
ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በደቡባዊ እሥራኤል ባርሺባ ከተማ የሚገኘውና በእሥራኤል ትልቁ ከሚባሉት አንዱ ሶሮካ ሆስፒታል መመታቱን እሥራኤል አስታወቀች። ኢራን ትናንት ጥዋት የፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት ዒላማ ያደረገው ቤርሼባ በተሰኘችው ከተማ ከሚገኘው ሆስፒታል አጠገብ የሚገኝ ወታደራዊ ስፍራ እንጂ ሆስፒታሉ እንዳልሆነ የኢራን የመንግሥት ሚዲያ ዘገበ።
እንደ ዜና ወኪሉ ከሆነ ጥቃቱ ያነጣጠረው የእሥራኤል መከላከያ ሠራዊት “የትዕዛዝ እና የመረጃ ዋና መሥሪያ ቤት” እንዲሁም በጋም ያም ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘው የመረጃ ማዕከል ላይ መሆኑን ነው። “ሆስፒታሉ የተጋለጠው ለፍንዳታዎቹ ብቻ ነው እንዲሁም ከባድ ጉዳት አልደረሰበትም። ነገር ግን ቀጥታ ዒላማ የነበረው ወታደራዊ መሠረተ ልማት ነው” ሲል ዘገባው ጠቁሟል።
የጋቭ ያም ኔጌቭ የቴክኖሎጂ ፓርክ “ከቤን ጉሪዮን ዩኒቨርስቲ ካምፓስ እንዲሁም የእሥራኤል መከላከያ ሠራዊት “የትዕዛዝ እና የመረጃ ዋና መሥሪያ ቤት” አቅራቢያ እንደሚገኝ” በድረ ገጹ አትቷል።
በእሥራኤል ደቡባዊ ክፍል ቤርሼባ በተሰኘች ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል በኢራን የሚሳኤል ጥቃት ተመትቷል። ኢራን የሚሳኤል ጥቃቱ ዒላማ በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኝ ወታደራዊ ይዞታ መሆኑን አስታውቃለች።
ኢራን ባስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች በተጨማሪም ሦስት የሲቪል ስፍራዎች መመታታቸውን አንድ የእሥራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን ገልጸዋል። በስፍራው በርካታ ሚሳኤሎች መወንጨፋቸውን እና በቴልአቪቭ እና እየሩሳሌም ፍንዳታ መሰማቱ ተገልጿል።
የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ “ሆስፒታሉ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል” ብለዋል። በአካባቢው “አደገኛ ንጥረ ነገሮች ሊፈስ” ይችላል በሚል ስጋት ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲርቁ እየተጠየቁ ይገኛል። የእሥራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማጌን ዴቪድ አዶም እንዳለው ኢራን በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 32 ሰዎች መጎዳታቸውን ገልጿል።
የኢራን የዜና ወኪል ኢርና በሆስፒታሉ አቅራቢያ የሚገኘው የእሥራኤል ወታደራዊ ማዘዣ እና የስለላ ጣቢያ ትናንት ጥዋት የሚሳኤል ጥቃት ዋና ዒላማ ነበር ብሏል። የእሥራኤል ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሆስፒታሉ ላይ የደረሰውን ጥቃት “ሆን ተብሎ የተፈጸመ” እንዲሁም “ወንጀል” ሲሉ አውግዞታል።
ጥቃቱ የተፈጸመው “በጦር ሰፈር ሳይሆን በሆስፒታል” ነው ያሉት ሚኒስትሩ ሻረን ሃስከል፤ ይህ ሆስፒታል ለኔጌቭ ክልል ነዋሪዎች ዋነኛ የሕክምና ማዕከል ነው። ይህን እኩይ ድርጊት “ዓለም ሊያወግዘው ይገባል” ብለዋል።
ኢራን ትናንት በፈጸመቻቸው የሚሳኤል ጥቃቶች የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 89 ከፍ ማለቱን የእሥራኤል የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማጌን ዴቪድ አዶም አስታወቀ። በተጨማሪ በቴልአቪቭ እና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል የተወነጨፉ ሮኬቶች ሦስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን እንዲሁም ሁለቱ ደግሞ በመካከለኛ ሁኔታ ላይ ናቸው ብሏል።
አብዛኛዎቹ የተጎዱት በፍንዳታዎች እንዲሁም በስብርባሪ እና ፍንጣሪዎች መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። የእሥራኤል መገናኛ ብዙኃንም የእሥራኤል መከላከያ አንድ ካምፓስ በስፍራው እየገነባ መሆኑን ከዚህ ቀደም ዘግበው ነበር።
እሥራኤል በምላሹ አገልግሎት በማይሰጠው በአራክ የኒውክሌር ማብላያ እንዲሁም የናታንዝ የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋም ጥቃቶች መፈጸሟ ተገልጿል። የእሥራኤል ጦር በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል አራክ የኒውክሌር ማብላያ እና ናታንዝ የዩራኒየም ማበልፀጊያ ጣቢያዎች ይገኙበታል።
ኢራን ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ቅሬታ አቅርባለች። እሥራኤል በኢራን ላይ የጀመረችው ጥቃት ስድስተኛ ቀኑን ይዟል። ኢራን በአጸፋው ሚሳኤሎችን ወደ እሥራኤል እያስወነጨፈች ትገኛለች።
በስድስቱ ቀናት ግጭት አንኳር ጉዳዮች መካከልም ሐሙስ ለዓርብ አጥቢያ እሥራኤል በኢራን የኒውክሌር ይዞታዎች እንዲሁም የመኖሪያ ስፍራዎች ላይ በፈጸመችው ጥቃት የኢራን የጦር አዛዦች፣ ኒውክሌር ሳይንቲስቶች እንዲሁም ሕጻናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። ኢራን በአጸፋው የእሥራኤልን ወታደራዊ ማዕከላትና የጦር ሰፈሮች ላይ ድሮኖች እንዲሁም ሚሳኤሎችን አስወንጭፋለች።
ቅዳሜ እና እሁድ በሳምንቱ መጨረሻ ሀገራቱ የሚያደርጉት የአየርና የሚሳኤል ጥቃቶች የቀጠለ ሲሆን በዚህም የነዳጅ መሠረተ ልማቶች ተመትተዋል። እሥራኤል በኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት እስከ እሁድ ምሽት ድረስ 224 ሰዎች ሲገደሉ 1 ሺህ 277 መጎዳታቸውን ኢራን አስታውቃለች። እሥራኤል በበኩሏ በጥቃቶቹ 20 ሰዎች ተገድለውብኛል ብላለች።
ሰኞ እሥራኤል የሰሜናዊ ቴህራን ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች። በዚያው ዕለትም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 17 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ቴህራን “ነዋሪዎች በሙሉ ከተማዋን በአስቸኳይ ለቀው መውጣት አለባቸው” ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስጠንቅቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ነዋሪዎች ከቴህራን ለመውጣት ሲሞክሩ በከተማዋ ዙሪያ የትራፊክ መጨናነቅ ታይቷል። ትራምፕ በተጨማሪም የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን “ቀላል ዒላማ ነው። አሁን አንገድለውም” ሲሉ ጽፈዋል ሲሉ ቢቢሲና የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም