ክልሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎትን ለማዳረስ እየሠራ ነው

ቢሾፍቱ:- ተገልጋዮች ባሉበት አካባቢ ሆነው በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ የዳኝነት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ሥርዓት በመዘርጋት ወደ ሥራ ለመግባት እየሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ደንበኞች ለክርክር ጉዳዩ በአካል ሳይቀርቡ ባሉበት ስፍራ በሚገኙ ማዕከላት ሆነው በርቀት ክርክር የሚያደርጉበት አሠራር ይዘረጋል፡፡

አሠራሩ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚተገበር የጠቆሙት አቶ አለምአንተ፤ በክልሉ የዳኝነት ሥርዓቱን ጨምሮ አጠቃላይ የፍትሕ ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ በዋናነት ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የአገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ተገልጋዮች ጉዳዩ ወደሚታይበት ማዕከል ሳይቀርቡ ኮፒ /እስካን የተደረጉ መዛግብት ወደማዕከላት በመላክ ፋይል መክፈት የሚችሉበት ዓይነት አሠራር ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች እየተጠናቀቁ ጠቁመው፤ መዛግብትን መከታተል የሚያስችሉ የተለያዩ መተግበሪያዎች ለማጎልበት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ለትግበራ አስፈላጊ መሠረተ ልማትና የእቃ ግዢዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆናቸውን አመልክተው፤ የርቀት ክርክር ትግበራው በተለይም በ14ቱም ዞኖች ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ላይ እንደሚተገበር አስታውቀዋል፤ በሂደትም እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶችን ለመድረስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ሥራው ዕውቀት እና ከፍተኛ ሀብት ይፈልጋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ከክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ፣ ከፌዴራል ደግሞ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከኢንሳ፣ ከአርተፊሽያል ኢንተለጀንስና መሰል ተቋማት የተውጣጡበት የቴክኒክ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የሚመራ ስትሪንግ ኮሚቴ ተደራጅቶ ፍርድ ቤቱ የሚያስፈልገውን ለመለየት ጥናት መሠራቱን የጠቆሙት አለምአንተ፤ ጥናቱን መሠረት በማድረግም ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ አስፈላጊ በጀትና ሥራዎች ከተለዩ በኋላ ዲጂታላይዝድ ወደ ማድረግ ተሸጋግረናል ብለዋል፡፡

በተለያዩ ዓመታት ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ የሚሆን ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚጠይቅ ፕሮጀክት መቀረጹንም አመልክተዋል፡፡ ካለው የሀብት ውስንነት አንጻር ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማሳካት ስለማይቻል ፍርድ ቤቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይቶ እየሠራ ነው፡፡ ለእዚህም ከክልሉ መንግሥት 400 ሚሊዮን ብር የሚሆን በጀት እንደተመደበለት አስታውቀዋል፡፡

በትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይ ከተያዙ አበይት ጉዳዮች መካከል ምቹ የሥራ ቦታ መፍጠር አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አለምአንተ፤ እቅዱ እንደሌሎች ተቋማት ቢሮዎችን የማሳመርና ሳቢ የማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎች በግልጽ ችሎት የመዳኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዲከበር ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ብዙ ቦታ ዳኞች በቢሮ የሚያስችሉበት አሠራር ትክክል አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራርን የሚፈጥር አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ በጠቅላይ ፍርድ ቤትና በከፍተኛ ፍርድ ቤት ደረጃ ቀደም ብለው ተጀምረው የነበሩ የሕንጻዎች ግንባታ መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ የነበረውን ባለ አራት ወለል ሕንጻ እንደገና ታድሶ ችሎቶች ተመቻችተው ወደ ሥራ መገባቱን አመልክተዋል፡፡ ተጨማሪ ባለ ሦስት ወለል ሕንጻ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ተጀምረው የነበሩ ሦስት የሚሆኑ ትላልቅ ሕንጻዎች ከጀነሬተርና ከሊፍት ገጠማ ጋር የተገናኙ ኤሌክቶሮሜካኒካል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ሁሉም ፍርድ ቤቶች ላይ በቂ ሕንጻዎች ኖረው በግልጽ ችሎት የምናስችልበት አሠራር ይፈጠራል ብለዋል፡፡

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You