
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተደራሽ መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሀይ ወረሰ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በክልሉ ቅድሚያ ከተሰጣቸው የፖሊሲ ሪፎርም አቅጣጫዎች መካከል፤ሕጻናት አንደኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲገቡ ማስቻል ነው።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ ቢሮው ባለው አቅምና መምህራን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹን ደረጃ የማስጠበቅ ሥራ በሂደት እየተሠራ ነው፤ የመማሪያ ክፍል እና የሰለጠኑ መምህራንን በተመለከተም ከ2018 ዓ/ም ጀምሮ በትኩረት የሚሠራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል ፡፡
ሥራው ከጤና ሚኒስቴር፣ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ እንዲሁም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የሚሠራ ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ዛሬ በሕጻናት ላይ የሚዘራው መልካም ዕውቀት ነገ ለምናገኘው የሰለጠነ የሰው ኃይል መሠረት ነው ብለዋል፡፡
ለልጆች የተመቸ የመማሪያ ስፍራ እና የሠለጠነ አስተማሪ እንዲኖር በቅድሚያ በእያንዳንዱ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቦታ በማስተካከል መጠነኛ ግብአት በመጠቀም ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን መጀመሩን አመልክተዋል።
ያሉትን ክፍተቶች ለማስተካከል የመንግሥት በጀት ከመጠበቅ ባለፈ፤ ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት በማሳተፍ ሀብት ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር ደረጃ የልጆችን የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ዕድሜያቸውን በሚመጥን መልኩ እንዲያገኙ ለማስቻል ከክልሎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገው ውይይት እና የሰነድ ስምምነት በርካታ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል፡፡
ማሰባሰብ ሂደት ላይ ኅብረተሰቡን የማነቃቃት ሥራ መጠቀማቸው ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በመግለፅ፤ ባለሀብቶች በግላቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች ማስገንባታቸው በክልላችን ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች በማሳየት በማነቃቃት መሰል ሥራዎች ለመሥራት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ለቅድመ አንደኛ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት እና አስፈላጊውን ግብአት ለማሟላት የሚደረገው ጥረት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤በተለይ በዘመናዊ ሕንጻ የሠለጠኑ መምህራንን በመጠቀም በአዲስ አበባ፣በሶማሌ፣በኦሮሚያ እና በሲዳማ ክልሎች የሠሩት ሞዴል ትምህርት ቤቶች አርአያ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
መጽሐፍ እና ተማሪዎች የመጫወቻ ግብአቶች ለማሟላት ከግብረሰናይ አካላት ጋር መቀናጀት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ፤ክልሉ በቀጣይ ሞዴል ትምህርት ቤቶች በማስገንባት የሠለጠኑ መምህራን በማስፋት የበለጠ ተደራሽ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም