“ኢ..ት…ዮ..ጵያ….. የኛ መመኪያ….” የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ዘመን ተሻጋሪና የሀገር ፍቅር በውስጡ ያነገበን ሰው ልብ የሚሰርቅ ዜማ በድምፅ ማጉያው ተከፍቶ በጋራ እያዜሙ በልዩ ድባብ ከወትሮ በተለየ መልኩ ሳይሰስቱ ጉድጓድ ምሰው፤ አፈር ዝቀው ችግኞችን ሲተክሉ ጥበብ ስራ ላይ ሆና ፤ጥበብ ልማት ላይ ሆና በልዩ መልክ የሚታይ ይመስላሉ። ይህ ዕለት ሀምሌ 22 የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፊያ ቀን ነው።
የጠዋቱ ብርድ ክረምትን በአንድነት ቅዝቃዜህን ተሸክመህ ና ብሎ ስብሰባ የጠራ ይመስላል። በካፊያ ታጅቦ አካባቢውን የወረሰው ቅዝቃዜ በበጎ ተግባር ላይ ለመሰማራት ከቆረጠው በሀገር ፍቅር ስሜት ውስጡ ከሞቀው ዜጋ ጋር የመፎካከር አቅም አጥቷል። ዘመቻውን የማስቆም አቅም አልነበረውም። ምክንያቱም ይህ የበጎ ተግባር ጥሪ እስትንፋስ የማስቀጠል ሀገርን ለምለም የማድረግ ተልዕኮ ነው። ይህ በየትኛውም መለኪያ በጎ አሻራን የማኖር ዘመቻ ነው።
ለሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሀምሌ 22 ሰኞ ንጋት 12፡30 ላይ አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ የተሰበሰቡት የሀሌታ አርቲስቶች ጥምረት ማህበር አባላት ጉዞዋቸው ወደ ፅህፈት ቤታቸው መገኛ አካባቢ አብነት ያደረጉት በሀገራዊ ዜማዎች ታጅበው ነው። ለሀገራዊ ጥሪው በተዘጋጁ ጥዑም ሀገራዊ ይዘት ባላቸው ዜማዎች የሀገር ፍቅር ስሜት በሚቀሰቅሱ መፈክሮች ታጅበው ከአብነት እስከ ሜክሲኮ አደባባይ ድረስ በተዘጋጀላቸው የችግኝ መትኪያ ቦታ አሻራቸውን ለማኖር እንቅስቃሴ ጀመሩ።
መኪናው ላይ በሰቀሉት የኢትዮጵያ ባንዲራ መንገዱን የተለየ ድባብ ሰጥተው በእለቱ ያለውን ዘመቻ እያደመቁ ያሰቡበት አብነት አደባባይ የደረሱት የኪነጥበቡ ባለሙያዎች በቦታው ቀድመው የተገኙት የማህበሩ አባላት በጭብጨባና በሆታ እንኳን ለአረንጓዴው አሻራ ማሳረፊያ ቀን አደረሰን በሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ተቀበሏቸው። የችግኝ ተከላው በማህበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት አርቲስት ኢሳያስ መለሰ ማህበሩ የችግኝ መትከል ሥርዓቱ ላይ የተገኙበትን ዋነኛ አላማ በመግለፅና መልዕክት ተጀመረ።
አርቲስቶች በሀገር ልማት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባና እነሱም እንደ ኪነ ጥበብ ባለሙያ ለሀገራዊ በጎ ጥሪው ምላሽ ለመስጠት መሰባሰባቸውን አርቲስት ኢሳያስ ተናግሯል። የኪነ ጥበብ ዘርፈ ብዙነት የኪነ ሁሉ አቀፍነት በማብራራት የማህበሩም ተሳትፎ ለዚሁ መሆኑን አስረድቷል።
በአረንጓዴው አሻራ ማኖር ቀን የራሳቸውን አባላት በማስተባበርና በጎ ተግባሩን በመቀላቀል ታሪክ ለማኖር ክፉ ሃሳቦች በመቅበር በአንፃሩ ደግሞ ችግኞቹ እንዲበቅሉ በመንከባከብ ታሪካዊ ሃላፊነት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ከአብነት እስከ ልደታ አደባባይ ከዚያም ሜክሲኮ ድረስ ያለው የአስፖልት መንገድ አካፋይ በሆነው አረንጓዴ ቦታ ላይ ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ የማህበሩ አባላት በግራና በቀኝ በተዘጋጁ የችግኝ መትኪያ ጉድጓዶች የያዙትን ችግኝ በመትከልና አዳዲስ ጉድጓዶች በመቆፈር ሥርዓት ባለው መንገድ ችግኞችን የተከሉት በደረቁ አልነበረም።
ለዚሁ ዘመቻ ማነቃቂያ በተዘጋጁ ልዩ ልዩ ትርዒቶች በመታጀብ በድምፅ ማጉያ በሚወጣ ሙዚቃ በማዋዛት በጎ ዘመቻና አላማው የተቃና እንዲሆን በኪነ ጥበብ የታገዘ ዘመቻ ሲያደርጉ ውለዋል። በባህላዊ ጭፈራና ወግ ተውበው የችግኝ መትከሉን ስራ በፍቅር እየተጋገዙ ሲተክሉ ላየ አንድም በአረንጓዴው አሻራው አሻራቸውን የማኖር እድል መሳተፋቸው ሲያስቀና በጥበባዊ ዝግጅቶችና ሁነቶች ታጅቦ መካሄዱ ደግሞ ሳይነሽጠው አይቀርም።
ይህ ታሪካዊ ቀን እኔም እንዳያመልጠኝ ብርቱ ምኞት ነበረኝና በተዘጋጁ ሶስት የችግኝ መትኪያ ጉድጓዶች ችግኞችን ከማህበሩ አባላት ጋር ተክዬ እጄን ጠራርጌ መቅረፀ ድምፅ ከኪሴ አወጣሁና አጠገቤ ያለውን ተሳታፊ ማነጋገር ጀመርኩ። በማህበሩ የተዘጋጀ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማ አግድም የተሰራበት ስከርቭ አንገቱ ላይ ጠምጥሞ እጆቹ በችግኝ ተከላው በብርቱ መሳተፋቸውን በሚያሳውቅ መልኩ በጭቃ ተለውሰው ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ሆኖ አጠገቤ ቀረበ።
ማህበሩን ከምስረታ ጀምሮ ተሳታፊ እንደሆነ በመግለፅ የሚጀምረው አርቲስት መኮንን ደባልቄ ሀገርን አረንጓዴ በማልበሱ ዘመቻ መሳተፉ እጅግ እንዳስደሰተውና እንደ ማህበር ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን በልማት ስራው እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል። አረንጓዴ መስክ ለኪነ ጥበቡ ማድመቂያ ወሳኝ መሆኑን የሚናገረው የኪነ ጥበብ ባለሙያው እንደሌላው ማህበረሰብ በዚህ መልክ የልማት ስራ ላይ መሰማራት ተገቢ መሆኑን ያስረዳል።
አርቲስት ሙሉነህ የተሰባሰቡበት ዋነኛ አላማ ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻውን በጎነት ከግብ ለማድረስ መሆኑን ይገልፃል። ለትውልዱ ለምለም የሆነ ሀገር ማውረስና ለህይወት ተስማሚ የሆነ ተፈጥሮን ጠብቆ ማስተላለፍ እንደሚገባም ያምናል። የሰዎች ጤና ማጣት መንስኤ ተፈጥሮ መዛባቱ እንደ ዋነኛ መንስኤ ነው የሚለው አርቲስት ሙሉነህ በዚህ የልማት ስራ መሰማራት ጤናን መፍጠር መሆኑን ይገልፃል።
ስለ ፍቅር ለመዝፈን፣ ስለ ፍቅር ለማውራት የተፈጥሮ ፀጋ ወሳኝ ነው የሚለን አርቲስቱ ማህበረሰባችን በአረንጓዴ ልማት ላይ ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚገባ መሆኑን ያሳያል። ከመትከል ባሻገርም የተተከለውን በመንከባከብ የተፈለገውን ጥቅም ማግኘት እንዲቻል ሁሉም ሊሰራና የተተከሉ ችግኞችን ሊንከባከብ ይገባል።
አርቲስት ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ የችግኝ ተከላውን ለማድረግ ከሌሎች ሀገር ወዳድ አጋሮቹ ጋር በመሆን ለዘመቻው ስምረት ቦታው ላይ ተገኝቷል። አርቲስቱ የኪነ ጥበብ ሙያ ማስዋቢያ ተፈጥሮ መሆኑን ይናገራል። የሙዚቃ፣የፊልምና የሌሎች ኪነ ጥበብ ዘርፎች ክዋኔ ያለ ተፈጥሮ ደብዛዛ መሆኑም ያስረዳል።
የኪነ ጥበብ ስራ ለማሳደግ ተፈጥሮን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን የሚናገረው አርቲስት ታምራት በለምለም መስክ ላይ የሚተገበር የኪነ ጥበብ ስራ ጥራቱም ውበቱም እንደሚጎላ ይጠቅሳል። እንደ ማህበር በዚህ ዘመቻ ላይ መሳተፍ የፈለጉበት ዋነኛ ምክንያትም ማህበራዊ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ለኪነ ጥበቡ ትልቅ ድርሻ ለመወጣት መሆኑን ይናገራል።
የኪነጥበብ ስራ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት በተለየ መልክ የሚገልፀው አርቲስት ኢሳያስ ነው። ኪነ ጥበብ ያለ ተፈጥሮ ጣዕሙን ያጣል። ተፈጥሮ የኪነ ጥበብ ማድመቂያ እንደመሆን ተፈጥሮን መንከባከብና መጠበቅ የኪነ ጥበቡን ስራ ይበልጥ ማሳደግና መንከባከብ መሆኑን ይናገራል። የማህበሩ አባላት ችግኙን ከመትከል ባለፈ በየጊዜው እንክብካቤ በማድረግ እድገታቸውን መከታተል እንደሚያስፈልግም አሳስቧል።
200 በሚደርሱ የማህበሩ አባላት ከጠዋቱ 12፡30 የተጀመረው የችግኝ ተከላና ልዩ የማነቃቂያ መርሀ ግብር የተሰጣቸውን ቦታ በመሸፈን በሀገራዊ ዝማሬና በኪነ ጥበባዊ ኪህን ታጅበው ወደ ፅህፈት ቤታቸው ተመልሰዋል። የማህበሩ አባላት በበጎ ተግባሩ ላይ መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ከገፅታቸው በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ለሙያው ቀጥተኛ ግንኙነት ባለው የልማት ስራ ላይ ተሳታፊ በመሆን ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣና ኪነቱን ለበጎ አላማ ሊያውለው እንደሚገባም የማህበሩ አባላት ገልጸዋል።
የሀሌታ የኪነ ጥበብ ማህበር አባላት በዚህ በጎ ተግባር ላይ መሳተፍ የኪነ ጥበብ በጎ አላማ ማመላከቻ የማህበረሰቡ ተሳተትፎ ማሳያ ነውና መሰል ተግባራት ላይ የመሳተፉ ልምድ ተጠናክሮ ይቀጥል እንላለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2011
ተገኝ ብሩ