
አዲስ አበባ፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለዘንድሮ ዓመት አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ240 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች ለተከላ መዘጋጀታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። 48 ሚሊዮን የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውም ተመላክቷል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ክንፉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የፍራፍሬ እና የደን ችግኞችን ጨምሮ እንደ ክልል ከ240 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
እንደ ክልል ለዘንድሮ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አጠቃላይ ከተዘጋጁ ችግኞች አንድ አራተኛ የሚሆነው የፍራፍሬ ችግኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀሪውን ድርሻ የሚይዙት የተለያዩ የደን ችግኝ ዓይነቶች ናቸው ሲሉ አመላክተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በመርሐ ግብሩ 48 ሚሊዮን የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ የተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ ክልሉ ከፍተኛ የአቮካዶ ምርት የማምረት አቅም ያለው እንደመሆኑ፤ ከተዘጋጀው አጠቃላይ የፍራፍሬ ችግኝ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ የአቮካዶ ችግኝ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ደቡብ ምዕራብ ክልል የስርጭት መጠኑ የሚለያይ ቢሆንም፤ ዓመቱን በሙሉ ዝናብ ያገኛል። ከዚህ አንጻር ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠናቸው ሲታይ የአተካከል ችግር ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ችግኞች የመፅደቅ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። አጠቃላይ በተደረገ ግምገማም የፅድቀት መጠናቸው ከ87 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ በላይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ሲታይም ካሉት አካባቢዎች ድርቅ የማያጠቃው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው፤ የአየር ንብረቱ ጥሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሚተከሉ ችግኞች ጥሩ ውጤት ማሳየታቸውን አስረድተዋል።
የፍራፍሬ ችግኞች የሚተከሉት ለምግብነት እንዲውሉ ታስቦ መሆኑን በመግለጽ፤ በሚተከሉበት ወቅት በዘፈቀድ ሳይሆን የአተካከል ሥርዓትን እና ርቀትን ጠብቀው እንደሆነ ገልጸዋል። በምርታማነት የአርሶ አደሩን ሕይወት በሚለውጥ መልኩ ችግኝ የመትከል ባህል እንደ ሀገር ለማዳበር ሁሉም ሊሳተፍ ይገባል ሲሉ አቶ አሸናፊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም