እስኪ ዛሬ ደግሞ በአንድ ሰፈር ውስጥ ያሉ ትንንሽ ሰፈሮችን ስያሜ እንይ። አንድ በሰፊው የሚታወቅ ሰፈር በውስጡ ሌሎች ሰፈሮችን ይይዛል። እነዚያ ሰፈሮች እንደዋናው ሰፈር ብዙ ሰው ላያውቃቸው ይችላል፤ ዳሩ ግን የአካባቢው ሰው ይጠቀምባቸዋል። የአካባቢው ሰው ብቻም ባይሆን እዚያ ሰፈር የደረሰ ሁሉ ሊሰማ ይችላል።
ቀጨኔ መድኃኒዓለም እንኳን አዲስ አበባ የሚኖር ክልሎች ድረስ የሚታወቅ ስም ነው። ቀጨኔን የመረጥኩ እዚያ ውስጥ ያሉ ሰፈሮችን ለመናገር ስለፈለኩ እንጂ እነ ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መርካቶ፣ ቦሌ… ከአዲስ አበባ ውጭ የሚኖር ሁሉ ያውቃቸዋል።
ደፋ ቀና
ቀጨኔ ውስጥ በሚገኝ ጠጅ ቤት ስም የተሰየመ ሰፈር ነው። ከችሎት ወደ መድሃኃኒዓለም ሲሄዱ ይገኛል። ጠጅ ቤቱ ደፋ ቀና ጠጅ ቤት ይባላል። ደፋ ቀና የተባለበት ምክንያት፤ ከጠጅ ቤቱ ውስጥ የሚወጡ ሰዎች እየወደቁ እየተነሱ ነው የሚሄዱት። ምንም እንኳን በአካባቢው ሌሎች ጠጅ ቤቶች ቢኖሩም ከአንጋፋነቱና ብዙ ሰው ከማስተናገዱ የተነሳ ብዙ ስካር የሚታየው ከዚህኛው ጠጅ ቤት ነው (ምናልባት እስካሁን ሌላ የበለጠው ጠጅ ቤት ይኖር ይሆናል)።
ማርገጃ
ከመድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በቅርብ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ቀጨኔ ከክፍለ አገር የሚመጡ ሰዎች ይበዙበታል። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ አንድ ቦታ ነው የሚሰባሰቡት። ይህ የሚሰበሰቡበት ቦታ ነው ማርገጃ የተባለው። ስያሜውን ካገኘ በኋላ በቀጥታ ሰዎች ለሚሰበሰቡበት ቦታ ብቻ ሳይሆን አካባቢውም ማርገጃ ተባለ። ማርገጃ ማለት የብዙ ሰው መንጋጋት፣ መሰባሰብ፣ በብዛት መጉረፍ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011