‹‹የደስታችን አንዱ በር ሲዘጋ ሌላኛው ይከፈታል። ሁልጊዜም ግን የተዘጋውን እንጂ ለእኛ የተከፈተውን አናይም›› ያለችው መስማትም ሆነ መናገርም ሳትችል ታዋቂ ጸሃፊ እና መምህር የሆነችው ሄለን ኪለር ነች። ይህ አባባል ከአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት እና ልጆቻቸው ታሪክ ጋር ተመሳሰለብኛ ነው ይህን ማለቴ። እናት ልጆቻቸውን ወደ አደባባይ የሚያወጣ አጋዥ ስላልነበራቸው ልጆቹ ምንም እድል እንደሌላቸው አምነው ለረጅም ዓመታት ቤት ውስጥ አስቀምጠዋቸው ነበር። እናም ልጆቻቸው የደስታቸውን በር የሚያሳያቸው ጠፍቶ በጨለማ ውስጥ ከቤት ሳይወጡ ሲኖሩ ቆይተዋል።
ህይወት አንዳንዴ ወልጋዳ እንዳዴ ሰንካላ ትሆናለች። ዋናው ቁም ነገር ግን ከነሰንካላነቷ ተጎዞ ለማሸነፍ መሞከር ነውና። የአርሲዋ እናት እና ልጆችም ችግር ያመጣባቸውን ጣጣ ለማሸነፍ እየታተሩ ይገኛሉ። ቤተሰቡ አሁን በፀበል ቦታ ይገኛል። እናትም ሁለት ልጆቻቸውን አቅፈው ይውላሉ። ቀን እስከስድስት ሰዓት ጸበል አስጠምቀው ምሳ ከቀማመሱ በኋላ ጸሎት ማድረሱንም አይረሱትም። ማታም ከልጆቻቸው ጋር ናቸው ስራቸው ሁሉ እነሱን መንከባከብ ሆኗልና።
ኑሮ በአርሲ
ባለታሪካችን ወይዘሮ ብርቱካን ሞሴ ይባላሉ። በኦሮሚያ ክልል አርሲ ጎሎልቻ ነው ውልደት እና እድገታቸው። ትዳር መስርተው በዚያው አርሲ አንጉሌ ሀራ በተባለ አካባቢ መኖር ጀመሩ። ከባለቤታቸው አራት ወንድ እና ሶስት ሴት ልጆችን ወልደዋል። በአራተኛ እና በአምስተኛ ሴት ልጆቻቸውቸው ላይ በደረሰ ህመም ግን ብዙ ፍዳዎችን እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ። ነገሩ እንዲህ ነው ይስማዓለም እና መሰረት የተባሉ ሴት ልጆቻቸውን አከታትለው ነበር የወለዷቸው። ታዲያ የአንድ ዓመት እና የሁለት ዓመት እምቦቀቅላ ህጻናት እያሉ ሁለቱም ልጆቻቸው በአንድ ቀን ህመም ያገኛቸዋል።
እንደ ትኩሳት አድርጎ የጀመራቸው ህመም ቀን በቀን እየጠናባቸውና ይልቁንም ሁለቱንም አላንቀሳቅስ ብሎ ቀስፎ ያዛቸው። መቆም እና መቀመጥ ያቃታቸው ህጻናት ከለቅሶ በቀር አፍ አውጥተው የሚናገሩበት አንደበታቸው ገና አልጠነከረም ነበርና ስቃያቸውን በጩኸት መግለፁን ቀጥለዋል። የዚህን ጊዜ ወላጆቻቸው የባህል ህክምና አዋቂዎች ዘንድ እያመላለሱ ማሳየቱን ስራየ ብለው ተያያዙት። አንድም የመንደሩ ባህል ሐኪም ግን ልጆቹን ከህመማቸው ሊገላግላቸው አልቻለም። እናም ሴት ልጆቻቸው አካል ጉዳተኛ የመሆን እድላቸው እየሰፋ መጣ።
እናት እና አባት በየጊዜው ወደ ባህላዊ ህክምና ሲወስዷቸው እግራቸውን ከማሻሸት እና በቅርቡ ይሻላቸዋል ከሚል ምክር በቀል ምንም መፍትሔ አላገኙም። እነሱም ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወደዘመናዊ ሐኪም ጋር ወስደው እንዲታከሙ አላደረጉም። ከቀን ቀን ይሻላቸዋል በሚል እሳቤ እቤት እንዲውሉ አደረጉ። መፍትሄ ያላገኘው የህጻናቱ ህመም ግን የልጆቹን እግር አሽመድምዶ አካል ጉዳተኛ አድርጎ ጥላውን አጠላባቸው። በጉልበታቸው ይድሁ የነበሩ ህጻናት እያደጉ ቢመጡም በህመሙ ምክንያት መቆም ሳይችሉ እየዳሁ ቤት ውስጥ መንቀሳቀሱን ቀጥለዋል።
ትምህርት ቤት ገብተው መማር ባለመቻላቸው እና የአካባቢው ማህበረሰብ ለአካል ጉዳተኛ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ በመሆኑ ኑሮአቸው በቤት ውስጥ ብቻ እንዲሆን ተገደዱ። ህይወት ከዚህ በኋላ ለልጆቹም ሆነ ለወላጆች ይበልጥ ፈታኝ ሆና ቀጠለች። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነውና እንዲሉ በዚህ ችግር ውስጥ እያሉ ደግሞ ህጻናቱ ስድስት እና ሰባት ዓመት ሲያልፋቸው የወላጅ አባታቸው ህይወት አለፈ። እናትም ሰባት ልጆችን የማሳደጉ ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ ጫንቃቸው ላይ ወደቀ። በተለይ ሁለቱን አካል ጉዳተኛ ሴቶች ቤት ውስጥ መንከባከብ እና ዘርፈ ብዙውን ኃላፊነት መወጣት አንዳንድ ጊዜም እንቅልፍ የሚያሳጣበት ጊዜ እንደነበር ወይዘሮ ብርቱካን ያስታውሳሉ።
ወይዘሮዋ ለቤተሰቡ ማስተዳደሪያ የሚሆን የቡና እርሻ ነበራቸውና ቀን ከልጆቻቸው ጋር የቡና ዛፍ ያለበት መሬት ላይ ሲያሳልፉ በምርት ወቅት ደግሞ ሰብስበው እና ለገበያ አቅርበው የልጆቻቸውን ብሎም የእራሳቸውን ጉሮሮ ሲያጎርሱ ኖረዋል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የቡና ዛፎቹም እየደረቁ በመምጣታቸው ለቤተሰብ ቀለብ የሚሆነውን ወጪ እንኳን መሸፈን እስኪያቅታቸው ተቸግረው እንደነበር አይዘነጉትም። ከዚህ በዘለለ ግን ከቤት ሳይወጡ የሚውሉ ሁለቱ ልጆቻቸው ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባቸው ነበር። ልጆቹም የጎረቤት ጓደኞቻቸው እና የአካባቢው ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ሲያዩ እኛስ ለምን አንሄድም በሚል መንፈስ ተወጥረው አይናቸው እንባ እያቀረረ ውሏቸውን ከጓዳ ማድረጉን አልቦዘኑም።
ይስማለም እና መሰረት ለትምህርት እና ለስራ ጉዳይ አሊያም ለተለያዩ ክንውኖች የቤተሰቡ አባላት በአብዛኛው ከቤት ሲወጡ ብቻቸውን ይቀራሉ። እናም የምንጊዜም ወጋቸው የሚጀምረው ለትምህርት ያላቸውን ፍላጎት በምን ማሳካት እንደሚችሉ በመነጋገር ነው። ይሁንና በአካባቢያቸው አንድም የእርዳታ ድርጅት ባለመኖሩ እና ዌልቼርም የሚያቀርብላቸው ወገን ባለማግኘታቸው በጉልበታቸው እየተረማመዱ ትምህርት ቤት መሄድ እንደማይችሉ አምነዋል።
ከቤት ወደቤት
እናታቸውም የሚረዷቸው ዘመዶች እና አይዞህ ባይ ሰው በማጣታቸው ልጆቻቸውን በምን አይነት መንገድ ወደ ትምህርት ገበታ ማቅረብ እንዳለባቸው ባለመገንዘባቸው ከቤት መዋላቸውን በተመሳሳይ አምነው ተቀብለዋል። ይሁንና ቤት ሲውሉ እህትና ወንድሞቻቸው ከአስኳላ መልስ የሚጽፉትን እያዩ ስማቸውን መፃፉን ብቻ ተለማምደዋል። በተጨማሪ እናታቸው ምግብ አብስለው እንዲበሉ በሚል ሽንኩርት እና የተለያዩ ግብዓቶችን አቅርበውላቸው አሰራሩን አስተምረዋቸዋል። በመሆኑም ከሱቅ ተሸምቶ የመጣላቸውን ምግብ አብስለው ለቤተሰቡ ማዘጋጀትም ሆነ ለእራሳቸው መመገቡን ልጆቹ አላቃታቸውም።
አንድ ቀን ግን ይስማለም እና መሰረት ቤታቸው ከመጡ ጎረቤታቸው እጅ ላይ ኪሮሽ እና የዳንቴል ክሮችን ይመለከታሉ። ስለሁኔታው ሲያጠያይቁም ለእጅ ስራ የሚሆን የዳንቴል መስሪያ እንደሆነ ይረዳሉ። እናም ይህንን ትኩረታቸውን የተመለከቱት እናታቸው የዳንቴል መስሪያ ክሮችን እና ኪሮሽ ገዝተው አቀረቡላቸው። በዚህ የተደሰቱትና ቤት ውስጥ መዋል የሰለቻቸው ሁለቱ ልጆችም በእራሳቸው መንገድ የዳንቴል አሰራሩን እየሞከሩ ከእናታቸው እና ከእህቶቻቸውም እየተማሩ በመጨረሻ የእጅ ጥበቡን ቻሉበት።
በመጀመሪያ የዳንቴል ስራቸው የአልጋ ልብስ እና የወንበር አልባሳትን አዘጋጅተው ለቤታቸው ማሳመሪያ አደረጉት። ይህች ቀን በህይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት። ምክንያቱም በደረሰባቸው የአካል ጉዳተኝነት ምክንያት ብዙም ከአካባቢው ሰው ጋር የማይቀራረቡት እና ቤት ውስጥ እንዲውሉ የተደረጉ መሆናቸውን አስረስቶ የበለጠ መስራት እንደሚችሉ ያወቁበት ቀን ነውና ደስተኛ ነበሩ።
ከዚህ በኋላ ሁል ጊዜም የሚቀርብላቸውን ግብዓት እየተጠቀሙ ዳንቴል መስራቱን ተያያዙት። በወቅቱ አንዱን ዳንቴል ለመጨረስ ሳምንት የሚፈጽባቸው መሆኑን ያስታውሳሉ። ከምርቶቻቸውም የተወሰነውን በ60 እና 70 ብር ለአካባቢው ነዋሪ እያቀረቡ መጠነኛ ገንዘብ ማግኘት ችለዋል። ይሁንና አሁንም እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በቤት ውስጥ የተገደበ በመሆኑ ተምሮ መለወጥ፤ ከሰው ጋር ተቀላቅሎ አዲስ አየር መቀበል፤ የሚፈልጉት ነገር ግን ያላደረጉት ጉዳይ ሆኖ ሁልጊዜም በአዕምሯቸው የሚመላለስ ጥያቄን ፈጥሮባቸዋል።
ለወይዘሮ ብርቱካን ሁለት ሴት ልጆች አስከፊው ጊዜ በተለይ የክረምት ወቅት መሆኑን ይናገራሉ። ምክንያቱም መፀዳጃ ቤት እንኳን በጉልበታቸው እየተንቀሳቀሱ ለመሄድ ቢፈልጉ ጭቃው እና ዝናቡ እንደሚያበላሻቸው ያውቁታልና ያስፈራቸዋል። ሙሉ አካል ላለው ሰው እንኳን ተጠንቅቆ ቢራመድ የግቢያቸው ጭቃ ሊያበላሸው እንደሚችል የሚያውቁት ሴቶች ለእነርሱ ደግሞ ነገሩ ከባድ ስለሚሆን ችግራቸውን በጉያቸው ደብቀው ለሰዓታት ከቆዩ በኋላ የግድ ሲሆንባቸው ነበር ወደመጸዳጃ የሚሄዱት። ከቀኑ ይልቅ ምሽቱን አብልጠው እንደሚወዱት አይደብቁም። ‹‹ምክንያቱም ቀን ቁጭ ብሎ ሳይንቀሳቀሱ ከመዋል ማታ አንደኛውን መተኛቱ ይሻለን ነበር›› ስትል በሚያሳዝን ድምጽ ይስማለም ትናገራለች።
ይህ የህይወት ዑደት ሲያስጨንቃቸው ታዲያ ሁለቱም ሴቶች መበሳጨት እና መቆጣትን ያዘወትሩ ጀመር። በተለይ እናታቸውን ወደ ውጭ ይዘዋቸው እንዲወጡ እና ታፍነው መቆየት እንደሌለባቸው መወትወት ሲጀምሩ እናትም ስለጉዳዩ የበለጠ ይጨነቁ ገቡ። እናም የአዕምሮ ውጥረት የበዛባቸው ልጆች ድጋሚ መታመም እና መረበሽ ውስጥ ሲገቡ ወደ ጸበል ይዘዋቸው እንዲሄዱ እናታቸውን ጠየቋቸው። እናትም በቤት ውስጥ ለ13 ዓመታት የተቀመጡትን እና ከተማ አይተው የማያውቁ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ የተባለ የጸበል ቦታ ይዘው ለመሄድ ወጠኑ።
ለፀበል ቆይታ
በወቅቱ ታግዛቸው የነበረችው ብቸኛ ሰው ደግሞ የቡና ማሳቸው መድረቅ ሲጀምር አይዞሽ እማዬ ብላ እያገዘች ለመኖር ወስና ለስራ አረብ አገር የሄደችው ሌላኛዋና እና ባለሙሉ አካሏ ሴት ልጃቸውን ነበረች። አረብ አገር ስምንት ዓመታት ሰርታ በየጊዜው እየረዳቻቸው ብትቆይም የሁለት እህቶቿ ስቃይ ግን መፍትሄ እንዲያገኝ ማድረግ ያልቻለችው ልጃቸውም ይህን እድል ስታገኝ አብራ ወደ ፀበል ቦታው አመራች። ወደ ሸንኮራ ሲያመሩ ግን ሁለት ልጆች ይዞ ለመሄድ የተደረገው ጥረት ፈታኝ እንደነበር ሁሉም ቤተሰብ የሚረሳው አይደለም።
አዲስ እይታ፤ አዲስ ባህል እና ለእነሱ አዲስ የሆነውን የውጭውን ዓለም በአይናቸው ሲመለከቱ ከእህቷ ጋር መገረም እንደፈጠረባቸው የምትናገው ወጣት ይስማለም፤ ከአካል ጉዳተኛ እህቷ ጋር በቴሌቪዥንም መስኮት ቢሆን አይተው የማያውቁትን መንገድ እና የሰዎች ትርምስ ሲታዘቡ እንዳሳለፉ ትገልጻለች። አይደረስ የለ ከረጅም ጉዞ በኋላ ፀበል ቦታው ላይ የደረሰው ቤተሰብ ተጨማሪ ፈተናን መጋፈጥ ጀመረ።
ሁለቱም ልጆች መራመድ አይችሉምና በየቀኑ ወደ ጸበል ቤቱ መሄድ ስለማይችሉ ከእናታቸው ጋር በቅርበት ቤት መከራየት ነበረባቸው። በወር 600 ብር የሚከፈልበት ዛኒጋባ ቤት ተከራይተው በየእለቱ እንጀራ እየገዙ የእራሳቸውን ምግብ ማብሰል ደግሞ የግድ ነበር። እናም ከሰው ጋር የመቀላቀሉ እና በቤት ብቻ ተወስኖ የነበረውን አኗኗር የመቀየሩ ተግባር ቢሳካም በየዕለቱ የሚወጣውን ወጪ ግን መቋቋም ቀላል አልነበረም። አሁንም ፀበል ቦታው የሚገኙት እናትና ልጆች እስከአሁን ለሁለት ዓመታታ በፀበል ቦታው ቆይተዋል። ማንያውቃል ተጨማሪ ዓመታትን በዚያው ሊያሳልፉ ይችላሉ።
በቆይታቸው ከአምላክ ፈውስን ከዜጎች ደግም እርዳታን እየጠበቁ ከውርጭ እና ዝናቡ ጋር እየታገሉ ኑሮን መግፋቱን ስራዬ ብለዋል። አረብ አገር የቆየችው እህታቸው ደግሞ በየጊዜው ከአገር ቤት ወደ ፀጸበል ቦታው እየተመላለሰች ብትረዳቸውም በእርሷ አቅም ብቻ የሚሆን ባለመሆኑ ድካሙ በዝቶባታል። አዲስ አበባ ከተለያዩ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ጋር የሚሰሩ ተቋማትን በመጎብኘት በመዘዋወር ለእህቶቿ የሚሆን መቆያ እና እርዳታ እያፈላለገች ቢሆንም እስስከአሁን አልተሳካላትም። ወደ ስልሳዎቹ የዕድሜ ክልል የተጠጉት ወላጅ እናትም እርጅናው እየተጫጫናቸው በመሆኑ የልጆቻቸው ቀጣይ ህይወት ይበልጡኑ እያሳሰባቸው ይገኛል።
አሁን የ16 እና የ17 ዓመት እድሜ ላይ የሚገኙ ሁለቱ ሴት ልጆች ስለአካል ጉዳተኞች ተሞክሮ የሚያዩበት እድል እንኳን አላገኙም። አሁንም በጉልበታቸው እየዳሁ መንቀሳቀሱ ስለሚከብዳቸው በጸበል ቦታው ተኮራምተው ይገኛሉ። በተለያዩ ከተሞች ስራ ፈጥረው ስለሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞች ምንም አይነት ግንዛቤው የላቸውም። ነገን ተምረው የእጅ ጥበብ ሙያዎችን በመቅሰም የእራሳቸውን ህይወት መምራት እንደሚፈልጉ የሚናገሩት ይስማለም እና መሰረት ለጋሽ እጆችን ይፈልጋሉ።
ለዘመናት ከቤት ሳይወጡ ሱቅ እንኳን መሄድ እየናፈቃቸው መውጣት ላልቻሉ ወጣቶች በቁሳቁስም ሆነ በስልጠና ብሎም ተሞክሮ አካፍሎ ድጋፍ በማድረግ ሰብዓዊነትን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል። በተለይም በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን እና ተቋማት የሙያ ስልጠናዎችን ቢሰጧቸውና የቤተሰቡን ህይወት ቢታደጉ ለሀገርም ለወገንም የሚያኮራ እሰየው የሚያስብል ተግባር ይሆናል። ቸር እንሰንብት!!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ጌትነት ተስፋማርያም