
ጅግጅጋ፦ በሶማሌ ክልሉ የማኅበራዊ ዋስትና ተደራሽነት ሥራን በሚፈለገው ደረጃ ለማስፋት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ጠየቀ። ጽህፈት ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት በባለፉት አስር ወራት ከጡረታ መዋጮ 444 ሚሊዮን 495 ሺህ 083 ብር መሰብሰቡን አመልክቷል።
በአስተዳደሩ የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀፍቶም መሀሪ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የማኅበራዊ ዋስትና ተደራሽነት ሥራን ለማስፋፋት የባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሠራር እጅጉን ወሳኝ ነው። ይሁንና በዚህ ረገድ በክልሉ ግልፅ ድክመት ይስተዋላል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ የማህበራዊ ዋስትና ተደራሽነት ሥራን ከማስፋፋት አኳያ በሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በኩል፤ የፌዴራል እና የክልል ገቢዎች ቢሮ፣ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆንሥራዎቹን ይሠራል። ነገር ግን በተቋማቱ የሚደረገው ድጋፍ እና እገዛ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፡፡
ጽህፈት ቤት ኃላፊው የገቢዎች ቢሮን ለአብነት በማንሳት እንደገለፁትም፣ በአዋጅ 1268/ 2014 መሠረት የጡረታ መዋጮ የመሰብሰብ ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ገቢዎች ነው። በፌዴራል ደረጃ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ በየክልሉ የሚገኙ ገቢዎች ቢሮ የጡረታ መዋጮውን በመሰብሰብ ወደ አስተዳደሩ ገቢ ያደርጋሉ።
በዚህ መሠረት ጽህፈት ቤቱ ከክልሉ ከገቢዎች ቢሮ አመራሮች ጋር የጡረታ መዋጮ አሰባሰብና ክትትልን በተመለከተ በመመሪያ ቁ6/2016 መሠረት በመፈራረም ወደ ትግበራ ገብቷል። በዚህ አግባብ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በአዋጁ መሠረት የጡረታ መዋጮ ሰብስቦ ለአስተዳደሩ ገቢ የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርበትም ፤ እስከ ወረዳ ድረስ ባለሙያ መድቦ የጡረታ መዋጮ መሰብሰብ ላይ ክፍተት አለበት። ከዚህ አንፃር በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ውስንነት ይታይበታል ብለዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ሙሉ በሙሉ በተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ባይሆንም፤ የማኅበራዊ ዋስትና ተደራሽነት ሥራን ለማስፋፋት የተቀመጠውን እቅድ ለማሳካት እየሠራ መሆኑን ያስገነዘቡት ኃላፊው፤ ‹‹በ2017 በጀት ዓመት አስር ወራት ከጡረታ መዋጮ 374 ሚሊዮን 412 ሺህ 368 ለመሰብሰብ አቅዶ፤ በባለፉት አስር ወራት በተሠራው ሥራ 444 ሚሊዮን 495 ሺህ 083 ብር ተሰብስቧል፤ ይህም አፈጻፀሙ 118 ነጥብ 72 በመቶ ሆኗል›› ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአስር ወር ውስጥ ሁለት ሺህ 256 ሠራተኞችን እና 714 ድርጅቶችን በመመዝገብ መረጃውን ወደ ሲስተም ለማስገባት አቅዶ፤ ሁለት ሺህ 200 ሠራተኞችን እና 744 ድርጅቶች መረጃ ወደ ሲስተም ማስግባቱን ጠቁመዋል፡፡
የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር የሶማሌ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በበጀት ዓመቱ የአስር ወራት አጠቃላይ አፈጻጸም ውጤታማ የሚባል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ ለተቋማት እና ለአሰሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መከናወኑም ለውጤቱ አይነተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።ባለድርሻ ተቋማት በተለይም ገቢዎች በሚፈለገው ደረጃ ኃላፊነታቸውን መወጣት ቢችሉ ከዚህ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደሚቻልም አመልክተዋል።
የማኅበራዊ ዋስትና ተደራሽነት ሥራን ለማስፋፋት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር እና ግንዛቤ ፈጠራ እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያስገነዘቡት ኃላፊው፣ የዘርፉ ተዋናይ ባለድርሻ አካላትም ሀገራዊ ጥቅሙን መሠረት በማድረግ ግዴታና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስምረውበታል፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም