አዲስ አበባ፡- በኢንዱስትሪ ፓርኮች
ለምርት አስፈላጊ ነው ተብሎ ከተጠየቀው 306 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የቀረበው 145 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን የኢንዱስትሪ
ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበኩሉ፤ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከዛሬ ተቋሙ የኃ ይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚያከናውነው በብድር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጫና ውስጥ መግባቱን አስታውሶ ፓርኮቹ በእራሳቸው ወይም በመንግሥት ብድር ኃይል ማስተላለፊያውን ከገነቡ ኤሌክትሪኩን እንደሚያገኙ ገልጿል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አስግዶም እንደገለጹት፤ በአጠቃላይ ለተገነቡ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች 306 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ቢጠየቅም እስከአሁን ድረስ እየቀረበ ያለው 145 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ብቻ ነው። በመሆኑም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር አንዳንድ ፓርኮች ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠረ ይገኛል።
እንደ አቶ አማረ ገለጻ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱ በተለይ መቐለ እና አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ችግሩ ይሰፋል። በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ 33 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ተጠይቆ የቀረበው ግን ዘጠኝ ሜጋ ዋት ነው። በተመሳሳይ በመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚያስፈልገው 30 ሜጋ ዋት ውስጥ የቀረበው ስምንት ሜጋ ዋቱ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ያለው የኃይል መቆራረጥ በፋብሪካዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ በፌዴራል መንግሥት በኩል ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ እቅድ ተይዟል። ይሁንና እንደፀሐይ ኃይል እና ሌሎች አማራጭ የኃይል ምንጮች በመጠቀም ለፓርኮቹ ዘላቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማሰብ ያስፈልጋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት አለባቸው። የኤሌክትሪክ አቅርቦቱ እጥረት ደግሞ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም እንደሚቀንሰው ይታወቃል። በመሆኑም ለእያን ዳንዱ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚያስፈልገው የኤሌ ክትሪክ ኃይል መጠን ለማቅረብ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ በመንግሥት ደረጃ የሚከናወኑ ሥራዎችን ማከናወን ይገባል። በተለይ በቀጣዩ ሁለት ዓመታት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥር 30 ስለ ሚደርስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል /ኢኤኃ/ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በብድር ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚውል የኤሌክትሪክ መስመር ማስተላለፊያ ግንባታ ሲያከናውን ቆይቷል። ይህ አሰራር ተቋሙን ለከፍተኛ የብድር ጫና ስለዳረገው ከዚህ በኋላ ለፓርኮቹ ኃይል ማስተላለፊያ ግንባታ ተበድሮም ሆነ በራሱ ወጪ አያከናውንም። እንደ ተቋም በተያዘው አሰራር መሰረት ትልልቅ ኃይል ፈላጊ ኢንዱስትሪዎች ኤሌክትሪክ ኃይል ሲፈልጉ ለኃይል ማስተላለፊያ የሚሆነውን ወጪ መሸፈን አለባቸው።
አንድ ግለሰብ እንኳን ኤሌክትሪክ ሲፈልግ ከአቅራቢያው ካለው መስመር እስከ ቤቱ ድረስ ያለውን የማስተላለፊያ መስመር ወጪ ሲከፍል ብቻ አገልግሎቱን የሚያገኝ መሆኑን አመልክተዋል። በተመሳሳይ ኢንዱስትሪ ፓርኮ ችም ይህን አሰራር መከተል እንዳለባቸው አስገ ንዝበው፤ መሰረተ ልማቱን ለመገንባት የሚያስችል ፋይናንስ ካቀረቡ ግን ድርጅታቸው ኃይል ለማቅረብ ችግር የሌለበት መሆኑን አስረድተዋል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወደቻይና በሄዱበት ወቅት ለፓርኮችና ለባቡር ኃይል አቅርቦት የሚውል 1ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ ሞገስ፣ እንደነዚህ አይነት የመንግሥት ጥረቶች የኃይል አቅርቦቶችን ችግር ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
እንደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ስር ከሚገኙ 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተጨማሪ በግል ድርጅቶች የሚገነቡ ተጨማሪ 12 ፓርኮች ይገኛሉ። ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ የሚፈለገው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ1ሺ700 ሜጋ ዋት በላይ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ፣ ነሀሴ 4/2011
ጌትነት ተስፋማርያም