
አዲስ አበባ፡- የዓባይ ግድብ ተመሳሳይ ግዙፍ ፕሮጀክት መገንባት የሚያስችል የሰው ኃይልና አቅም መፍጠሩን ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ተናገሩ።
የግድቡ የምሕንድስና ቴክኒክ ኮሚቴ አባል የነበሩት የውሃ መሐንዲሱ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በዓለማችን ውስጥ ካሉት በጣም ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነውና በቴክኒክ ረገድ በጣም ከባድ የሚባል ውስብስብ ሂደት ያሳለፈው የዓባይ ግድብ ተመሳሳይ ግዙፍ ፕሮጀክት ለማጥናት፣ ለመገንባትና ለማስተዳደር የሚያስችል የሰው ኃይል ፈጥሯል።
በግንባታ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አማካሪዎችና ሥራ ተቋራጮች መሳተፋቸውን ጠቁመው፣ በግንባታው ሂደት ከተገኙት ትልቁና አንደኛው ጥቅም ኢትዮጵያውያን መሰል ግድቦችን በራሳችን አቅም መገንባት የምንችልበትን እውቀት፣ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ያካተተ ልምድ ማካበታችን ነው። ይህ ልምድ ተጨማሪ ግድቦችን ከመገንባት ባለፈ ግድቡ በሚገባ እንዲያዝና አገልግሎቱ የሚጠበቀውን ያህል እንዲሆን የሚያግዝ የሰው ኃይል አፍርቷል ብለዋል።
በአፍሪካ ደረጃም ሆነ በመሰል ሀገሮች በዓባይ ግድብ ደረጃ ያለ ፕሮጀክት ተሠርቶ አይታወቅም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ግብፅ ግድቡ እንዲሠራ ብዙ የከሸፉ ሙከራዎችን አድርጋለች። በእኛ በኩል ደግሞ ቁርጠኝነቱ አለ። ይሄን ቁርጠኝነት ደግሞ ከመንግሥት አልፎ ጉዳዩ በሕዝብ እጅ ገብቶ ሕዝቡ የሚችለውን ያህል ተረባርቦ እዚህ ደርሷል። ተሳትፎ አድርገው እዚህ ያደረሱንን ሁሉ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።
እንደ ዓባይ ግድብ ዓይነት ግድብ እስከ ሁለት መቶ ዓመታት ሊደርስ የሚችል የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዳለው አመላክተው፣ ለብዙ ትውልዶች የሚያገለግል ነው። ትላልቅ ግድቦች ሀብታም በሚባሉት ሀገራትም ጭምር የሚሠሩት በብድር ነው። እኛ እንዲህ ያለ የብድር አገልግሎት ለማግኘትም አልቻልንም። ይሄ ሁኔታ ባለበት ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተረባርቦ ግድቡን የገነባው። በእውነት በኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ኮርቻለሁ ብለዋል።
ግብፆች የግድቡን ጉዳይ ወደ ኃያላን ሀገራት እና ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት ሄደው አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በቁርጠኝነት ጉዳዩን ስለያዙት የትም ሊደርሱ አልቻሉም። ውሃው ተይዟል፤ ግድቡም ተጠናቋል። ይህን ማሳካት የቻልነው በጠብመንጃ ኃይል ወይም ሌላ አትንኳቸው የሚል ወገን አግኝተን አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በግድቡ ጉዳይ አንድ ላይ በመቆሙ ነው። አንድ ላይ የቆመ ሕዝብ ይፈራል፤ ይከበራል፣ ግድቡንም ያሳካል ሲሉም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋዊ ወንዞችን በተመለከተ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በዚህ ብቻ የሚቋጭ አይደለም ያሉት የውሃ መሐንዲሱ፤ በሌሎች ተፋሰሶችም በራሱ በዓባይ ወንዝም ገና ወደፊት ልናደርጋቸው የሚገቡን ነገሮች አሉ። እነዚያን ሁሉ እውን ለማድረግ ትልቁ ነገር ሥርዓት ባለው፣ መልክ ባለው መንገድ ተጨባጭ እውነታን የያዘ መልዕክት በመለዋወጥ ዲፕሎማሲያዊ ትግልን ማፋፋም አለብን ብለዋል።
ግድቡ እንዳለቀ ሁሉም አካባቢ የሚፈልገውን የኃይል መጠን በአንድ ጊዜ ማግኘት አይችልም። ግድቡ ብቻ አይደለም የኢነርጂውን አገልግሎት እውን እንዲሆን የሚያደርገው። ከግድቡ የሚገኘው ኃይል መሰራጨትና ወደ ተጠቃሚው መቅረብ መቻል እንዳለበት ጠቁመው፤ ይሄን ለማድረግ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታዎችና በየቦታው የሚያስፈልጉ ጣቢያዎች መደራጀት አለባቸው። በዚህ ረገድ ጠንክረን በመሥራት እስካሁን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ያላገኙ ወገኖች ሁሉ እንዲደርሳቸው ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም መክረዋል።
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ተጠናቆ የፊታችን መስከረም የሚመረቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።
በተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም