አዲስ
አበባ:- የኢትዮጵያ የኑዌር ልማት ማህበር
ከተቋቋመበት አላማ አንፃር ማህበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ መሆኑ ተገለፀ።
የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ቡል ቤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ 3ኛው ዓመታዊ ጉባኤውን ከሐምሌ 25 እስከ 26/ 2011 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት ያካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው ከክልል እስከ ወረዳ የተመለመሉ 500 የማህበሩ አባላት በጋምቤላ ክልል በኮርገን ከተማ ተገኝተው የማህበሩን የሥራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት ገምግመዋል። ማህበሩ የተቋቋመበትን ዓላማ በማሳካት ማህበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል ብለዋል።
እርሳቸውም እንዳብራሩት ማህበሩ የተቋቋመበት አላማ ለኑዌር ብሔረሰብ ጥራት ያለው ትምህርት ለማዳረስ፣ የትምህርት ሽፋን፣ የሴቶችና ልጃገረዶችን የንግድ ተሳትፎ፣ የጤና አጠባበቅ አቅሙን ለማሳደግና ግንዛቤ ለመፍጠር፤ የብሔረሰቡን የግብርና ሥራ እንዲጠናከር ድጋፍ ማድረግ፣ በድርቅ የተጎዱና የተቸገሩትን ለመደገፍ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ሲደርስ ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ማህበሩ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ በሚያደርገው ዓመታዊ ጉባኤውን የማህበሩን የሥራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት የሚገመገም ሲሆን፤ የማህበሩ የሥራ አፈፃፀም እንደሚያሳየው ባለፉት ሁለት ዓመታት በደቡብ ሱዳን የሚገኝ ሙሩሌ በተባለ ብሔረሰብ በደረሰባቸው ጥቃት ለተጎዱ ለመኩይ ወረዳ የኑዊር ማህበረሰብ ነዋሪዎች መቶ ኩንታል በቆሎ እና ባለ 20 ሊትር 20 ጀሪካን ዘይት ድጋፍ አድርጓል።
እንዲሁም አገር አቀፍ የብሔራዊ ፈተና ተፈታኝ ለሆኑ የስምንተኛ፣ የአስርኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በብሔራዊ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ ለ1 ሺ 500 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ሰጥቷል። ለ450 ሴቶችና ልጃገረዶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፤ ለ150 ለሚሆኑ ለብሔረሰቡ ተወላጆች ስለ ኤች አይቪ ኤዲስና አካባቢ ጥበቃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል።
በጎርፍ ለተጎዱ ለለሬ ወረዳ የማህበረሰብ ክፍል 200 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ ተደርጓል። እንዲሁም በዋንትዋ ወረዳ በዘጠኝ አባውራ ቤቶች ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ ቤትና ንብረታቸው ለወደመባቸው የማህበረሰብ ክፍል 50 ኩንታል በቆሎ፣ 10 ጀሪካን ዘይት፣ 1 ኩንታል ጨው፣ 30 የአልጋ አጎበር፣ 30 ብርድ ልብስና የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን ማህበሩ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኑዌር ልማት ማህበር በ10 ሺ የብሔሩ ተወላጅ በሆኑ አባለት በ2004 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን፤ የማህበሩ የቦርድ እና የኦዲት አባላት ምርጫን በማካሄድ ትናንት ሦስተኛ ዓመታዊ ጉባኤውን አጠናቋል።
ሶሎሞን በየነ