ምንጊዜም ኢትዮጵያውያን ከአቧራ ይልቅ አሻራ ማኖርን ይመርጣሉ። በአረንጓዴ አሻራው ቀንም ከአቧራ ይልቅ አሻራ ማኖርን መርጠዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ልክ ነዎት! ሕዝቡ ከአቧራ ይልቅ ለአሻራ ቦታ የሚሰጥ ሕዝብ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ አስረግጦ አስረድቷል። ይህ በአገራችን ታሪክ ከአንድም እልፍ አንድ ጊዜ የታየ ሀቅ ነው።
ይህንን ሀቅ ያልተረዱና ቢረዱም ወስልተው ያልተረዱ ወይንም በኪሳራ ያበዱ ሕዝቡን ወደወረዱበት ትንንሽ አጀንዳ በመሳብ አቧራ ሊያስነሱ ሲማስኑ ታይተዋል። ሕዝቡ ግን ሁልጊዜም ትልቅ ስዕል ማየት ስለሚችል በየዘመኑ አቧራውን ትቶ አሻራውን በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ እያኖረ እዚህ ደርሷል። ሐምሌ 22 የሆነውም ይኸው ነው። የአያቶቹ እሴት የሆነውን የመሪዎቹን ጥሪ መቀበልና መፈጸም ዛሬም ድረስ አብሮት እንዳለ በተግባር በአንድ ጀንበር አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት፤ «ይህ የተሳትፎ ማዕበል እና የእምቢ ለሀገሬ ሆታ በታሪክ ማህደር ላይ መቼም አይረሳም»። አዎን አይረሳም!
ኢትዮጵያውያን እንደቀደመው ዘመን የአገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ ተቀብለው ወደ ተባሉበት ሳያቅማሙ በነቂስ ወጥተው በመሄድ የተባለውን ማድረግ እንደሚችሉ ዳግም አሳይተዋል። በዚህም ከመንግሥታቸው ጋር በመሆን ሁለት ጊዜ ድል ነስተዋል። አንድም የታቀደውን ችግኝ የመትከል እቅድ ከእቅዱ በላይ በመፈጸም፤ አንድም ደግሞ ይህ አጀንዳ ከታወጀበት ዕለት ጀምሮ «አክቲቪስት ነኝ» የሚል የጥፋት አጀንዳ ወርዋሪ ሁላ በአገራዊ አጀንዳው ተደፍቆና ከስሮ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ድምፁ ኮስምኖ መሰንበቱ ነው።
ሕዝብ የሥራ አጀንዳ ከተሰጠው መከወኑን አሳምሮ እንደሚያውቅበት በተግባር አሳይቷል። ሕዝቡ አገራዊ የልማት አጀንዳ በተነፈገበት አጋጣሚ እነ ጠብ ያለሽ በዳቦዎቹ ሥራ አስመስለው ሴራ እያቀበሉት ሕዝቡን ግራ ሲያጋቡት አይተናል። ባስ ሲልም አንዱን በሌላው ላይ እያስነሱ ሲያጫርሱ ታዝበናል። እስኪሰለቸን ድረስም ሞትና መፈናቀሎችን ቆጥረናል። ከዚህ ሁሉ ጥፋት የሚታደገን ሕዝባዊና አገራዊ የልማት አጀንዳ ሳያሳልሱ ለሕዝብ ማቅረብ ብቻ ነው። የአረንጓዴ አሻራው ቀን ጥሩ ማሳያ ነውና መንግሥት ከዚህ ብዙ ይማር። ወደፊትም ሁለት ጊዜ ድል መንሳት ከተፈለገ ተመሳሳይ አጀንዳዎች ሳይስተጓጎሉ ለሕዝቡ ይቅረቡለት።
ሕዝቡም ትልቅ ነውና ለትልልቅ አጀንዳዎች ብቻ ጆሮውን ይስጥ። «ታላቅ ነበርንና ትልቅ እንሆናለን» ማለት ብቻውን ታላቅ አያደርግም። ይልቁንም የጥፋት ኃይሎችን ጥሪ ትቶ በአገራዊ አጀንዳዎች መጠመድና ከግብ ማድረስ ሲቻልም ጭምር ነው። ስለሆነም ለአቧራ በታኞች ጆሮን ነስቶ ለአሻራ አኗሪዎች ልብን መስጠት ከሁሉም አገር ወዳድ ይጠበቃል።
የዛሬዋ አገር በብዙ መልኩ ትናንት የተሰራችና የተረከብናት ናት። የነገዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ዛሬ የምትሰራና ለቀጣዩ ትውልድ የምትተላለፍ ናት። ይህንን ሀቅ ተረድቶ ዳግም ለእልፍ ድሎች መዘጋጀት ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ከአገራዊ የፖለቲካ ለውጡ ወዲህ የገባንበት ቀውስ ለታሪካችንና ለአገራዊ መልካችን የማይመጥን ስለሆነ በፍጥነት መውጣት ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ለዚህ ትውልድ የሚከብድ አይደለም። የጥፋት መንገድ ሲሄዱበት ቀላል ሲደርሱበት ግን ክሽፈት መሆኑን በውል መረዳት ይገባል። «ካልታዘልኩ አላምንም» እንዳለችው ሙሽራ ጥፋቱ ደርሶ ካላየሁ አላምንም ከሚል አዙሪት መውጣት አለብን። በአንድ አንድ ክልሎች የሚታዩ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ድርጊቶችን መጨረሻ ለመረዳት እያንዳንዳችን መጠሪያ ስማችንን የማወቅ ያህል ቀላል ነው። እውነቱ ይሄ ከሆነ ትጋታችን ለአገራዊ አንድነታችን እንጂ ለውድቀታችን አይሁን። ትናንት የነበረ አገራዊ ማንነት እንጂ አዲስ የመጣ ማንነት የለንም። ስለሆነም ትናንት ተዋደን ሺህ ዓመት የኖርን፤ ጠላትን በጋራ ድባቅ እየመታን አገራዊ አንድነትን እዚህ ያደረስን ሕዝብና አገር ሆነን ሳለን፤ ዛሬ ስለምን አገራዊ አንድነታችንን የሚገዳደር ተግባር እንፈጽማለን፤ ሲፈጸምስ አይተን እንዳላየን እንሆናለን? ሁለቱም አይበጁንምና በጊዜ እንንቃ! መንግሥትም ሕዝቡን በተለይም አፍላ ወጣቶችን ነቅቶ በማሰማራት ከሴራ ይጠብቅ። ዳት ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 27 /2011