አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት አዲሱን የጥሪ ማዕከል ዘመናዊና ቀልጣፋ ማድረጉን ገለጸ።
በኢትዮጵያ ኤሌክተሪክ አገልገሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ ከዚህ በፊት በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል ከተቋሙ የሚገናኙበት በዘመናዊ ደረጃ ባለመዋቀሩና በጣም ውሱን ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ጥሪ ማስተናገድ አይችሉም ነበር። በአዲሱ “905” ነፃ የጥሪ ማዕከል ግን ደንበኞች የሚያቀርቡት ቅሬታዎች፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶች መሰረት በማድረግ ድርጅቱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያስችለዋል።
እንደ አቶ መላኩ ገለፃ፣ አዲሱ የጥሪ ማዕከል ተቋሙ በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተሳሰረ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስቸልና ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚያደርገው ሽግግር ማሳያ ነው። ከዚህ በፊት ኔት ወርኩም ውሱን በመሆኑ ደምበኞች በሚፈሉጉት ልክ የሚስተናገዱበት አልነበረም። ድርጅቱ ግን ባለው ሀብትና አቅም ተጠቅሞ አገልግሎቱን በተለያዩ ከተሞች የማስፋፋት ሥራ እየሠራ ነው።
አዲሱ ”905” ነፃ የጥሪ ማዕከል የተደራጀው በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያስችል ደረጃ ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ምዕራፍ አገልግሎት የሚሰጠው በአዲስ አበባ ለሚገኙ ተጠቃሚዎች እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ምክንያት ደግሞ ማዕከሉ ከኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ሥርዓት አተገባበር ጋር የተገናኘ በመሆኑ የመጀመሪያው ምዕራፍ ትግበራ በአዲስ አበባ ተጀምሯል ብለዋል።
ሲስተሙ በሁሉም ክልሎች በሙሉ አቅም ተግባራዊ ሲደረግ የጥሪ ማዕከሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አክለው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/ 2011
ማእረግ ገ/እግዚአብሔር