– 21ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፤
– በ9ሚሊዮን ብር ሁለት ጎታች ጀልባዎች ተሠርተውለታል፤
– አሁን ሥራ ለማስጀመር ከ5ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል፤
በጣና ሐይቅ ጎርጎራ ወደብ ላይ ነን። ወደቡ የጀልባ መስሪያና መጠገኛ ክፍሎች እንዲሁም የሆቴል አገልግሎት ይሰጣል። ከወደቡ ተጠግቶ ግማሽ አካሉን ውሃ ውስጥ ዘፍዝፎ ግማሹ ለፀሐይ ተጋልጦ የባለቤት ያለህ እያለ ለዓመታት የኖረ አንድ ትልቅ የደለል ማውጫ ማሽን ይገኛል።
«ድሬጂንግ ወይም ድሬጀር ማሽን» ይሉታል ባለሙያዎቹ፤ የጣና ሐይቅን ደለል ለማውጣት ታስቦ ነበር በውጭ ምንዛሬ የተገዛው። ካለምንም ፋይዳ ለዓመታት በእንቦጭ በሚታመሰው ጣና ሐይቅ ላይ ተቀምጦ ይገኛል።
ትልቋ የዕቃና የሰው ማመላለሻ ጀልባ «ጣናነሽ»ን በወደቡ ሲያድሱ ያገኘኋቸው የጀልባዋ ካፒቴን አቶ ስጦታው አላምረው፤ የደለል ማውጫ ማሽኑን «የተረሳ ንብረት ሆኗል» ይላሉ። ከስድስት ዓመት በፊት ሲመጣ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያውያን ጋር ገጣጥመው እና ሞክረው ነበር ያስረከቡት። አሁን ግን ባለቤት አልባ ሆኗል። ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ጎታች ጀልባ ለማሽኑ ተሠርቶለት ያለሥራ ሐይቁ ላይ ከማሽኑ ጎን አብሮ ታስሮ ተቀምጧል። አብሮ የተገጠመው ጀኔሬተርም ማሽኑ ላይ እንዳለ ካለሥራ በመቀመጡ የመበላሸት እጣፋንታ እንደሚገጥመው መስጋታቸውን ይናገራሉ።
ማሽኑ ለዓመታት ውሃ ውስጥ መቀመጡን የሚናገሩት ካፒቴኑ፤ ባለቤት ነኝ የሚል አካል አለመምጣቱ አሳዝኗቸዋል። ከአስር ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ጣና ሐይቅ ከፍተኛ የደለል ስጋት ስላለበት እንደቻድ ሐይቅ ሊጠፋ ይችላል የሚል ስጋት ስለነበረ ነው። ይህንን ታሳቢ ተደርጎ ቢገዛም እስከአሁን አገልግሎት ለመስጠት አልተቻለም። ማሽኑ ወደ ሥራ ቢገባ ኖሮ ደለሉን በመጥረግ ለአካባቢ ጥበቃ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ይሆን ነበር። ያለአገልግሎት ረጅም ጊዜ በመቀመጡ በየጊዜው በሐይቁ በሚነሳው ማዕበል ምክንያት ወደቡን እያፈራረሰው መሆኑ አቶ ስጦታውን አሳስቧቸዋል።
ጉዳዩን ይዤ ወደቡን ወደሚያስተዳድረው የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅት ዋና መስሪያቤት ባህርዳር አቀናሁ። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙላት ፀጋው እንደሚገልጹት፤ ማሽኑ ወደ ወደቡ የመጣው በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ነው። ድርጅቱ በባለቤትነት ቢረከበውም ለጣና በለስ የተቀናጀ ውሃ ሀብት ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ በሚል በውጭ ፈንድ አማካኝነት የፌዴራል ውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ነው የገዛው። ማሽኑ ለረጅም ጊዜ ያለሥራ የተቀመጠው የመለዋወጫ ጉድለት ስለነበረበት ሲሆን፤በተጨማሪ ለማሽኑ ማንቀሳቀሻ የሚሆኑ ሁለት ጀልባዎች ተሠርተውለታል። ደለል ማውጫው ቱቦ ተገጥሞለት እስከ አምስት መቶ ሜትር ርቀት የሚገኝ አሸዋና አፈር ያወጣል ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ ነው። ለማሽኑ የሚያገለግሉ ስድስት ሜትር ርዝመት ያላቸው 200 የብረት ቱቦዎች በተጨማሪ ወጪ ቢገዙም አሁንም በድርጅቱ ግቢ ቦታ ይዘው ያለአገልግሎት ተቀምጠዋል። አንዱ ሁለት ነጥብ ስድስት ኪሎ የሚመዝን ብረት በመሆኑ ውሃ ላይ የመንሳፈፉ ጉዳይም አጠራጣሪ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሙላት ገለጻ፤ የጣና ሐይቅ ውሃ በደለል ምክንያት እየቀነሰ ነው። ለአብነት ደልጊ ወደብ በደለል የተጠቃ በመሆኑ ጀልባዎች ወደቡን ለመጠጋት ባለመቻላቸው እስከ ሦስት መቶ ሜትር ድረስ እየራቁ ለመቆም ተገደዋል። በሌላ በኩል ለእምቦጭ አረም ምቹ ነው የሚባለው ደለሉ ከጠፋ የእንቦጭ አረም ይቀንሳል። ምክንያቱም አረሙ ደለል በበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ስር ሰዶ ይቆያልና። በውሃ ላይ ሲበቅል ግን ከሳምንት በኋላ ይደርቃል። በመሆኑም መሳሪያው ደለል ማውጣት ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የእንቦጭ አረምን ችግር ሊቀርፍ ስለሚችል የማሽኑ አስፈላጊነት እንደማያጠያይቅ ያስረዳሉ።
ማሽኑን ያመጣው የጣልያን ኩባንያ ድጋሚ ስልጠና ሰጥቶ አገልግሎት እንዲጀምር ካልተደረገ ደለል ማውጫው አገልግሎት ሊሰጥ አይችልም። ወደ ሥራ እንዴት ይግባ? የሚለውም ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ማሽኑን ወደሥራ ለማስገባት በማሰብ አባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ተረክቦ እንዲሠራበት በመወሰኑ በቅርቡ የሰነድ ልውውጥ መደረጉንም ይናገራሉ።
የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ የወንድወሰን መንግሥቱ በበኩላቸው ማሽኑ የተገዛው በቀድሞው ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አማካኝነት ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ መሆኑን ያስታውሳሉ። ወጪውም 21 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነበር። «ማሽኑ ከውጭ ሲመጣ ተሟልቶ እንዲቀርብ መደረግ የነበረባቸው ያልተሟሉ ክፍሎች ስለነበሩበት የሚፈለገውን አገልግሎት አልሰጠም። ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያውያን አዲስ ስለነበርና መለዋወጫዎች ተሟልተው እንዲገቡ አልተደረገም። ነገርግን ያለሥራ ሐይቁ ውስጥ ያለሥራ በመቀመጡ ወደሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነበር» ይላሉ።
እንደ አቶ የወንድወሰን ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ማሽኑ ጥገና አግኝቶ ሥራ እንዲጀምር ማሽኑን ያስገባው ድርጅት ባለሙያዎች እንዲመጡ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ማሽኑን ለማስነሳትና ስልጠና ለመስጠት ባለፈው ዓመት 160 ሺ ዩሮ(ከ6ሚሊዮን ብር በላይ) ክፍያ ተጠይቆ ነበር። አሁን ጊዜው በመሄዱ ክፍያው ሊጨምር ይችላል። ስልጠናው ከተሰጠና የጎደሉ ዕቃዎች ከተሟሉ ማሽኑ ባፋጣኝ ሥራ ይጀምራል። መቼ ይጀምራል? የሚለውን ግን እርሳቸውም በውል አያውቁትም። በደፈናው «ቀኑ ይሄ ነው ማለት ባይቻልም፤ በጀት ከተገኘ እና ስልጠናው ከተሰጠ በኋላ ይጀመራል» ይላሉ።
የቀድሞው የጎርጎራ ወደብ ኃላፊ የነበሩትና አሁን የአማራ ብረታብረት ኢንዱስትሪና ማሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኢንተርፕራይዝ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዳንኤል ጌራ፤ ማሽኑ ሲገዛ ስፔሲፊኬሽን ያዘጋጀው ኮሚቴ ውስጥ ሠርተዋል። በዓለም ባንክ ድጋፍ የተገዛው ማሽን በሰዓት አንድ ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያጣራ ከደለል ነፃ እንደሚያደርግ ይናገራሉ። መሳሪያው ሲመጣ ግን ደለል ማስወገጃ ቱቦዎቹ ባለመኖራቸው ሥራ ላይ አልዋለም። ቱቦዎቹ በአገር ውስጥ ከተመረቱ በኋላ ደግሞ ብረት በመሆናቸው ውሃ ላይ መንሳፈፍ የሚችሉበት መንገድ ያስፈልግ ነበር። እነዚህ ችግሮች ተደማምረው ማሽኑ እንዲቆም ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።
እርሳቸው በሰጡኝ ሰነድ መሰረት የማሽኑ ግዢ ጨረታ ሰነድ ሲዘጋጅ «Technical Evaluation» በሚል መስፈርት ተዘርዝሯል። በመስፈርቱም ስር ማሽን አቅራቢው ድርጅት ያስረከበው መሳሪያ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ቢያንስ እስከ ሦስት ሺ የሥራ ሰዓታት ድረስ አስፈላጊው መለዋወጫ ዕቃዎች ቢኖሩ የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት ሰፍሯል።
አቶ ዳንኤል አስራት በቀድሞ የፌዴራል ውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የጣና በለስ የተቀናጀ ውሃ ሀብት ልማት ፕሮጀክት የቁጥጥር እና ምዘና ባለሙያ እንዲሁም የፕሮጀክት አስተባባሪ ተወካይ ሆነው አገልግለዋል። አሁን በሚኒስቴሩ የብሔራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም የቁጥጥር እና ምዘና ባለሙያ ናቸው። ማሽኑ ሲገዛ በፕሮጀክቱ ስር ነበሩ። ማሽኑ ዋና ሥራው እንደርብ እና ጉመራ ያሉ ትልልቅ ወንዞች ወደሐይቁ በሚገቡበት ቦታ ላይ ያለውን ደለል ለማውጣት መሆኑን ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ዳንኤል ማብራሪያ ፤ ማሽኑ ከመጣ በኋላ ያለውን የመለዋወጫ ችግር ለመቅረፍ የገንዘብ ችግር አጋጥሞ ነበር። በዚህ ምክንያት ውሃ ውስጥ ያለሥራ ለዓመታት ተቀምጧል። አሁን ግን የአባይ ተፋሰስ ባለስልጣን ስለተረከበው ችግሮቹን በጋራ በመቅረፍ በቀጣይ ወደ አገልግሎት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። ቀሪው ተግባር የውጭ ምንዛሬ በማፈላለግ ባለሙያዎች አስመጥቶ መሳሪያው እንዲሠራ የሚያስችል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ማሽኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት ተመሳሳይ ማሽኖች መካከለኛ የሚባል አቅም ያለው ነው። በመሆኑም በፍጥነት ወደሥራ የማስገባቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ ይህን ያህል ዓመት ያለሥራ ለመቆየቱ ተጠያቂው ማን ነው? የሚለው ጉዳይ ሊጣራ ይገባል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2011
ጌትነት ተስፋማርያም