
አዲስ አበባ፡– አዋጁ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የድርሻዋን እንድትወጣ የሚያስችል መሆኑን የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 37ኛ መደበኛ ስብሰባው በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ትናንት በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።
የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ረቂቅ አዋጁን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ አዋጁ በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመዋጋት በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት ላይ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ እንድትወጣ የሚያስችል ነው፡፡
ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በርካታ ድንጋጌዎች የነበሩት ቢሆንም፤ ወቅቱን ያገናዘበ እና በሚፈለገው ደረጃ ሥራዎችን በአግባቡ ለመሥራት በሚያስችል መንገድ ያልተደራጀ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
የሕግ ማሻሻያው ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች በአግባቡ ለመተግበር፤ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለተሰጡ ግብረ መልሶች ምላሽ ለመስጠት እና በተግባር ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለመሙላት እንዳስፈለገ አስታውቀዋል፡፡
የተሻሻለው አዋጅ ወንጀሎችን በግልጽ ያስቀመጠ እና ለትርጉም አስቸጋሪ የነበሩትን አንቀጾችን ማስተካከል ያስቻለ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሰብሳቢው፤ አዋጁ ወቅቱን የጠበቀ፤ ጠንካራ ሕግና አሠራር በመዘርጋት የተረጋጋ፤ ግልጽነት ያለው፤ ቀልጣፋ እና ጤናማ የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል ብለዋል፡፡
አዋጁ የፋይናንስ ተቋማት የሆኑት እና ያልሆኑ ተቋማትን ትክክለኛነት እና ተጠቃሚ ባለሀብቶች እነማን እንደሆኑ ለመለየት፤ ወንጀልን መከላከል በሚያስችል መልኩ መረጃዎችን ለመያዝ የሚያስችል አሠራር ያስቀመጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረውን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በመሻር በአዲስ መልክ ለማውጣት ዝግጅት እንደተደረገ የጠቆሙት ሰብሳቢው፤ ነገር ግን ቋሚ ኮሚቴው ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ነባሩን አዋጅ ማሻሻል አስፈላጊ ነው በሚል ውሳኔ ለመድረስ ችሏል፡፡ በዚህም ነባሩ አዋጅ ከነበሩት 58 አንቀጾች ውስጥ 14 አንቀጾች እንዲሻሻሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአዋጁ ሕግ የሚያስከብረው አካል የመግደል ወንጀል እስካልፈጸመ ተጠያቂ አይሆንም፤ አጠራጣሪ የገንዘብ ዝውውር ካለ ለሰባት ቀናት ይታገዳል በሚለው እና አዋጁ ከተሻሻለበት ጊዜ 10 ዓመት ወደኋላ ያገለግላል በሚሉ የድንጋጌ ክፍሎች ላይ ከምክር ቤት አባላት ተቃውሞ የቀረበ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከሀገር ተዘርፎ ወደ ሌሎች ሀገራት የተላከ ገንዘብ ማስመለስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራም ሃሳብ ቀርቧል፡፡
አዋጁን በተመለከተ የተለያዩ የተቃውሞ ሀሳቦች እና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፤ በሦስት ተቃውሞ፤ በአንድ ድምፅ ተዐቅቦ፤ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡ ምክር ቤቱ በዕለቱ የስታርት አፕ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሰው ሀብት ልማት ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
በዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም