“ባለኝ ልምድና ማስረጃ መሠረት እንድመደብ ለተቋሙ ቢጻፍም ሊፈጽምልኝ አልቻለም”-ቅሬታ አቅራቢው

 “ወደ ተቋማችን ሲመጡ የነበራቸው ደረጃ 13 ሲሆን የተመደቡት በደረጃ 14 ነው”-የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት

አዲስ አበባ፡– በቀድሞው የደቡብ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ውስጥ የሙስናን ድርጊት በማጋለጣቸው በተፈጠረባቸው ጫና ምክንያት ወደ ፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተዛውረው እንዲሠሩ በፍትህ ሚኒስቴር ደብዳቤ ቢላኩም የተመደቡት ከደረጃቸው ዝቅ ተደርገው እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢው አቶ ሕዝቅኤል ማራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በበኩሉ፤ አቶ ሕዝቅኤል ማራ ወደ ተቋማችን ተመድበው ሲመጡ የነበራቸው ደረጃ 13 (XIII) መሆኑን ጠቅሶ፤ አሁን ተመድበው የሚገኙት ግን በደረጃ 14 (XIV) መሆኑን ገልጿል፡፡

ቅሬታ አቅራቢው አቶ ሕዝቅኤል፣ “ከለላ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ስዛወር በሕገ መንግሥቱም ከለላ ተደርጎልኛል፤ በመደቡ ላይ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ ማለትም ደረጃ 17 ላይ ከለላ አለኝ ብዬ ከለላውን ጭምር የዓቃቤ ሕግ ውሳኔንና የፍርድ ቤት ውሳኔን ሁሉንም አያይዤ አስተካክሉልኝ ብዬ ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አቅርቤያለው ብለዋል። ተቋሙ ያቀረብኩትን ለማስተካከል አሉታዊ ምላሽ የሚሰጥ ሳይሆን ቀና አመለካከት ያለው ነው ሲሉ ጠቁመው፤ ነገር ግን ለማስተካከል የተቸገረበት ምክንያት ምን እንደሆነ አልገባኝም ሲሉ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሕዝቅኤል፣ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ላይ ያሉ ኃላፊዎች መልካሙን ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረው፤ ምክንያቱም የዓቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ውሳኔ ማስረጃዎችን አያይዘው ማቅረባቸውን አመልክተዋል።

ሙስናውን በማጋለጣቸውና በመመስከራቸው የተነሳ በደረጃቸው ላይ በቀል መፈጸሙን የሚያሳዩ ነገሮች ስላሉ በቀሉን ለማስወገድ ደረጃቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ለፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ደብዳቤ ተጽፎ የመጣው መረጃ ደረጃ 13 መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሕዝቅኤል፣ አገልግሎቱ ደብዳቤውን መነሻ አደርጎ ደረጃ ቢሰጠኝም፤ የፍርድ ቤት ውሳኔ ስላለ በውሳኔው መሠረት ማስተካከል ሲገባ መስተካከል አልቻለም ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል።

ወደ አገልግሎቱ የተዛወሩት የቀድሞው የፍትህ ሚኒስትር፤ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በጉዳዩ መጉላላታቸውን በማየት የደረሰባቸው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁኔታዎች እስከሚስተካከሉ በሚል ከሃዋሳ ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ ደብዳቤ በመጻፋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በወቅቱ ሲዛወሩም ሚኒስትሩ በወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው እንዲሠሩ የተወሰነ መሆኑን አውቆ የሚቀርብለትን የትምህርት እና ሥራ ልምድ ማስረጃ መሠረት በማድረግ እንዲመደቡ በማሳወቃቸው እንደሆነ አስታውሰው፤ እነርሱ ግን በዚህ መሠረት አልመደቡኝም በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 28 ዓመት የሥራ ልምድ እያላቸውም አሁን እየተከፈለኝ ያለው ግን የጀማሪ ደመወዝ ነው ብለዋል። ቀድሞ የነበሩበት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች መንገዶች ባለስልጣን ቢሮ ሲሠሩት የቆዩት በደረጃ 17 ላይ እንደነበር አስታውሰዋል፤ በፍርድ ቤትም እንደተረጋገጠላቸው ተናግረዋል።

የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በሰነድ በተደገፈ ማስረጃ እንዳብራራው፤ አቶ ሕዝቅኤል፣ የተቋማችን የሕግ ጉዳዮችና የሰነዶች ዝግጅት ባለሙያ ወደ ተቋማችን ተመድበው ሲመጡ የነበራቸው ደረጃ 13 (XIII) መሆኑን አውስቶ፤ 2ኛ አሁን ተመድበው የሚገኙት በደረጃ 14 (XIV) መሆኑ እየገለጽን፤ 3ኛ ተጠቃሹ ተዘዋውረው ሲመጡ ደረጃ 17 ( XVII) ነበርኩ ሶስት ደረጃ ዝቅ ተደርጌ ተቀንሶ ተመድቤያለሁ ብለው ያቀረቡት በተቋማችን በኩል ያልተቀነሰ መሆኑን አስገንዝቧል።

በአስቴር ኤልያስና ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You