ቅርበታቸውን የሚያውቁ ሁሉ ጓደኝነታቸውን ይመሰክራሉ። የሁልጊዜው አብሮነ ታቸው የፈጠረው ዝምድናም እስከቤተሰብ ትውውቅ አድርሷቸው ነበር። ውሎ ሲያድር ግን መቀራረባቸው ቀዝቅዞ መገናኘታቸው ቀናትን ያስቆጥር ያዘ። እንደቀድሞው ተፈላልጎ አብሮ መዋልን ትተው መራራቅን መረጡ። ይህን ያዩ አንዳንዶች የሁለቱን ባልንጀሮች ቅርበት አስታውሰው በመሀላቸው ስለገባው ንፋስ ለማወቅ ጣሩ። ከእነሱ መሀል አንዳንዶችም ጉዳያቸውን በእርቅ ሊፈቱ ሽምግልናን ሲሞክሩ ቆዩ።
ጓደኛሞቹ ከስምንት አመታት በፊት ምስጢረኞች ጭምር ነበሩ። አንዳቸው የሌላቸውን ጉዳይ ቁምነገር ብለው ከያዙም ዳር ሳያደርሱ አይተውትም። ፋንታሁንና ከበደ ጊዜያትን ባስቆጠረ ቅርበታቸው ብዙ የሚባሉ ደስታና መከራዎችን ተካፍለው የጋራ የሚሏቸውን ጉዳዮች ተጋርተዋል።
ከበደ ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። ራሱንና ቤተሰቡን ለመተዳደሪያ በሚገለገልበት ታክሲ በአግባቡ ያኖራል። ውሎና ማርፈጃውን መርካቶ ላይ አድርጎም የንግድ ዕቃዎችን ሲያመላልስ ይውላል። ሁሌም ንጋት ከአስራ አንድ ሰአት ጀምሮ የከበደ አይኖች ፈጥነው ይነቃሉ። በዚህ ሰአት የአሮጌ ታከሲውን ሞተር አሙቆ ራሱን ለጉዞ ያዘጋጃል። ረዳቱን ቀስቅሶም መኪናውን ለጭነት ያመቻቻል።
ይህ ጊዜ ለእርሱና ለደንበኞቹ ወሳኝ የሚባል ሰአት ነው። ስራውን ከሌሎች ተሻምቶ ገበያውን ለመቅደም የሚችለው ማልዶ ሲነሳና ከቦታው ገስግሶ ሲደርስ ነው። በዚህ ልማድም ለአመታት ሳያስተጓጉል ቆይቷል። መልከ ብዙ ባህርይ ባለቤት የመርካቶ ገበያም በስልትና በመላ ዘይዶ አመታትን ሲመላለስ ኖሯል።
ከበደ የስራ ባህርይው ከብዙዎች ያገናኘዋል። በርካቶቹ መልካም ደንበኞቹ ናቸው። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ለነገርና ሽኩቻ፣ ለጠብና ድብድብ ጭምር የማይመለሱ ስለመሆናቸው እሱም ያውቃል። ይህን አሳምሮ የሚረዳው ባለታክሲ ታዲያ ሁሉንም እንዳመጣጣቸውተቀብሎ እንደየባህርያቸው ሲያስተናግድ መዋሉን ተክኖበታል።
ይህ አይነቱ ወሎ ደግሞ ከበደን ብዙ እንዲያስብ እያደረገው ነው። ጥሩ የሚባሉትን በመልካምነት የሚሸኛቸውን ያህል ዘወትር ከጎኑ ሳይርቁ ለስራው እንቅፋትና ፈተና የሚሆኑት ደግሞ ፈጽሞ አይመቹትም። እነሱን አስቀድሞ ስላወቃቸው ግን እንደየማንነታቸው እየመረጠ ይችላቸዋል።
አንዳንዴ ደግሞ ማልዶ ከቤቱ ሲወጣ የደህንነቱ ጉዳይ በእጅጉ ያስፈራዋል። የእሱን መውጫና መግቢያ የለዩ ዘራፊዎች አሳቻ ሰአት መርጠው ጉዳት እንዳያደርሱበት ይሰጋል። ይህ እውነት አንድ ቀን ሊከሰት ቢችል የሚፈጠረውን እያሰበም ሲጨነናቅ ቆይቷል።
ከበደ ከዚህ ቀድሞ በመኖሪያው አካባቢ በርካታ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ያውቃል። የእሱን ባለቤት ጨምሮ ብዙዎች ቦርሳቸውን ተነጥቀው ሞባይልና ገንዘባቸውን ተዘርፈዋል። ‹‹አሻፈረኝ›› ያሉ አንዳንዶች ደግሞ በስለት ተወግተው ህይወታቸውን እሰከማጣት ደርሰዋል።
የእሱ የስራ ባህርይ ደግሞ ከሌሎቹ ውሎ ይለያል። በጨለማ ተነስቶ ጉዞ መጀመሩ ዝርፊያን እንጀራቸው ካደረጉ ጨካኞች እጅ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ገምቷል። እንዲህ ከሆነም ንብረቱን ብቻ ሳይሆን ህይወቱን ጭምር ሊያጣ ይችላል። እሱ ደግሞ ይህ እስኪፈጸም ቆሞ መጠበቅን አይሻም።
አንድ ቀን ግን ሁሌም ከሚሰጋበት ጉዳይ የሚገላግለውን መፍትሄ በእጁ ማስገባት እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደረሰ። ይህን ለመወሰን ከራሱና ከሌሎች ጋር ሲመከር ከርሟል። ጥቂት ቆይቶ ግን የእሱ የውስጥ ፍላጎትና የሌሎች ምክር እውነት እንዳለው አመነ።
አሁን ከበደ ራሱን ከስጋት የሚጠብቅበትንና ሁነኛ ያለውን መፍትሄ አግኝቷል። አንዳንዶች ሽጉጥ ይዞ መታየትን ለጉራ እንደሚጠቀሙበት ያውቃል። ጥቂት የማይባሉትም መሳሪያን ላልተገባ ጉዳይ እንደሚያውሉት አልጠፋውም። እሱ ግን ለምን ዓለማ እንደሚይዘው ጠንቅቆ ተረድቷል።
ሽጉጥ ለመያዝ በቂ የሚባል ምክንያት የነበረው ከበደ ከተገቢው አካል ህጋዊ የመሳሪያ ፈቃድን ለማግኘት አልተቸገረም። ያለውን እውነታ ሁሉ በተገቢው ምክንያት አሳውቆ ለደህንነቱ ያሰበውን ‹‹ኤም ብሪዊንግ›› መትረየሰ ሽጉጥ ከእጁ አስገባ።
ከበደ መሳሪያውን ከጎኑ ሽጦ መታየት ከጀመረ ወዲህ ደህንነት ይሰማው ይዟል። ለሰራ ሲንቀሳቀስም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ሊደርስበት የሚችለውን ሁሉ ለመመከት ከእጁ ያለው መሳሪያ እንደያሚያግዘው ተማምኗል።
የሚኖርበት አካባቢ ከዝርፊያ ስጋት የራቀ አይደለም። በሰፈሩ ማን እየቀማ እንደሚሮጥ ለአብዛኞቹ እይታ ግልጽ የሚባል ነው። ሁሌም ግን አሳቻን ሰአት ጠብቀው በስለት እያስፈራሩ ከሚዘርፉት መሀል አንዳቸውም ‹‹ተያዙ›› አልያም ‹‹ታሰሩ›› ሲባል አይሰማም። ይህ እውነት ደግሞ ነዋሪውን ከነስጋቱ እንዲቀጥል አስገድዶታል።
ባለታክሲው ከበደ በማለዳ ከቤቱ እየወጣ መርካቶ ገበያን በስራ ይቃኛል። ውሎው ከቀናው ደግሞ ከቤት ለሚጠብቁት ሚስትና ልጆቹ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይዞ ይመለሳል። እነርሱም ቢሆኑ ይህን ልማዱን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሁሌም ደጁን በጉጉት እየቃኙ በናፍቆት ሲጠብቁት ይውላሉ።
የቀድሞ ጓደኛው ፋንታሁን ከእርሱ ከራቀ ቆይቷል። የጠባቸው ምክንያት ባይታወቅም መቀያ የማቸውን ብዙዎቹ እያወሩት ነው። አልፎ አልፎ ድንገት በተያዩ ጊዜ ይገለማመጣሉ። በተለይ ፋንታሁን ጥላቻውን ለማሳየት የማይሆነው የለም። ከንፈሩን እየነከሰና እጁን በእጁ እያማታ በንዴት ይዝታል። በመሀላቸው የተፈጠረው ችግር ከሽምግልና አልፎ እስከ ክስ አድርሷቸዋል። ከሸንጎ ችሎት ያቆማቸው ቅያሜም መቋጫ ሳያገኝ በቀጠሮ ታስሮ ጊዜያትን ተሻግሯል።
ከሳሽ ከበደ ተከሳሽ ደግሞ ፋንታሁን በሆኑበት መንገድ እንደ ዋዛ ሰምንት የጥላቻ አመታት ተቆጥረዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን የክስ ፋይሉ በወጉ ተቋጭቶ አልተዘጋም። ቀጠሮ ሌላን ቀጠሮ እያስከተለ በውጤት አልባነት ሲሻገር ቆይቷል።
የስምንት አመታቱ የክስ ምልልስ ደግሞ ለከሳሽም ሆነ ለተካሳሽ የሚያመች አልሆነም። አንዳቸው የሌላቸውን መሸነፍ እየተመኙ ቀናትን ሊቆጥሩ አስገድዷል። በተለይ ክሱ ለቀረበበት ፋንታሁን እነዚህ አመታት የድካም ዘመን ሆነውበታል። በቀጠሮ ምልልስ ያባከነውን ጊዜ ከባላንጣው ምክንያት ጋር ማዳመሩም የጥላቻውን ከፍታ አሳድጎታል።
‹‹ተበድያለሁ›› ሲል ክስ ያቀረበው ከበደም ቢሆን እነዚህ ስምንት አመታት ጊዜና ጉልበቱን፣ ገንዘብና ሞራሉን በልተውበታል። ጉዳዩ እልባት ቢኖረውና ከፍርድ ውሳኔው የሚሻውን ቢያገኝም ይወዳል። ከበደ ሁሌም ፋንታሁንን ባገኘው ቁጥር መገለማመጥና መዛዛቱ ሰልችቶታል። ‹‹ይቅር›› ብሎ ክሱን እንዳይተው ቸግሮት እንጂ እንዲህ መሆኑን ፈልጎት አያውቅም።
ድንገቴው እይታ
ምሽቱ ገፍቶ፣ጨለማው በርትቷል። በዚህ ሰአት ብዘዎች ብቻቸውን ለመሄድ አይደፍሩም። በመንገዱ ማቋረጥን የሚሹ ቢኖሩ እንኳን ሁለትና ሶስት በመሆን ነው። የዛን ዕለት ምሽት ከበደ ወደቤቱ ለመግባት በጉዞ ላይ ነበር። ጊዜው ገፍቶ ምሽቱ እንዳየለ ቢያውቅም ቤት መድረሱን እያሰበ ወደፊት መጓዙን ቀጥሏል። ከቤቱ አቅራቢ ሲደርስ ግን የፍጥነት ጉዞውን ከሚገታ አጋጣሚ ጋር ተጋፈጠ።
የጨለማው ብርታት እርስ በርስ ለመተያየት ያላገዳቸው ከበደና ፋንታሁን እንደተለመደው ተፋጠጡ። ሁኔታው ድንገቴ የሆነበት ከበደ ጥቂት ደንገጥ ቢልም ፈጥኖ ራሱን ለማበርታት ሞከረ። ወዲያውም ከፊት ለፊቱ ቆሞ ከሚያፈጥበት ባላንጣው ላይ እርሱም አፈጠጠ።
የዚያን ዕለት ምሽት ፋንታሁን እንደሌላው ቀን ብቻውን አልነበረም። በዙሪያው ሌሎችም አጅበውታል። የእነርሱን መኖር ያስተዋለው ከበደ ራሱን ከማንኛውም ጥቃት ለመጠበቅ በማሰብ ዙሪያ ገባውን አማተረ። ከጎኑ የማይለየው ሽጉጡ ዛሬም ከእርሱ ጋር ነው። ለውሳኔ ግን አልቸኮለም። ባላንጣው እየተጠጋው መሆኑን ቢያውቅም የሚሆነውን ሁሉ በትዕግስት ጠበቀ።
ፋንታሁን አጋጣሚውን ለመጠቀም የፈለገ ይመስላል። ለከበደ ከስምንት አመት በፊት የከፈተበትን የክስ ፋይል እያስታወሰ ዛሬም ጉዳዩን ፈጽሞ እንዳልረሳው ሊያሳስበው ፈለገ። አሁንም ክሱን የማያነሳለት ከሆነም በሄደበት ሁሉ እየተከተለ መድረሻ እንደሚያሳጣው ጭምር አስጠነቀቀው።
ፋንታሁን ንግግሩን በአጭር ቃላት ብቻ ገልጸ አላቆመም። ደግሞ ደጋግሞ አሁንም ክሱን ካላነሳለት ሰው በተሰበሰበበት አደባባይ እንደሚደፋው ጭምር ዛተበት። ይህን ሲናገር በስፍራው የነበሩ ሁሉ ደነገጡ። አብረው ያጀቡት ባልንጀሮቹም ጉዳዩን ለማረጋጋት ሞከሩ። ከበደ ይህ አይነቱን ቃል ሲሰማ የመጀመሪው አይደለም። ሁለቱ ድንገት በተገናኙ ቁጥር ከፋንታሁን አንደበት ዛቻውን ሲያደምጠው ቆይቷል። ዛሬም ቢሆን ሌሎች በአባባሉ ሲደነግጡ የእሱ ግርምታ እምብዛም ሆኗል።
ይህ አመታትን የተሻገረ ቂምና በቀል የፍርድ ቤት ውሎ ሳይቋጨው በዛቻና ማስፈራራት እየተዋዛ ቀጥሏል። ይህ ቅራኔው ከተከሰተ በኋለ የሁለቱም ጆሮዎች የሚባለውን ሁሉ ከመስማት ቦዝነው አያውቁም። በመሀላቸው ያሉ ነገር አመላላሾችም ቢሆኑ የአንዳቸውን ስሜት ለሌላቸው ለመንገር አጋነውና ጨማምረው ወሬ መቀመማቸውን አልተውም። እነሱም የሚባለውን ሁሉ ሳይንቁና ሳይጥሉ መቀበላቸው አልቀረም። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ነገሩን ከማዳፈን ይልቅ ጉዳዩን እያጋጋመ በእሳት ላይ ቤንዚን የመጨመር ያህል ሆኗል።
ህዳር 30 ቀን 2005 ዓም ምሽት
ሁለቱ ጠበኞች ከተገናኙ ጥቂት የሚባሉ ቀናት ተቆጥረዋል። ከበደ ከዛንለታው አጋጣሚ በኋላ የመንገዱን ግራና ቀኝ አያምነውም። የፋንታሁን ተደጋጋሚ የ‹‹እደፋሃለሁ›› ዛቻም ከልቡ ገብቷል። ለአባባሉ የሰጠው ትርጓሜ ደግሞ ከወትሮው የተለየ ሆኗል። አሁን የበለጠ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ለውስጡ ደጋግሞ እየነገረው ነው።
በህዳር ወር የመጨረሻው ምሽት ደግሞ እንዲህ ተከሰተ። ከበደ ወደቤቱ ለመግባት በእግሩ ጉዞ ጀምሯል። ጥቂት እንደተራመደ ግን ፋንታሁንን ከመንገዱ ቆሞ አገኘው። ከእርሱ ጋር ሶስት ጓደኞቹ አብረውት አሉ። ሁኔታቸው ባያምረውም አስቀድሞ ምንም ለማለት አልፈለገም። አመጣጣቸው ለበጎ አለመሆኑ ቢገባው መንገዱን ለቆላቸው ሊያስቀድማቸው ፈለገ። እነርሱ ግን በቅርበት እየተጠጉት ባለበት እንዲቆም አስጠነቀቁት። ከበደ ቃላቸውን አድምጦ ትዕዛዙን አላከበረም። ድንገት አዘናግቶ በሩጫ ወደፊት ተፈተለከ።
ፋንታሁንና ጓደኞቹ በድርጊቱ ተናደው ከኋላው ተከተሉት። እያባረሩት እጃችው ስራ አልፈታም። ከመንገዳቸው ያገኙትን እያነሱ የድንጋይ ሩምታ አወረዱበት። ከበደ በጨለማው ተሽሎክልኮ ከቤቱ ሲደርስ አባራሪዎቹ ተስፋ ቆርጠው ተመለሱ።
ከበደ ከአካባቢው ብዙ ያለመራቃቸውን ሲያውቅ ወደቤቱ ገብቶ ለባለቤቱ ሰዎቹን በርቀት አሳያት። እሷ በድንጋጤ መሀል ብትሆንም ከፋንታሁን ጋር የነበሩትን አሻግራ ለማየት ሞከረች፤አልተሳሳተችም። ከአራቱ መሀል አንደኛው በቅርቡ ጨለማን ተገን አድርጎ በስለት አስፈራርቶ ሞባይሏን የወሰደባት ወጣት ነበር።
አሁን ከበደ፣ ፋንታሁን ከነማን ጋር እንደሚውል አውቋል። ይህን ማወቁ ደግሞ ይበልጥ ራሱን እንዲጠብቅና በጊዜ ወደቤቱ እንዲገባ አስጠንቅቆታል። ሁሌም ማለዳ ለስራ ወጥቶ ሲመለስና በመንገዱ ሲንቀሳቀስ ዙሪያ ገባውን በትኩረት ይቃኛል። ከሰፈሩ ከሚገኝ የቀበሌ መዝናኛ ጎራ ማለትን የለመደው ባለታክሲ ጥቂት ቆየት ብሎ ወደቤቱ ይመለሳል።
ታህሳስ 4 ቀን 2005 ዓም ንጋት
ከበደ ዛሬም ወደ መርካቶ ለመሄድ ዕቃ ጭኖ የወጣው ሌሊቱ ለንጋት ስፍራውን ሲያስረክብ ነበር። እንደተለመደው ረዳቱን ጠርቶ ራሱን ለስራ አዘጋጅቷል። ከመኪናው ጣራ ላይ ሆኖ ጭነቱን እያሰረም ተመልሶ የሚከውነውን ያስባል። በዚህ መሀል ግን አንድ የሚያውቀው ድምጽ ወደ ጆሮው ደረሰ።
ከበደ ድምጹን ወደሰማበት አቅጣጫ መለስ ከማለቱ ፋንታሁንን አየው። ንዴት ይነበብበታል። ፊት ለፊት እንደተያዩም ከሄደበት ሲመለስ እንደሚያገኘው ከዛቻ ጋር አሳሰበው። ከበደ በንግግሩ ቢገረምም ሀሳቡን እንደ ሌላው ቀን ችላ ሊል አልተቻለውም።
ከበደ የዕለቱን ስራ ያጠናቀቀው እኩለቀን አካባቢ ነበር። እንዲህ በሚሆን አጋጣሚ ደግሞ ከሰፈሩ ከሚገኝ የቀበሌ መዝናኛ አረፍ ብሎ ጊዜ የማሳለፍ ልማድ አለው። የዛንለታም የሆነው እንዲሁ ተመሳሳይ ነበር። ከበደ ከስራ መልስ ወደ ስፍራው ደርሶ ውሀውን እንደያዘ ተቀምጧል። በድንገት ግን ከአንድ ጥግ ተቀምጦ የቆየው ፋንታሁን ተነስቶ አፈጠጠበት።
ጉዳዩ ፈጣን የሆነበት ከበደ ጊዜ አልሰጠውም። አመጣጡን ተረድቶ ፊት ለፊት ተጋፈጠው። አንገት ለአንገት ሲያያዙ አንዳንዶች ከመሀል ሊገቡ ሞከሩ። የሁለቱ ድብድብ ማየሉ ግን ለግልግል የሚያመች አልሆነም። ባላንጣዎቹ እንደተያያዙ ከመሀል ወለል ወደቁ። አንዳቸው ሌላቸውን ለማጥቃት የሚያደርጉት ሙከራ አስደንጋጭ ነበር።
ከበደ ፋንታሁን ያለምክንያት ሊያገኘው እንዳልፈለገ ሲገባው በተለየ ሁኔታ ታገለው። በድብድቡ መሀል ደጋግሞ ኪሱን እየፈተሸ መሆኑ እየተሰማው ነው። አሁን የዛቻውን ውጤት በግልጽ ተረድቷል። እሱም ቢሆን መሳሪያ ይዞ እንደመጣ አውቋል። ሀሳቡን እውን ከማድረጉ በፊት ግን ሊቀድመው እንደሚገባ ወሰኗል።
ገላጋዮቹ ከበው መጮሀቸውን አላቆሙም። በዚህ መሀል ከከበደ ወገብ በድንገት ሽጉጥ ሲወጣ ያዩ ከአካባቢው ለመራቅ ተራወጡ። ይህ አፍታ እምብዛም አልቆየም። የወጣው ሽጉጥ በተተኮሱ ጥይቶችና ከባድ ድምጽ ታጅቦ በባሩድ ሽታ ስፍራውን አጠነው።
የጥይቱን ድምጽ ተከትሎ ከበደ ከግቢው ሮጦ ሲወጣ ታየ። ስፍራው በደም እንደተበከለም የፋንታሁንን ተጎድቶ መውደቅ ያዩ ጉዳዩን ለህግ ለማሳወቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመሩ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ጥቆማውን ተከትሎ ከስፍራው ሲደርሰ ተጎጂውን በህይወት አላገኘውም። በአካባቢው ያገኛቸውን መረጃዎች በተገቢው ማስረጃዎች አደራጅቶ የሟችን አስከሬን እንዳነሳም ተጠርጣሪውን ለመያዝ ተንቀሳቀሰ።
ፖሊስ ተፈላጊውን በቁጥጥር ስር አውሎ ጥያቄውን አቀረበ። ገዳይ ሟችን ለመግደል አስቦ ያለመውጣቱንና በስፍራው የተገኘው ለሌላ ጉዳይ እንደነበር ተናገረ። ድርጊቱን የፈጸመው በሟች ኪስ መሳሪያ መኖሩን ጠርጥሮና ሳይቀድመው ለመቅደም አስቦም መሆኑንም አስረዳ።
መርማሪው የተጠርጣሪውንና የምስክሮችን ቃል መርምሮ ተገቢውን መረጃ አሰፈረ። በምክትል ሳጂን ሲሳይ ተሾመ የሚመራው ቡድንም የህክምና ማስረጃን ከቴክኒክ ምርመራዎች፣ ከምስክርነት ቃልና ከሌሎች ወሳኝ ማሰረጃዎች ጋር አዛምዶ ዓቃቤህግ ክስ ይመሰርት ዘንድ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 385/05 የተመዘገበውን መረጃ አሳልፎ ሰጠ።
ውሳኔ
ታህሰስ 4 ቀን 2007 ዓ.ም የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀጠሮ ሲመለከተው የቆየውን ጉዳይ ውሳኔ ለመስጠት ዳኞችን ሰይሟል። ተከሳሹ የቀረበበት ህጋዊ ማስረጃዎችና የሰው ምስክሮች ወንጀሉን ስለመፈጸሙም አመላክተዋል። የተከሳሹን ጥፋተኝነት ያረጋገጠው ፍርድቤት ሆን ብሎ የሰው ህይወት ባጠፋው ከበደ ሹሜ ላይ ባሳለፈው ፍርድ እጁ ከተያዘበት ቀን አንስቶ በሚታሰብ የሀያ አመት እስራት ከማረሚያ ይቆይ ሲል ወሰኗል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
መልካምስራ አፈወርቅ