
ጋምቤላ፦ በጋምቤላ ክልል የምገባ ፕሮግራም ከተጀመረ በኋላ ትምህርት የሚያቋርጡ የተማሪዎች ቁጥር መቀነሱን እና በትምህርት ውጤት ላይ መሻሻል እየታየ መምጣቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩኜ ኦኬሎ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በክልሉ በ24 ትምህርት ቤቶች ሲሰጥ የነበረውን የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም፤ በ2017 በተደረገው የማኅበረሰብ ንቅናቄ ወደ 52 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማስፋፋት ተችሏል።
ከኢኮኖሚ ችግር ጋር ተያይዞ በክልሉ በርካታ ተማሪዎች ትምህርታቸው ሲያቋርጡ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ በተለይ ሴት ተማሪዎች ትምህርት በማቋረጥ ብልጫ ቁጥር እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በዓመቱ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝና በዚህም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በመጀመሩም ያቋርጡ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እስከመጨረሻው ማጠናቀቅ የቻሉ መሆኑን አስረድተዋል። የምገባ ፕሮግራሙ መጀመር መጠነ ማቋረጥ ብቻ ሳይሆን የተማሪዎች ውጤት ማሻሻል ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልፀዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የማኅበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በክልሉ ከሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ50 በመቶ በላይ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ለመጀመር መታቀዱንም ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙን በመንግሥት አቅም ብቻ ለማዳረስ የማይቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ የማኅበረሰብ እና የግል ድርጅቶች ተሳትፎም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የምገባ ፕሮግራም በትምህርት ቤት መጀመሩ ጠቀሜታው ይህ ነው ተብሎ ከሚገለፀውም በላይ መሆኑን አመልክተው፤ በምግብ ይዘት ውስጥ ምን መሟላት እንደሚገባ ዩኒሴፍን ጨምሮ ተሳትፎ በማድረግ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ምን ምን መሟላት አለበት በሚለው ላይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሙከራ ሥራው ከተሳካ በቀጣይ የምገባ ፕሮግራሙ የሚጀመርባቸው ትምህርት ቤቶች በፓይለቱ ውጤት መሠረት የሚጀመር መሆኑን አመላክተዋል።
ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ማቅረብ ካልተቻለ እንገነባለን ያልነው ሀገር ለመገንባት አዳጋች ነው ያሉት ኃላፊው፤ ሀገሪቷን ማበልፀግ የሚችል ዜጋ ለማፍራት እንደመንግሥት ኃላፊነት በመውሰድ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተለይ ከተማሪዎች ውጤት ማሻሻል ጋር ተያይዞ የክልሉ መንግሥት ኃላፊነት ወሰዶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ያልነበሩ የትምህርት አዋጆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቀው በየደረጃው ያለው ማኅበረሰብ፣ የተማሪ ወላጅ ጭምር ተገንዝቧቸው እየተሠራባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የስድስተኛ ክፍል የሚኒስትሪ ትምህርት በ2017 ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠቱን አስታውሰው፤ ለዚህም በዓመቱ የቅድመ ዝግጅቶች እና የአቅም ማጠናከሪያ (የቱቶሪል) ትምህርቶች ከጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል። በመሆኑም በራሱ የሚተማመን ብቁ ዜጋ በመፍጠር በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኡኩኜ አስረድተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም