የጋብቻ ሥነሥርዓት በአሣግርት ወረዳ

በሰሜን ሸዋ ዞን ከአንድ የሕይወት ምዕራፍ ወደ ሌላ የሕይወት ምዕራፍ የሚያሸጋግረው የጋብቻ ሥነሥርዓት ፈረጀ ብዙ መልክ አለው። ሥርዓተ ሂደቱ እምብዛም ባይሆን ከቦታ ቦታ የሚለያይበት የተወሰነ ባህሪያት እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ። የሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ተዋበች ጌታቸው እንደሚሉት፤ ጋብቻ በኢትዮጵያ በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ ያለና የነበረ የተለየ ባህላዊ ክዋኔ ነው። ሥርዓቱ ግን ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ፦ ሸዋ ዞን ልዩ ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ጋብቻ ሲከወን የተለየ የራሱ መልክ ይኖረዋል። በአሣግርት ወረዳ ያለው የጋብቻ ሥነሥርዓት ደግሞ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው።

በወረዳው ጋብቻ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው በአካባቢው ባህልና ወግ እንዲሁም ሃይማኖትን ተከትሎ ይከወናል። በእዚህ መሠረት ማህበረሰቡ ጋብቻ ከመመስረቱ በፊት አንድ ነገር የማጣራት ግዴታ አለበት። ይሄውም ሁለቱ ጋብቻ ለመመስረት ያሰቡ ጥንዶች እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ በሥጋ ዝምድና ሊኖራቸው አይገባም የሚለው ነው። ምክንያቱም በጋብቻ መሥራቾቹ መካከል የሥጋ ዝምድና አለመኖሩ ቤተሰብ እንዲሰፋ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። እናም ይህ ተግባር ከተከወነ በኋላ ጋብቻው በሁለት መልኩ መደረግ እንደሚችል ይወሰናል።

ኃላፊዋ እንደሚናገሩት፤ በወረዳው ጋብቻ በተለያየ መልኩ የሚፈጸም ሲሆን፤ አንዱ የጋብቻ ዓይነት በተጋቢ ቤተሰቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የሚከናወነው ነው። ጋብቻውን ለመፈጸም ደግሞ በአካባቢው ልማድ መሠረትም የጋብቻ ጥያቄ ይቀርብበታል። ጥያቄው የሚቀርበው በወንዱ ቤተሰብ በኩል ሲሆን፤ ጥያቄውን ከሚያቀርበው ቤተሰብ መካከልም አባት፣ ወይም አጎት፣ አልያም አክስት ተጠቃሽ ናቸው።

ከእዚሁ ጎን ለጎንም ወንዱ ለጋብቻ የሚፈልጋትን ልጅ ማንነት የተመለከተ ማጣራት ያደርጋል። በማጣራቱ ሂደትም ልጅቱ መልካም ጸባይ ያላት መሆኑን ያያል። በመልካም ሥነ-ምግባር ተኮትኩታና ታርማ ስለማደጓም ፍተሻ ይደረጋል። አንዱ ደግሞ መልካም ወላጆች ወገን ያላት የመሆኑ ጉዳይ ነው። የእዚህ የልጅቱ ማንነት ጉዳይ በወጉ ከተጣራ በኋላም ወደ ሽምግልና መረጣ ይኬዳል። ለሽምግልና ሦስት ሰዎች ይመረጣሉ።

የሚመረጡት ሽማግሌዎች ተናግረው ማሳመን የሚችሉ እና በአካባቢው በማህበረሰቡ ዘንድ የሚከበሩና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው መሆን ይኖርባቸዋል። ከእዚያ የተመረጡት ሽማግሌዎች የልጅቱ ወላጆች ቤት ውስጥ ይኖራሉ ተብሎ በሚታሰብበት ቀን ይሄዳሉ። ሽማግሌዎቹ ወደ ልጅቱ ወላጆች ዘንድ የሚሄዱበት ቀን እሁድ ቢሆን የተሻለ ስለመሆኑ ይመከራልም።

ታድያ ሽማግሌዎቹ ከሴቷ ቤተሰቦች ዘንድ እንደደረሱ ከሰላምታ ልውውጥ በኋላ በልጅቱ ወላጆች ወደ እልፍኝ እንዲገቡ ቢጠየቁም በእጄ ብለው አይገቡም። እናትና አባቷን ይዘው ከቤት ውጪ ቁጭ ይላሉ። በመካከሉ ከሦስቱ አንደኛውና የተለየ ክብር የሚሰጠው ሽማግሌ ድንገት ከመቀመጫው በመነሳት “ልጃችሁን ለልጃችን እንድትሰጡን አቶ እገሌ ወይም አያ ማንትስ ሽምግልና ልኮን ነው” በማለት የመጡበትን ጉዳይ ይናገራሉ። ስለሁኔታው በዝርዝርም ያስረዳሉ። ሆኖም የልጅቱ ወላጆች ለሽማግሌዎቹ ወዲያው ምላሽ አይሰጡም። “ከዘመድ መምከር አለብን” በማለት ለምላሹ የቀጠሮ ቀን ቆርጠው መልሰው ወደመጡበት ይሰድዷቸዋል።

በቀጠሮው ቀን ሽማግሌዎቹ በሴቷ ወላጆች ቤት ይገኛሉ። የሴቷ ወላጆች በወንዱ ቤተሰቦች ሃሳብ የማይስማሙ ወይም የማያምኑበት ከሆነ ምክንያታቸውን መናገር አለባቸው። ምላሻቸውንም በዝርዝር ካስረዱ በኋላ ለጋብቻ ልጃቸውን ለመጠየቅ የመጡትን ሽማግሌዎች በጨዋ ደንብ ያሰናብታሉ። ይህ ችግር እንዲከሰት ከሚያደርጉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በወንዱ በኩል ያለው ወገን በሀብት ብቻ ሳይሆን በዘር እነሱ እንደሚሉት የትልቅ ሰው ልጅ ወይም የተከበረ ሳይሆን ሲቀር ነው።

የሴቷ ወገኖች ሽማግሌዎቹ ይዘው የመጡትን የወንዱን ወገን ልጃችሁን ለልጃችን ስጡን ጥያቄ የሚያምኑበት ከሆነ ደግሞ የልጅቱ ወላጆች ጥያቄያቸውን በተቀበሉበት ዕለት በባህሉ መሠረት ቤት ያፈራውን ይጋብዟቸዋል እንጂ በባዶ አይሸኙዋቸውም። የልጅቱ ወላጆች ደህና ሀብት ያላቸው ከሆኑ ደግሞ የኑሮ ደረጃቸውን ለማሳየት ከብት እስከማረድ ድረስ ይደርሳሉ። ይህ ክንውን ደግሞ በእዚያውም መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉበት ተደርጎ ይወሰዳል። ለወደፊቱ አማቻቸው ትልቅ እንደሆኑ የሚነግሩበት ተደርጎም ይታሰባል። ይህ ሁሉ ነገር ካለቀ በኋላና ሽማግሌዎቹ በክብር ከመሸኘታቸው በፊት የሚከናወነው ተግባር የወንዱ እና የሴቷ ቤተሰቦች የሠርጉን ቀን ለመወሰን የሚገናኙበትን ቀን መቁረጥ ነው።

ኃላፊዋ ተዋበች እንደሚናገሩት፤ በአሣግርት ወረዳ አብዛኛውን ጊዜ የሠርግ ሥነሥርዓት የሚከወነው በጥር እና በሚያዝያ ወር ነው። በመሆኑም የልጅቱ እና የልጁ ቤተሰቦች በቀጠሮው ሲገናኙ ሠርጉ በአንዱ ወር እንዲፈጸም ይወስናሉ። ከእዚያም በየፊናቸው ወደ ዝግጅቱ ይገባሉ። ዝግጅቱ አልቆ የሠርጉ እለት ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ቤት ምሽት ላይ ከሦስቱ ሚዜዎችና ከሰባት እስከ 20 ከሚደርሱ አጃቢዎች ጋር በመታጀብ ይሄዳል። የአጃቢዎች ብዛት እንደ ደጋሾች አቅም የሚወሰን ነው።

ከአጃቢዎች ውስጥ የልጁ አባት፣ ሽምግልና ተልከው የነበሩት ሽማግሌዎች ይገኙበታል። የሙሽሪት ጥሎሽም በአንደኛ ሙዜ ተይዞ የሚኬድ ሲሆን፤ ሙሽሪት ቤት ሲደርሱ ውጪ ይቆማሉ እንጂ አይገቡም። ከሙሽሪት ወገን ሽማግሌዎች ተመርጠው ወደ እነሱ በመምጣት የመጡበትን ምክንያት ይጠይቋቸዋል። እነርሱም “ልጅ እንድታደርጉን ነው የመጣነው” በማለት ይመልሳሉ። የያዙትን ዱላ በሙሉ ይቀበሉና “ግቡ” ይሏቸዋል። ከገቡ በኋላም በተዘረጋው ቁርበት ላይ ከሴት ወገን ሁለት ሴቶች ተመርጠው ሙሽራው ለሙሽሪት ያመጣውን ጥሎሽ ሚዜው እንዲያስረክብ ይደረጋል። ለጥሎሽ ከሚቀርበው መካከል ጫማ፣ ነጠላ፣ ቀሚስ፣ የአንገት ብር ከነማተቡ፣ ሻሽ፣ ሱሪ፣ የጆሮ ጌጥ፣ ጃንጥላ፣ ሚዶ፣ መስታወት፣የውስጥ ልብስ፣ ሹራብ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ጥሎሹ ሲጣል ካልጎደለ በቀጥታ ርክክብ ይፈጸማል። ከጎደለ ግን የግድ ማስያዥያ ዋስ ይጠየቃሉ። እናም የጎደለበትን ምክንያት ተናግረው ብር እንዲጥል ከሌለው ሊያሟላ የሚችል ዋስ እንዲጠራ ይደረጋል። አባት “የቁጥር ስጦታ” የሚባለውን ይሰጣሉ። ይህም የወንዱ አባት “እህል፣ በሬ፣ ላም፣ ፍየል፣ በግ ለመተዳደሪያችሁ ቆጥሬያለሁ” በማለት የሚናገረው ነው። የሴት አባት ደግሞ “ላም እና ከተገኘም ፍየል ሰጥቻለሁ” ይላል። ከእዚያ የሁለቱም ስጦታዎች ተጽፈው በውል እንዲቀመጡ ይደረጋል። በእዚህ ውል ላይም ሙሽሮቹ ይፈርሙበታል። ይህ ከተጠናቀቀ በኋላም ሙሽራውን ሚዜዎቹ አጅበውት ቦታ ይሰጣቸውና ይቀመጣሉ። ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ይዘፍናሉም።

ገላዋንና ጸጉሯን ታጥባ የነበረችው ሙሽሪትም ከረጅሙ ሰዓት በኋላ የፈትል ቀሚስ እስከ አላባሹ ለብሳ፣ ሻሽ አስራ ጫማ ታደርጋለች። የለበሰችውን ነጠላ ፊቷ እንዳይታይ ተደርጎ እንድትከናነበውና እንድትቀመጥ ትሆናለች። ከጎኗም ሚዜው መጥቶ ሙሽሪትን ሲወስድ እንዲያሳስቱ ሌሎች እኩዮቿን ሞሽረው ያስቀምጧቸዋል። የእሷን ነጠላ ለአንዷ ያለብሱና የሌላዋን ለእሷ አልብሰው እንድትቀመጥ ያደርጋሉ።

የሙሽራው ሚዜዎች ሙሽሪት ካለችበት ከእዚህ ቤት ገባ ብለው ሻሽ ያስሩላታል፣ የአንገት ቀለበት ያደርጉላታልም። ከእዚያም በተጨማሪ አስፈርመዋት ሽቶ እሷንም ሌሎቹንም ሴቶች ቀብተው ተመልሰው ይወጣሉ። ትንሽ ቆይተውም ሊወስዷት ይመጣሉ። ከቤት ያሉት አናስገባም ሲሏቸው እዛው እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። እየዘፈኑ እየጨፈሩ ይገባሉ ። እቤትም ሲጨፍሩ ቆይተው ስጡን ሲሉ ሽቶ ቀቡንና ይሏቸዋል። ሽቶ ካልቀቧቸውም ሆነ ከቀቧቸውም በኋላ በባህሉ መሠረት እየተረቡአቸው ይዘፍናሉ።

ኧረ ሚዜው ሽቶ አምጣ

ካላመጣህ ና ውጣ፤ ከአሉ በኋላ ሚዜው ሽቶውን ሲያርከፈክፍባቸው ደግሞ መለስ ብለው

“ኧረ ሚዜው ድሃ ነው፣

ሽቶው ውሃ ነው” እያሉ በዜማ ያጥረገርጓቸዋል። ባህሉ ነውና ማንም አይቀየምም። ይልቁንም እየተሳሳቁ ወደ ቀጣዩ ሥራቸው ይገባሉ። ይህም ሚዜው ሙሽሪትን ለይቶ እንዲወስድ የሚፈቀድበት ጊዜ ነው። አሳስቶ ከጎተተ

የሚዜውን ድንግርግር ፣

በለው በድግር።

የሚዜውን ከርፋፋ፣

በለው በአካፋ እያሉ ይዘፍኑበታል። የያዛትን መልሶ ሌላዋን ይጎትታል። ሞክሮ ሞክሮ ከተሳሳተ ከቤት ያሉት ትክክለኛዋን ሙሽራ ይሰጡታል። አጅበውም ወስደው ከሙሽራው ጎን ያስቀምጧታል። ለሙሽሮቹ በአንድ ሳህን ምግቡን አዘጋጅተው በማምጣት ሚዜዎቹ እያጎረሱ ያበሏቸዋል። ሌሎቹም እራት ይበላሉ። ከእራቱ በኋላ የሴት አጃቢዎች የሙሽሪት አባት እየመረጠ ያስመዘግባል። ከሙሽራው ቤት 10 ተከታይ ከመጣ ከሴት ቤት እጥፍ ተደርጎ 20 ተከታይ ይላካል። ለሙሽሪትም አጫዋች(ደንገጡር) ባሏ ደግሞ በአሳዳሪነት ይመረጣል። በመቀጠል ለተከታይነት የተመረጡት ድጋሚ እራት ይበሉና የሙሽሪት እናት አባት፣አያት፣አክስት፣አጎት፣ ታላቅ እህትና ወንድም በቅደም ተከተል ይቀመጡና 1ኛ ሚዜ ይቀድምና የተቀመጡትን ሰዎች ጉልበት ይስማል። በመቀጠል ሙሽራው፣ቀጥሎ ሙሽሪት፣ ቀጥሎ 2ኛ እና 3ኛ ሚዜ ጉልበት ይስሙና ሜዳ ላይ ቁርበት ተነጥፎላቸው ከቁርበቱ ላይ ይቆማሉ። የልጁ ንስሐ አባት ያሳርጉላቸውና እዛው ቁርበቱ ላይ ቁጭ ቁጭ ይሉና ከቤት ያሉት ሽማግሌዎች ይመርቋቸዋል።

ምረቃው እንደተጠናቀቀ አጃቢው ሲጠራ ለስም ማውጫ ተብሎ የተጋገረ ዳቦ በመሶብ ይሸከምና መንገድ ይጀምራሉ። ሚዜው ሙሽራዋን እቅፍ ድግፍ አድርጎ በበቅሎ ወደ ደጋ ከሆነ በፈረስ ያደርግና ይጓዛሉ። ከደከማትም ያዝሏታል። ከወንድ ደጅ ሲደርሱ ከቤት ውጪ ቁርበት ይነጠፍና ሙሽሮችና ሚዜዎች ቁርበት ላይ ይቆማሉ። የምራት ስም ይወጣል። ሙሽራው ዲያቆን ከሆነ መንበርሽ ወርቅ፣ድባብሽ ወርቅ፣ ደብርሽ ወርቅ ተብላ ትሰየማለች። ዲያቆን ካልሆነ ደግሞ ከተማሽ ወርቅ፣ አበባሽ ወርቅ፣ ሙሉ ወርቅ ወዘተ እየተባለች የምትጠራበት ስም ይወጣላታል። ከእዚህ ውስጥ አንድ ስም የሚመረጥ ሲሆን፤ ከቤተሰቡ ውስጥ የሌለ መሆን ይኖርበታል። ምርጫው የሚጸድቀውም በወንድ ቤተሰብ ነው።

ሙሽሪት ከቤቷ ስትነሳ አጫዋች ይመደብላታል። ይህቺ አጫዋች መቀነት ከወገቧ ላይ ውሉ እንዳይገኝ አድርጋ ታስታጥቃታለች። መቀነት ሳይፈታ የሴት ወገን ጠላ ቢሰጣቸውም አይጠጡም። አለመጠጣታቸውን አይተው የወንድ ወገን መቀነት ይፈታላቸው ይሉና ሁለት ሴቶች እጣንና ሰንደል ይዘው ይሄዱና ያጨሱና መቶ ብር ለአጫዋቿ ይሰጣሉ። አነሰ ካለች ይጨምሩና መቀነት ይፈታሉ። መቀነቱ ከተፈታ በኋላ ጠላ ይጠጣል፤እራት ይበላል። ለሙሽሮች የዶሮ ወጥ እንቁላል ይሰጣሉ። ሙዜዎቻቸውና አጫዋቿ እየበሉ ያጎርሷቸዋል። ቀጥሎ እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ሲጫወቱ ያመሹና ሚዜዎቹ እና አጫዋቿ ሙሽሮቹን ያስተኛሉ። ሲነጋ ሙዜዎቹ ተነስተው ይፎክራሉ። ወደ ሴት ቤት ሊሄዱ ይዘጋጃሉ።

ቡና ይፈላና የስም ማውጫው ዳቦ ይቆረሳል። ቡራኬ በመጣበት መሶብ ይደረጋል። ልጅቷ ክብረ ንጽህና ካላት የፍየል ሥጋ የኋላ እግር ድፍኑን ከቡራኬው መሶብ ውስጥ ይደረጋል። ከሌላት ደግሞ ሥጋው በጩቤ ከመካከሉ ሰንጠቅ ይደረግና ይዘው ወደ ሴቷ ቤት ይሄዳሉ። ከደጅ ሲደርሱም ልጅቷ ክብረ ንጽሕና ያላት ከሆነች

ሌሊት እደርሳለሁ ገና በማለዳ፣

ይዠላችኋለሁ የድንግል መርዶ።

ልጅቷ ጨዋ ክብሯን ጠባቂ፣

እናቷ ጨዋ እንዝርት አራቂ፣

አባቷ ጨዋ ቄስ አስታራቂ እያሉ ሚዜዎቹ እየተቀባበሉ ይፎክራሉ። እናቷን አባቷን ከቤት ያሉትን ሰዎች በሙሉ እያሞገሱ የብር ሽልማት ይቀበላሉ። የተሸለሙትንም ገንዘብ ሠርጉ ካለፈ በኋላ የተለያዩ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችን ገዝተው ለሙሽሮቹ ጎጆ መውጫ ይሰጣሉ።

ሚዜዎቹና አጃቢዎቹ ከጨፈሩና መቀበል ያለባቸውን ያህል ብር ከሰበሰቡ በኋላ ቁጭ ብለው ይጋበዛሉ። ተሰናብተው ወደ ወንዱ ቤት ከሄዱ በኋላም እዚያም እንደ ሴቷ ቤት ይጨፍራሉ። ሲያሞግሱ ሲሸልሙ ይውላሉ። ሌሎቹም ሲዘፍኑ ሲጨፍሩ ውለው ያድራሉ። ሚዜዎች ሙሽራዋን እና አማቷን የሠርጉ ማግስት ወደ ማታ ቡና አፍልተው ጎን ለጎን አስቀምጠው ምግብ ያበሏቸዋል። አጫዋቿ እና ሦስቱ ሚዜዎች ሲቀሩ አጃቢዎቹ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።

ሦስተኛው ቀን “የቤት መልስ” በመባል ይታወቃል። መልሱ አጫዋቿ ከነባለቤቷ እና ሚዜዎቹ ሆነው ሙሽሮቹን ይዘው ወደ ሴቷ ቤተሰቦች የሚሄዱበት ልዩ ቀን ነው። ሲገቡ እናት፣አባት፣አያት፣አጎት እና አክስት፣ታላቅ ወንድምና እህት ተሰይመው (ተቀምጠው) ይጠብቋቸዋል። አንደኛ ሚዜ ይቀድምላቸውና ሙሽሮቹ ጉልበት ስመው ይቀመጣሉ። ጠላ ይሰጡና ሲጫወቱ አድረው እስከ ሠርጉ አምስተኛ ቀን ድረስ ከርመው ወደ የቤታቸው ይሄዳሉ። የሠርጉ ሥነሥርዓትም እዚህ ላይ ያበቃል ሲሉ ኃላፊዋ አጫውተውናል። መልካም ሳምንት!

በሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You