‹‹ሴቶች የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርትን አይችሉትም፣ አይወዱትም ፣ወደ ዘርፉም አይገቡም›› እየተባለ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ይህም ሴቶች ልጆች የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርቱ ፍላጎትና ችሎታው ቢኖራቸውም ዘርፉን እየሸሹት እና እየራቁት እንዲሄዱ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል። ይህንን እሳቤ በመሻር የአፍሪካን ሴቶች ‹‹የሂሳብ ንግስት›› ማድረግን ዓላማ አድርጎ የተሰናዳ ጉባኤና የሽልማት ስነስርዓት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሰሞኑን አካሂደዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደው ጉባኤ በተለያዩ ልማዶች፣ ባህል ፣በተሳሳቱ አስተሳሰቦች እና ተግባራት ምክንያት ዘርፉን እየሸሹ እና እየራቁ ያሉትን አፍሪካውያን ሴቶች ከተሳሳተ ሃሳብ አላቅቆ ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ ለማድረግ ታስቦ የተሰናዳ ነበር፡፡ ሴቶች በሂሳብ እና ሳይንስ ትምህርቶች ራሳቸውን አብቅተው አገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ባለሙያዎችና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ይናገራሉ፡፡
አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ የሁለተኛ ዓመት የሂሳብ ተማሪዋ ሆሳዕና መለሰ፤ ወደ ሂሳብ ትምህርት ክፍል የገባችው ሳትፈልገው ነበር፡፡ ትምህርቱን ከጀመረች በኋላ ግን እንደወደደችውና እንደጠበቀችው ከባድ ሆኖ እንዳላገኘችው ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ ቤተሰቦቿና ጓደኞቿ የሂሳብ ትምህርት መማሯ እንደማያስደስታቸው ትገልጻለች፡፡ ይህ አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑንና መቀየር እንዳለበትም ነው የምትናገረው፡፡
በስብሰባው መሳተፏ ልምድ ለመቅሰም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና ሴቶች በሂሳብና ሳይንስ ትምህርት የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚረዳ ትገልፃለች፡፡
ሴቶች የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርት እንደሚከብድ በማሰብ እንደማይመርጡት የምትናገረው ተማሪ ሆሳዕና፤ ዝግጅቱ ይህንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለመለወጥ ጥሩ ዕድል እንዳለው ትናገራለች፡፡ ዘርፉን መርጠን እየተማርነው ላለነው ጠንክረን እንድንማር፣ ሌሎችም ወደ ዘርፉ ተስበው እንዲገቡ በማድረግ በኩል ጥሩ ሚና እንደሚኖረውም ትገልጻለች፡፡ የሂሳብ ትምህርት ከመሰረቱ በአግባቡ እንዲሰጥ፣ ተማሪዎችም ሳይፈሩት እንዲማሩ ፣ መምህራንም ህጻናቱ የሂሳብ ትምህርት እየወደዱት እንዲማሩ በማድረግ
ማሳደግ እንደሚገባ ትመክራለች፡፡
አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ የሁለተኛ ዓመት የሂሳብ ተማሪዋ የኔነሽ መኩሪያው ከመጀመሪያም የሂሳብ ትምህርት ትወድ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ‹‹ሂሳብ ደስ ብሎኝ የምማረው ትምህርት ነው›› ትላለች፡፡
ዘርፉ እንደሚወራው ያክል ከባድ እንዳልሆነና በቀጣይም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመስራትም ፍላጎት እንዳላት ትገልፃለች፡፡ ሴቶች የሂሳብ ትምህርትን በድፍረት መርጠው ሊማሩት እንደሚገባም ነው የምትመክረው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ መምህርቷ ዶክተር ይርጋለም ጸጋዬ፤ ሴቶች የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርት ዘርፍን ትምህርት እንደሚችሉ፣ አፍሪካ ውስጥ ሴት የሂሳብ ባለሙያዎች መኖራቸውን፣ በስፋትና በተደራጀ መልኩ ተረክበው እንደሚሰሩ እና በርካታ የሂሳብና የሳይንስ ሴት ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚቻል ለማሳየት ታቅዶ ጉባኤው መከናወኑን ይናገራሉ፡፡
በአፍሪካ ሴቶች የሂሳብ ማህበር የተዘጋጀው መሆኑን በመጠቆምም፤ ማህበሩ እ.ኤ.አ በ2013 በደቡብ አፍሪካ መቋቋሙንና ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በየአመቱ ሲካሄድ እንደነበረና ዘንድሮ የተካሄደው ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ ስብሰባው ከዝግጅት አንስቶ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ሴቶችን በሂሳብ ትምህርት ዘርፍ አወዳድሮ እውቅና መስጠት አዲስ ሃሳብ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
ሴቶችን በሂሳብና በሳይንስ ትምህርት ለማበረታታት ውድድር ማካሄድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያመለክቱት ዶክተር ይርጋለም፤ ይህንን በስፋት በማከናወን በአፍሪካ ሳይንስና ቴክሎጂ የማይፈሩ ሴቶች ለማፍራት እንደሚያግዝ ይገልፃሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ከየትምህርት ቤቱ በሂሳብ ትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ ነጥብ ካላቸው ከ8ተኛ እና ከ12ኛ ክፍል አምስት አምስት ተማሪዎችን በመምረጥ በሁለት ዙር ፈተና እርስ በእርስ ተወዳድረው ከሁለቱም አንድ አንድ ተማሪዎች ለመጨረሻው ዙር መመረጣቸውን ይናገራሉ፡፡
ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ለሴቶች ጥሩ መሆኑን የሚያነሱት ዶክተር ይርጋለም፤ 50 በመቶ ሚኒስትሮች ሴቶች መሆናቸው፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ የምትገኙት ፕሬዚደንቷ ሴት መሆናቸውን በአብነት በማንሳት፤ በየቤታቸው፣ በገጠር እና በከተሞች የሚገኙ ህፃናት ሴት ልጆች ህልማቸውን ትልቅ በማድረግ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ይገልጻሉ፡፡
ስብሰባ መካሄዱ ብቻውን ሴቶችን በሂሳብና በሳይንስ ትምህርት ለማብቃት በቂ አለመሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ይርጋለም፤ ቡድን ለመፍጠር፣ ለመወያየትና እርስ በእርስ ለመማማር፣ ነጻ የትምህርት ዕድል ለማግኘትም ዕድል ይፈጥርላቸዋል ይላሉ፡፡ ይህም ሴቶች ያለምንም ፍርሃት በሂሳብና በሳይንስ ትምህርት እንዲበረታቱና ስኬታማ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡ ይህንን በማስቀጠል ወደፊት 50 በመቶ ሴት የሂሳብ ባለሙያዎች እንዲሆኑ እና 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ ሳይንቲስት እንዲሆኑ በማድረግ ለችግሮች በጋራ በመሳተፍ በአህጉሪቱ የተሻለ መፍትሄ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ መምህሩ ዶክተር ነጋ አረጋ በበኩላቸው፤ ሴት ተማሪዎችን የሂሳብ ትምህርት ፍላጎት አድሮባቸው እንዲመርጡት በማድረግ አቅማቸውን ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ሂደትም ወጣት ተማሪዎች ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መወዳደራቸውን በመጠቆም በውድድሩ ከፍተኛ ነጥብ ያገኙ እውቅና ይሰጣቸዋል፡፡
በአፍሪካ በሂሳብ ትምህርት ተሳትፎ የሚያደርጉና ሳይንቲስት ሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን የሚገልጹት ዶክተር ነጋ፤ ብዙዎቹም ወደ ዘርፉ ለመግባት ፍላጎት እንደሌላቸው ነው የሚናገሩት፡፡ ዘርፉን የማይመርጡበት ትክክለኛ ምክንያቱ በጥናት መለየት የሚገባው ቢሆንም ‹‹ሂሳብ ትምህርት ይከብዳል›› የሚል ራሳቸው የፈጠሩት የተሳሳተ የአመለካከት ችግር እንደሆነ ይገምታሉ፡፡
ታዋቂ የሂሳብ ባለሙያዎች እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየተሳተፉ የሚገኙ ሴቶች መኖራቸውን ያመለክታሉ፡፡ በየዓመቱ የሚካሄደውና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ በሂሳብ የላቀ እውቀት ያላቸው ሴቶች ተወዳድረው ብልጫ ያገኙት የሚሸለሙበት ስብሰባ ዋና ዓላማ አፍሪካውያን ሴቶች ወደ ሂሳብ ትምህርት ተስበው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ይላሉ ዶክተር ነጋ፡፡
ሴቶች በሂሳብ ዘርፍ የደረሱበትን ደረጃ ገምግመው መስራት የሚችሉትን እና በዘርፉ መስራት ያለባቸውን ነገር በመለየት እቅድ የሚያወጡበት እና ስልት የሚነድፉበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ውድድሩ ሴቶችን ለማበረታታት እንደሚረዳ በመግለጽም በተያዘው ዓመትም ሁለት ሴት ተማሪዎች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ ነጻ የትምህርት ዕድል መሰጠቱን ይናገራሉ፡፡
ከዚህም በላይ መሰራት እንዳለበት የሚናገሩት ዶክተር ነጋ፤ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት ከስር መሰረቱ መሰራት እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡ ስራው መጀመር ያለበት ከቅድመ መደበኛ እና ከመጀመሪያ ደረጃ አንስቶ ነው፡፡ ልጆች የሂሳብ እና የሳይንስ ትምህርት ፍቅር እንዲያድርባቸው በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ በሳይንስና በሂሳብ ትምህርት ብቁና ፍላጎት ያላቸው ሴት ተማሪዎችን በብዛት ማፍራት ይቻላል፡፡
ሴቶችን ለማብቃት ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ግንዛቤ በአንድ ወገን ወይም ለተወሰነ ጊዜ ተተግብሮ የሚተው አይደለም፡፡ በውስን ጊዜ ውጤት ያስገኛል ተብሎ ተስፋ ሊደረግበትም አይቻልም፡፡ ትግበራው ተከታታይነት ያለው የማንቃት እና የማትጋት ስራ ይፈልጋል፤ ይላሉ ዶክተር ነጋ፡፡
ሴቶች በአንድ ሀገር ሁለንታናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት ለመላቀቅ እልህ አስጨራሽ ትግል ለሚያደረጉ ሀገራት የሴቶች ሚና ወደር የለውም፡፡ ሴቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በመደገፍ፣ የራሳቸውን እና የቤተሰባቸውን ህይወት በመለወጥ ረገድ የማይናቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ሴቶችን ማብቃት የሚያስገኘውን ፈረጀ ብዙ ጠቀሜታ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ ለስኬቱም ጅምሩም ፍሬ እንዲያፈራ ከመንግስት ባሻገር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማት እና አጋር አካላት የቅንጅትና የትብብር ሥራዎችን የበለጠ አጠናክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011
ዘላለም ግዛው