
ሀገራችን በቀደሙት ዘመናት የነበራትን ከፍታ የሚመጥኑ ሰፊ የባሕር በር እና የተለያዩ ወደቦች ባለቤት እንደነበረች ዓለም የሚያውቀው፤ የታሪክ መዛግብት በደማቅ ቀለም የጻፉት የትናንት የገዘፈ ታሪካች አንድ አካል ነው። የባሕር በር ወደቦች እንደሀገር በዘመኑ ለነበረን ከፍታችን የነበራቸውም አስተዋጽኦ ከቋንቋ በላይ እንደሆነ ይታመናል።
በዘመናት የታሪካችን አካል የሆነው ሰፊ የባሕር በር እና የተለያዩ ወደቦች ባለቤትነት እንደ ሀገር የነበረን ታላቅነት እየተዳከመ ሲሄድ፤ ቀስ በቀስ ከእጃችን እየወጣ አሁን ላይ የባሕር በር የትውልዱ ዋነኛ ጥያቄ ሆኗል። እንደ ሀገርም የህልውና ጉዳይ መሆኑ በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ እና አእምሮ ውስጥ የተጻፈ የሚያቃጭል የስጋት ደውል ከሆነም ውሎ አድሯል።
በቀደሙት ዘመናት የሆነውን እንኳን ትተን ባለፉት አንድ ምዕተ ዓመት በተለያዩ መንገዶች ያጣናቸውን የባሕር በር እና ወደቦች ለማስመለስ እና አጽንቶ ለማቆየት በየዘመኑ የነበሩ መንግሥታት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። በዚህም የትናንት ታሪካችን አካል የሆኑ የባሕር በሮችን ለማስመለስ በተ,ደረገ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጥረት ዳግም የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ባለቤት የሆንበት እውነታ ተፈጥሮም ነበር።
ይህም ሆኖ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እና የእኛ ማደግ የሁል ጊዜ ስጋት የሚሆንባቸው ኃይሎች እና ወቅታዊ የዓለም ፖለቲካ በፈጠሩት ጫና ሀገር ተመልሳ የባሕር በር እና ወደብ አልባ ከሆነች ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ እየተቆጠረ ነው። በእነዚህ ዓመታትም ሀገራችን በለተለያዩ የኢኮኖሚ ጫናዎች እና ስጋቶች ውስጥ ለማለፍ ተገዳለች።
ሕዝባችን እንደሀገር ለአንድ ምዕተ ዓመት የሉዓላዊ ግዛቱ አካል የነበረውን የባሕር በር እና ወደቦች መልሶ በእጁ ለማስገባት ጠንካራ የዲፕሎሚሲ ትግል አድርጓል፣ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶቹን በስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ በእጁ ማስገባት የቻለበትም ታሪክ አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበር የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው።
ከለውጡ በፊት ሀገር ሲያስተዳድር የነበረው መንግሥት በተዛቡ ትርክቶች ፤ የባሕር በርን ከሀገር ህልውና ጋር ያለውን ቁርኝት አሳንሶ በማየት፣ ከሁሉም በላይ ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስጠበቅ ከነበረው ዳተኝነት የተነሳ ሀገሪቱ የባሕር በር አልባ እንድትሆን የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ተንቀሳቅሷል፤ በስልጣን ዘመኑም ጉዳዩ ሀገራዊ አጀንዳ እንዳይሆን በብዙ ተግቷል።
በዚህም ሀገር እንደሀገር ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በብዙ የተፈተነችበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ለወደብ ኪራይ ከፍተኛ ሀብት ከማፍሰስ ባለፈ ቀልጣፋ እና አስተማማን የሆነ የወደብ አገልግሎት ማግኘት የምትችልበት አማራጭ አጥታ ቆይታለች። የባሕር በር ማጣታችን በአስቸጋሪ ወቅቶችም ሉዓላዊነታችንን አደጋ ውስጥ ሊጨምሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችንም ለማስተናገድ ተገድዳለች።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ፤ ግዙፍ ኢኮኖሚ፤ ከባሕር ከ60 ኪሎሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ሆና ለባሕር በር ባይተዋር የሆነችበት አዲስ ዓለምአቀፍ እውነታ ውስጥ ለመኖር ተገድዳለች። በዚህም በአካባቢው ጂኦ ፖለቲካ ውስጥ ሊኖራት የሚገባውን ተጽእኖ መፍጠር ሳትችል ቀርታለች። ብሔራዊ ጥቅሞቿን ሳይቀር በአግባቡ ማስጠበቅ ሳትችል ቀርታለች ፤ ይህም እንደሀገር የህልውና ስጋት ሆኖባታል።
ከአሁናዊ ዓለምአቀፍ እውነታዎች፤ ከተጨባጭ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና ከተጠየቅ አኳያ 130 ሚሊዮን ሕዝብ በተዘጋ ቤት ውስጥ ሆኖ ስለ ነገዎቹ ማሰብ የሚቻል አይደለም። ስለሀገሪቱ ቀርቶ፣ ስለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት፤ ልማት እና ከልማት ስለሚመነጭ እድገት ማሰብ የሚቻል አይደለም።
ይህንን ተጨባጭ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ስጋት ለመቀልበስ እና ለሕዝባችን ሆነ ለቀጣናው ሕዝቦች ብሩህ ነገዎቻቸውን ለማየት እና ተጨባጭ ለማድረግ፤ ሕዝባችን ለሚያነሳው የባሕር በር ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ አግባብ ያለው ምላሽ መስጠት የዓለምአቀፉ ህብረተሰብ ዋነኛ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
በተለይም እንደሀገር የህልውና ጉዳይ አድርገን ላነሳነው የባሕር በር ጥያቄ የጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች እና መንግሥታት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። ጥያቄው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ የመሆኑ እውነታ በራሱ የጥያቄውን ምላሽ ቀላል እንደሚያደርገው ይታመናል።
የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች መካከል ካለው ቤተሰብነት፤ ከዚያም ባለፈ የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች የጋራ እጣ ፈንታ ተጋሪ ከመሆናቸው አንጻር ለጥያቄው ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚከብድ እና ለግጭት የሚያንደረድር አይሆንም!
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም