ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደውን የ«አረንጓዴ አሻራ ቀን» ሕዝባዊ ንቅናቄና በአንድ ጀምበር ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል የተጠናቀቀውን መርሀ ግብር ተከትሎ በርካታ ቁም ነገሮች ተዳስሰዋል፤ ተብራርተዋል፤ ተተንትነዋል። ከዚሁ ጋር የተያያዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችም እንደዚያው። እኛም «ያልተዳሰሰ» ያልነውን የደንን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተመለከተ ለመዳሰስ ሞክረናል፤ በዘርፉ ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም «ልዩ» በሚያደርጓት ፀጋዎቿም ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተናል።
ሰነዶች እንደሚያረጋግጡት ልባም አገራት ከደኖቻቸው ሀብትን እየዛቁ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደኖችን በተመለከተ ባካሄደው 10ኛው ፎረም ላይ እንደገለፀው በዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን እስከ 1ነጥብ5 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የገቢ ምንጫቸው የደን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው። እንደ ድርጅቱ ከሆነ፤ ይህ ቁጥር የሚያመለክተው የተጠናከረ የመረጃ ቋት ያላቸውን አገሮች ሲሆን ሁሉም አገራት የመረጃ ቋት ቢኖራቸው ቁጥሩ ከዚህም እንደሚበልጥ ያብራራል።
በዶክተር ቴራንስ ጄ. ሬፋን “The Economic Impact of Virginia’s Agriculture and Forest Industries” (2017) መጽሐፍ ላይ እንደተብራራው ቨርጂኒያ ከደን ኢንዱስትሪዋ ብቻ በየዓመቱ 21.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች። የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን «የደን ኢንዱስትሪው ዘርፍ በድምሩ 9.3 ቢሊዮን ዶላር ለሚከፈላቸው 107ሺህ 900 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ካለው የሥራ ዕድል 8.7 በመቶውን የሚይዘው የደን ልማት ኢንዱስትሪ የአገሪቱን 9.5 ጂ.ዲ.ፒም የሚሸፍነው ይሄው ዘርፍ ነው።
እነ ኢንዶኔዥያን የመሳሰሉ አገራት ወደ ምጣኔ ሀብታቸው በዓመት 21 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀላቀል የሚያደርጉት ከደን ከሚገኝ ገቢያቸው መሆኑ፤ ካናዳ በ2017 ብቻ 24.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢን ከደኗ ማግኘት ችላለች። ወደ ራሳችን ስንመጣ ግን የምናገኘው የተገላቢጦሽ፤ ወይም ዝቅ ብለን የምናገኛቸው የአገራችን ተመራማሪ «ቢሆን ኖሮ» እንዳሉት ነው። ተጨባጩን ሁኔታ ስንፈትሽም ከደን ያገኘነውን ሳይሆን ገና ልናገኝ የምንችለው ነው የሚነገረው።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የ«አረንጓዴ አሻራ ቀን»ን አስመልክተው ስለዛፍ መትከል (ደን ማልማት) ጥቅም በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት ከደን ሀብት የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንድና ሁለት ተብሎ ብቻ የሚተው አይደለም፤ የተሳሰረ ነው። ከብት ማርባት አለ፣ ንብ ማነብ አለ፣ ዛፎችን ለተለያዩ ጥቅሞች ማዋል አለ፤ ለቁሳዊ ምርቶች፣ የሥራ ዕድልና የመሳሰሉት ሁሉ ከደን የሚገኙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ናቸው። ግን አልተሰራባቸውም። «በመሆኑም» ይላሉ ሚኒስትሩ «በዚህ ዘርፍ ሁሉም ሰው ላፍታም ችላ ሊል አይገባም።»
የአካባቢ የአየር ንብረት ለውጥ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም «ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ለየት ያለች ነች» የሚል ለየት ያለ ሃሳብ አላቸው። እሳቸው እንደሚሉት መልከአ-ምድራዊ አቀማመጧ፣ ተስማሚ የአየር ንብረቷ እና አፈሯ ሁሉ ለደን ልማት በጣም ምቹ ናቸው። በመሆኑም ሌላው አገር ዛፍ ተክሎ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማግኘት ከ80 እስከ 120 ዓመታትን ይጠብቃል።
እኛ አገር ግን ከአምስት ዓመት ጀምሮ ጥቅም ማግኘት ይቻላል፤ ተፈጥሮ ምላሿ ፈጣን ነው። ስለዚህ ዛፍ ስንተክል ለትውልድ ብቻ ሳይሆን እኛም ተጠቃሚዎች ነን። ይሁንና ይህን የተፈጥሮ ችሮታ አልተጠቀምንበትም። በመሆኑም እነዚህንና መሰል መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ዛፍ መትከል፣ የዛፎች ክምችት የሆነውን ደን ማልማት ተግባር ላይ ልናተኩርና ተጠቃሚ ልንሆን ይገባል።»
የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪና በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአየር ንብረት ሳይንስ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አደፍርስ ወርቁ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ከሆነ ኢትዮጵያ በደን ሀብቷ ላይ እየሰራችም፤ እየተጠቀመችም አይደለም።
ለምሳሌ የደን ውጤቶችን «ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መላክ ሲገባን እንዳለመታደል ሆኖ ከውጪ እናስመጣለን። ይህ ደግሞ በደን ላይ መዋቅር እንኳን አልነበረንም፤ ዘርፉን ማዕከል ያደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች የሉም። ገና አሁን ነው ደንን አስመልክቶ ተቋም የተፈጠረው። ኢትዮጵያ በምድር ላይ ባለው ብዝሀ-ሕይወት ከዓለም 25ኛ፣ ከአፍሪካ 5ኛ ናት። ይህ ማለት መሬቱ ብዙ ዓይነት ነገር ማብቀል ይችላል ማለት ነው። እንደ ሌላው አገር አንድ ዓይነት ሰብል ወይም የዛፍ ዓይነት ብቻ አይደለም የሚያበቅለው፤ የሰጠኸውን ሁሉ ይቀበላል። አገራችን ተራራማ መሆኗ ሌላው ዕድል ነው። ይህንን በደን ሸፍነነው ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሆንን ነበር።
አንድ ዛፍ እንኳን የሌላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ለእኛ ትልቅ የገበያ ዕድል ይሆኑን ነበር። ነገር ግን ደኑን እንደ ኢኮኖሚ ምንጭ ይዘን እየሰራንበት አይደለም። ቢሆን ኖሮ ኤክስፖርት እያደረግን በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ በሆንን ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛፍ ተክለህ 10 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፕሮሰስ አድርገህ ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ግን ይሄን ሁሉ እጃችን ላይ ያለ ሀብት አውቀን መጠቀም አልቻልንም።
«ኢትዮጵያ ከሰልን በቋሚነት ማልማትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እየቻለች አሰራሩን ካለማወቅ ብቻ ከሰል እያመረትን ያለነው ደን እየጨፈጨፍን ነው። ይህ ስህተት ነው። ለከሰል የሚሆን ደንን በዘላቂነት በማልማት ከሰል ማምረት ይቻላል። አሁን ይህ እየተጀመረ ነው። በአማራ ክልል አዊ ዞን እየተሰራበት ይገኛልና እሱን ተሞክሮ ማስፋት ይገባል።
«ከሥነ-ምህዳራችን ልዩ መሆን አንፃር ዕድለኞች ነን። የአገራችን ሥነ-ምህዳር ትንሽ እንደ ሰራህ ወዲያውኑ መልስ ይሰጥሀል። ይህን ሌሎች አገራት የላቸውም። ችግሩ ባለመስራታችን ነው። በተለይ ተቀናጅቶ፣ ተናቦ፣ በጋራ አቅዶ የመስራት ሁኔታ እኛ ጋር የለም። ይህን ማድረግ ከቻልን በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያችን ያድጋል፤ ተጠቃሚም እንሆናለን።» ነው ያሉን። የአገራችን አጠቃላይ ሁኔታም ከዚህ ውጪ ባለመሆኑ፤ ደን፣ ደን ልማትንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ወደ መዳሰሱ እንመለስ።
የዓለም ሕዝብ ቁጥር (በ2050) በ10 ቢሊዮን እንደሚጨምር በተተነበየበት፤ የሕዝብ የምግብ ፍላጎት አሁን ካለው በ50 በመቶ በሚጨምርበት፤ ከምንመገባቸው ፍራፍሬዎች 50 በመቶዎቹ ከደን የመጡ በመሆናቸው፤ ከውጭ አገር ጎብኚዎች 70 በመቶ የሚሆኑት መዳረሻቸው ደኖች (በተለይም ጥብቅ ደኖች) መሆናቸው፤ በገጠር የሚኖሩ 250 ሚሊዮን ድሆች ለዕለት ጉርስ የሚሆናቸውን የሚያገኙት ከደንና ዛፎች መሆኑ፤ 40 በመቶ የውሃ ምንጭ መገኛዎች ከግማሽ በላይ የደን ሽፋናቸው ወድሞ አደጋ ላይ ባሉበት፤ በዓለማችን ከሚኖረው ሕዝብ 1/3ኛው ወይም 2.4 ቢሊዮን ከዛፍ በሚገኝ ማገዶ የሚገለገል ከመሆኑ አንፃር፤ 40 በመቶ ታዳሽ ኃይል ለዓለም የሚቀርበው ከዛፍ (woodfuel) በሆነበት፤ ረሀብን፣ ድርቅን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ወዘተ ከመቋቋም አኳያ ወሳኙን ሚና የሚጫወቱት ደንና የደን ውጤቶች ከመሆናቸው አኳያ፤ በየዓመቱ ከየፋብሪካና ከተሞች ከሚለቀቀው በካይ ጋስ (carbon dioxide) ሁለት ቢሊዮን ቶን ያህሉን የሚመጠው ደን እንደመሆኑ፤ በዚህ ሰዓት ደንን አለማልማት፣ አለመጠበቅና አለመጠቀም ማለት እብደት ነው የሚሉ ብዙዎች ሲሆኑ የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO)ም ይህንኑ ሃሳብ ይጋራል። (“2018 THE STATE OF THE WORLD’S FORESTS” ይመለከቷል።)
ይህ ብቻ ሳይሆን ፋኦ ሌላም የሚለው አለው። ድርጅቱ እንዳጠናው ዓለማችን በመልከአ-ምድር ጉስቁልናና ደን ውድመት ምክንያት በየዓመቱ 4.5 ትሪሊዮን ዶላር ታጣላች። በነፍስ ወከፍ እያንዳንዱን ሰው 650 ዶላር ያሳጣል ማለት ነው። እንደ ዎርልድ ባንክ ግሩፕ (WBG) ጥናት የደኖች መጨፍጨፍና በረሃማነት መስፋፋት ከ2002 እስከ 2010 ድረስ በየዓመቱ 2.9 ቢሊዮን ቶን ካርቦንዳይ ኦክሳይድ (CO2e) እንዲለቀቅና የአየር ብክለት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ዎርልድ ባንክ ግሩፕ “Forest Action Plan FY16–20” (FAP) በሚለው ሰነዱ (በ2020 የዓለም ደን ሽፋንን ወደ ነበረበት የመመለስ እቅድን የያዘ ነው) እንዳስታወቀው የዓለማችን 1/5 ሕዝብ ህልውናው በደን ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ 22 በመቶ ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች የገቢ ምንጫቸው ከደንና ደን ውጤቶች ነው። በዓለም ካሉ ድሃዎች ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ከከፋ ድህነት የተላቀቁት ከደን በተገኘ ሀብት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 11 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን ናቸው፤ በዓለማችን የሚገኙ 2.4 ቢሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ የተመጣጠነ አመጋገብ ሊኖራቸው የቻለው ከደንና ከደን በሚገኙ ውጤቶች አማካኝነት ነው። (የመድኃኒት ዓይነቶችም ሁነኛው ምንጭ ደን መሆኑ ይታወቃል።)
ዎርልድ ባንክ ግሩፕ “FAO 2014”ን ጠቅሶ እንዳሰፈረው ደን ለዓለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ «ቲምበር» ዛፍ ብቻውን ለዓለም ኢኮኖሚ 600 ቢሊዮን ዶላር በማበርከት ከዓለም ጂዲፒ የአንድ በመቶ ድርሻን ሲይዝ፤ ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ደግሞ የሥራ ዕድልን ፈጥሯል፤ 5ሺህ የእንጨት ምርት ዓይነቶችን በመስጠትም ለኢንዱስትሪው መበልፀግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል።
ከላይ እንደተመለከትነው በዓለም አቀፍ ደረጃ በደን ተሸፍኖ የነበረው መሬት እጅግ እየቀነሰ የመጣና በረሃማነት እየተስፋፋ ይገኛል። ዓለም እስካሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ተጨማሪ ደን ሊያለማ ያወደመውን እንኳን መልሶ መተካት አለመቻሉ የብዙዎች ራስ ምታት ነው።
በአፍሪካ «TerrAfrica» ስር የሚገኘው «SAWAP» ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ አገራት እንቅስቃሴና ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው እነዚህኑ የተራቆቱ ደኖችን ወደ ነበሩበት ለመመለስና ምድርን ለሰው ልጅ ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ ነውና ሁሉም በዚሁ ዓይነት መስመር ሊጓዝ ይገባል፤ ለዚህም የሰኔ 22ቱ የኢትዮጵያ «የአረንጓዴ አሻራ ቀን» እና በአንድ ጀምበር የ353, 633, 660 ችግኝ የመትከል እርምጃ ትክክለኛና ወቅታዊ እርምጃ ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2011
ግርማ መንግሥት