዲበራከት ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡
ጥቃቱ በሁለቱም ፆታ ሊደርስ ቢችልም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ግን ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡
የጾታዊ ጥቃት ከጤና አንፃር፣ ከማህበራዊ ህይወት ከግል ህይወት እና ከስነ-ልቦናዊ አንፃር ጫናዎች አሉት፡፡
ስነ-ልቦናዊ ጫና ተጎጂዋ ለራሷ የሚኖራት ግምት ዝቅ እንዲል ሊያደርግ ይችላል፤ በሌሎች ላይም እምነት ማጣትም ሊኖር ይችላል፡፡ ከዚህም አልፎ ተጎጂዋ የራሷን ቤተሰብ መመስረት እንዳትችል ሊያደርጋት ይችላል፡፡
አልኮልና አደንዛዥ እፆች ልማድ ውስጥም ልትዘፈቅ ትችላለች ይህም ሁኔታ በሂደት ወደ ድብርት እንዲሁም የአዕምሮ ህመም ችግር ውስጥ እንድትገባ ሊያደርጋት ይችላል ብለዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዮናስ፣ የጾታዊ ጥቃት ሌላው መገለጫ ችግሩ ሲደርስ በሚገባ ሪፖርት አለመደረግ፣ ያለመናገርና የሃሳብ መታፈን በጊዜ ሂደት ወደ ህመም ሊያመራና በህይወቷ፣ በቤተሰቧ ብሎም በሀገር ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፡፡
አያይዘውም በተለያዩ አላስፈላጊና ጎጂ ሱሶች ውስጥ የገቡ ሴቶችን ጠቃሚ በሆኑ ሌሎች ተግባራት ለምሳሌ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ የተለያዩ ተመስጦዎች፣ የአተነፋፈስ ለምምዶችን( ብሪዚንግ ኤክሰርሳይስ) በማድረግ ጫናውን በተወሰነ ማቅለል ይቻላል ብለዋል፡፡
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር መሀመድ ንጉሴ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት እና ኤች አይቪ ኤድስ በተለይ ከሴቶች የአዕምሮ ጤንነትጋር ከፍተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የሴቶች ፆታዊ ጥቃት ጉዳይ በሚነሳበት ወቅት በጥንቃቄ ለተጎጂዋ ሴት ብቻ መነሳት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ከሚደረጉት ዕርዳታዎችም መጀመርያ በሚገባ ማዳመጥ እና ፍላጎት ወይም ሃሳብ መጠየቅ፣ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም እነርሱን አስመልክቶ መደረግ ከማይገባው ነገር መካከል ችግሩን አለበቂ ጥናት ለመፍታት መሞከር፣ የትዳር አጋርን ወይም ባለቤቷን እንድትፈታ መምከር እንደሚገኝበት ገልጸው በዓለም አቀፍ ደረጃ 39 በመቶ ሴቶች የሞት ምክንያት በትዳር አጋር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሌላው መረሳት እና መዘንጋት ያሌለበት ነገር ደግሞ የተጎጂዋን ፍላጎት በሚገባ ማክበር ያስፈልጋል፡፡
በአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አቶ አብዩ የኔዓለም በበኩላቸው፣ በሚድያ ለችግሩ የሚሰጠው ሽፋን አነስተኛነት እንዳለ ሆኖ በህክምና ባለሙያዎች በኩል ችግሩ ከመባባሱ በፊት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ብዙ እንዳልተሠራ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከሚዲያ አካላት ጋር በትብብር መረጃ መስጠትም በሚቻለው አቅም ግንዛቤን ለማዳበር ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011