መረን የለቀቀ የግብይት ሥርዓት ልጓም እንዲበጀትለት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ይደመጣሉ። መንግሥት ፍትሐዊ የሆነ የውድድር ሜዳ በማመቻቸት የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት።
የሸማቾችና የንግድ ሥራዎች ውድድር ባለስልጣን ሕግ በማውጣት ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ ነው። ሕግ ቢኖርም የቁጥጥር ሥርዓቱን የሚያስፈጽሙ አካላት ወይም ግለሰቦች በብቃት ሥራቸውን እየሠሩ ስለመሆናቸው ግን አጠያያቂ እየሆነ መጥቷል።
በአገራችን ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚታዩት በርካታ ችግሮች የሥር ነቀል ለውጥ ያለህ እያሉ ባሉበት በዚህ ወቅት በአምስቱም የአዲስ አበባ መውጪያና መግቢያ በሮች አርሶ አደሮች ምርታቸውን የሚያስቀምጡባቸውንና ለገበያ የሚያቀርቡባቸውን ማዕከላት ለመገንባት መታቀዱን ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ለመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ያቀደው ተግባር እውን ሲሆን ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ያቃተው በሴራና በአሻጥር የተተበተበ የግብይት ሥርዓት ለሕዝቡ አቅም እንዲውል ያደርግ ይሆን?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ታምሩ ባልቻ እንደሚሉት፤ የዋጋ ንረቱ አንዱ ምክንያት የገበያ ሰንሰለቱ በመርዘሙ ነው። በአምራችና ሸማች መሀል የበርካታ ተጋሪ ሰዎች ጣልቃ ገብነት አለ። በዚህ ሂደትም የምርት ዋጋው ከፍ እያለ ይሄዳል። በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእህል ሰብሎች ምርት ላይ ያለው ችግር አብዛኛውን ጊዜ ገዢውና ሻጩ በአንድ ነጋዴ አማካኝነት ብቻ የሚገናኙበት መንገድ ጠባብ ነው። የግብይት ሰንሰለቱ በርካታ ሂደቶችን ያልፋል።
‹‹በግብይት ሰንሰለቱ ውስብስብነት ምክንያት ሸማቹ ላይ የሚደመረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው። በዚህ ሂደት አርሶ አደሩም ተጠቃሚ አይሆንም። አርሶ አደሩ የሚያመርተው ምርት ለሸማቹ ማህበረሰብ የሚደርሰው በእጥፍ ጨምሮ ነው። ይህ ሁለቱንም አካላት ማለትም ሻጭና ገዢውን የማይጠቅም አካሄድ ነው›› ሲሉ አቶ ታምሩ የግብይት ሥርዓቱን ሂደት ይዳስሳሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራያ፤ አዲስ በሚገነቡት የገበያ ማዕከላት ደላሎችን ጨምሮ በመሀል የሚገቡ ነጋዴዎች ቁጥር ማሳነሱ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሸማቹ ማህበረሰብ ትልቅ ተስፋ ነው። አርሶ አደሩ በቂ ሀብት ለማግኘትና የበለጠ ምርት ማቅረብ ያስችለዋል። ለሸማቹ ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን እንዲያገኙ ያግዛል።
ነገር ግን ምንም እንኳን የገበያ ማዕከሉን ለማቋቋም ቢታቀደም ደላላን መከላከል አስቸጋሪው ጉዳይ ነው። በደላሎች በኩል የሚፈጸሙ አግባብ ያልሆኑ በደሎች የሚገቱበትን ሥርዓት አብሮ ማስኬድ ይገባል። ይህንን የሚቆጣጠር አካል ከሌለ አፈጻጸሙ ላይ ችግር ሊከሰት ይችላል። የግንባታው ሀሳብ መልካም ቢሆንም አርሶ አደሩ የለፋበትን እንዲያገኝ፣ ሸማቹም ሳይጉላላ ምርቱን በቅናሽ ቀጥታ እንዲያገኝ የቁጥጥሩ ጉዳይ አብሮ ታሳቢ ሊደረግበት ይገባል።
አቶ ታምሩ፤ አርሶ አደሩ በቀጥታ ለሸማቹ ማህበረሰብ ምርቱን የሚያቀርብበት መንገድ ጠባብ በመሆኑ፤ በዚህ ሀሳብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት አርሶ አደሮች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ግንባታው በአምስቱም የከተማዋ መውጫና መግቢያ በሮች ማድረጉ ደግሞ የከተማዋን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል። ምንም ሳይሰሩ በምላሳቸው ብቻ ከሸማቹም ሆነ ከአርሶ አደሩ በላይ እየተጠቀሙ ያሉት አካላትን ቁጥር ከመቀነስ አኳያም ፋይዳው ቀላል አይደለም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ይህ አይነቱን ሀሳብ ተግባራዊ ያደረገ አሸዋ ሜዳ ላይ የገበያ ማእከል ተቋቁሞ እንደነበርና ይህም በዘላቂነት ጥቅም ሲሰጥ እንዳልነበር፤ አሁን ላይ የታቀደው ግንባታም ሲከናወን መገንባት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊነቱ ክትትል እንደሚያስፈልገው አቶ ታምሩ ያስገነዝባሉ።
የገበያ ማዕከል ግንባታውን ማከናወን የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ ብዙ ለውጥ አያመጣም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በኑሮ ውድነት ምክንያት ድህነት እየተስፋፋ መጥቷል። የዚህም ምክንያት የእቃ እጥረት፣ ብዙ ገንዘብ መኖርና ነጋዴው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ነው።
‹‹አሁንም ቢሆን አርሶ አደሩ በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሮች ምርት ቢያቀርብ ነጋዴውና ደላላው ነው የሚረባረብበት። ስለሆነም ነጋዴው የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ይረዳዋል። መፍትሄ ሊሆን የሚችለው መንግስት ከነጋዴው ጋር ተወዳድሮ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ሱቆችን በማብዛት መስራት ቢችል የተሻለ አማራጭ ይሆናል። መንግስት በቅናሽ ዋጋ ምርቱን እንዲያቀርብ ቢደረግ ነጋዴው ራሱ የዋጋ ቅናሽ ያደርጋል። ይህም የማህበረሰቡን የኑሮና ኢኮኖሚ ሁኔታ ያሻሽላል›› ይላሉ- ፕሮፌሰሩ። ማዕከሉ በመንግስት ቁጥጥር ሥር መሆን እንዳለበትም ይገልጻሉ።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት፤ የገበያ ማዕከሉ ይገነባባቸዋል ተብሎ በታሰበባቸው አካባቢዎች ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተው ግዥ ለመፈጸም ስለሚቸገሩ ነጋዴው የበላይነትን እንዲያገኝ እድል ይከፍትለታል። በዚህ ሂደት ውስጥ አርሶ አደሩ በጥቂቱ ሊጠቀም ይችላል። ይህ መልካም ቢሆንም የሸማቹ ማህበረሰብን ተጠቃሚነት ማዕከል አለማድረግ ደግሞ አሁንም ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።
በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ነጋዴዎች ጤናማና ፍትሐዊ በሆነ ውድድር እየተፎካከሩ ባለመሆናቸው፤ በአሁኑ ጊዜም አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች በስፋት የመወዳደሪያ ሜዳውን መውረራቸውን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ፤ በአም ራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ አከፋፋይነትና በቸርቻሪነት ሥራዎች ውስጥ የተሰማሩ የተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ጤናማ ውድድር እንዳይኖር እያደረጉ መሆናቸውን፤ የምርትና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዋጋ እንደፈለጉ እንደ ሚወስኑ፤ የአቅርቦትና የሥርጭት መስመሮችን እንደሚዘጉ፤ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ እንደሚቆልሉና ሰላማዊና ጤናማ መሆን የሚገባውን የውድድር ሜዳ በማጣበብ ሕገወጥነትን እያስፋፉ መሆኑን ይጠቅሳሉ። በመሆኑም ሊገነባ በታቀደው የገበያ ማዕከል እነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የግብይት ሥርዓቱን ከዘመናዊ አሠራር ጋር በማጣላት ሕዝቡን እንዳይበዘብዙ ስጋት አለኝ ብለዋል።
ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ ‹‹ገበሬው ቀጥታ ለሸማቹ የማያደርስ ከሆነ ደግሞ ለውጥ ስለማይኖረው መገንባቱ ፋይዳ የለውም። ይልቅ የግንባታው ዓላማ መንግስት ፍትሐዊ የትርፍ ሕዳግ አድርጎ ምርቱን ከአርሶ አደሩ ተቀብሎ ለሸማች ማህበረሰብ የሚያከፋፍልበት መሆን ይኖርበታል። ካልሆነም ከአምስቱ የገበያ ማዕከላት ተቀብሎ በየአካባቢው ባሉት ሸማች ማህበራት ቢያቀርብ ችግሩን ሊያቀለው ይችላል። የነጋዴውን ትርፍ ለመቀነስ መሞከርም መንግስት ሊወጣው የሚገባ ተግባር ነው›› ይላሉ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ የአገሪቷ የዋጋ ልምድ በገበያው ስሪት አንድ ጊዜ ዋጋው ከወጣ አቅርቦቱ ቢኖር እንኳን አይወርድም። እቃ ሲበዛ ዋጋ ይወርዳል የሚለው የነጻ ገበያ አስተምሮም ተግባራዊ ሲደረግ አይስተዋልም። በመሆኑም የመንግስት ተወዳዳሪ መሆን የገበያውን ድክመት ሊያሻሽለው ይችላል። ገበያው መከፈቱ በመንግስት ህግና ቁጥጥር መሠረት ከሆነ ዋጋው እንዲወርድም ያደርጋል።
ጤነኛ የሚባል የግብይት ሥርዓት ዋነኛ ተዋናዮቹ ማለትም ሸማች፣ ነጋዴና መንግሥት እየተናበቡበት በሥርዓት እንዳካሄድ ምሁራን ይመክራሉ። እነዚህ ሦስት አካላት በሚገባ ካልተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ እንደሚታወክ፣ በ ተ ለ ይ ኢ ኮ ኖ ሚ ው በ ነ ፃ የ ገ በ ያ ሥ ር ዓ ት ይመራበታል በሚባልበት አገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ ከታወከ በሥርዓተ አልበኞች ለመወረሩ ማሳያ እንደሚሆንና ሦስቱ አካላት ካላቸው ሚናና ኃላፊነት አንፃር የሚታዩትን ችግሮች መፍታት እንዳለባቸውም ይናገራሉ። በዚህም አምራቹ እና ሸማቹ እንዲሁም ነጋዴው ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 3/2011
አዲሱ ገረመው