
በዓለም እንደ አንድ አማራጭ የኃይል ምንጭ በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል፤ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ኢንዱስትሪዎች እየተጠቀሙበት ዓመታት ተቆጥረዋል። በኢትዮጵያም የድንጋይ ከሰል ከፍተኛ የሙቀት አቅም ያለው ኃይል የሚያመነጭ በመሆኑ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ የሲሚንቶ፣ የብረት፣ የሴራሚክ፣ የጨርቃጨርቅ ፣ የጂፕሰም እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎችም ለኃይል ምንጭነት እየተጠቀሙበት ናቸው።
በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች በተፈጥሮ ይዘቱ ኃይል የማውጣት አቅሙ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳና ተመራጭ እንደሚያደርገው በማንሳት፤ የድንጋይ ከሰል ዘላቂና አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2021 ኢንተርናሽናል ኢነርጂ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የድንጋይ ከሰል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅሙ በዓለም 37 በመቶ ድርሻ ያለው ከፍተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጪ አማራጭ ነው። አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና አውስትራሊያን የመሳሰሉ ሀገራት ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ክምትች አላቸው።
ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ሀብት ያላት ሀገር ናት። ኢትዮጵያም እንዲሁ ከግማሽ ቢሊዮን ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል ክምችት አላት። የሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል ሀብት ክምችቱም በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዳሉ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በሀገር ደረጃ የድንጋይ ከሰል ክምችት ያለው ፍላጎት መጠንም ተለይቷል። በእዚህም ሀገሪቱ ለኢንዱስትሪዎቿ ኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያስፈልጋትና በሀገር ውስጥ ያለው የድንጋይ ከሰል ፍላጎቱም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ይህም ሀገሪቱ ያላት የክምችት መጠን የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚመጣውን ሙሉ ለሙሉ መተካት የሚያስችል መሆኑን የሚያሳይ ነው።
ይሁንና ቀደም ባሉት ጊዜያት ለበርካታ ዓመታት ሀገር ውስጥ ያለው ድንጋይ ከሰል ጥራት የጎደለው፤ የእርጥበት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚፈልጉ ፋብሪካዎች የማይሆን ነው በሚል በማዕድን ሀብቷ መጠቀም ሳትችል ቆይታለች። ኢንዱስትሪዎቹም ከቱርክ፣ ከቻይና፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከመሳሰሉ ሀገራት የሚመረቱ የድንጋይ ከሰል ምርቶችን በውድ ዋጋ እየገዙ መጠቀማቸው ይታወሳል። ለእዚህም በየዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ሲደርግ መቆየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ለእዚህም በምክንያትነት ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች ሀገር ውስጥ የሚመረተው ድንጋይ ከሰል ጥራት የጎደለው ነው። የእርጥበት መጠኑ ከፍተኛ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚፈልጉ ፋብሪካ አይሆንም የሚል ነበር። ይሁንና አሁን ላይ እየወጡ ያሉ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ በሀገር ውስጥ የሚመረተው የድንጋይ ከሰል ከውጭ ከሚገባው ይልቅ ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው።
የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየትም ይህንኑ መረጃ የሚያጠናክር ነው። ነዳጅንም ሆነ የድንጋይ ከሰል ጥቅም ላይ የሚውሉት ለኃይል አገልግሎት ነው። ይህ ሲባል ነዳጅ በፈሳሽ መልኩ ያለ ኃይል ሲሆን፤ የድንጋይ ከሰል ደግሞ በጠጣር መልኩ ያለ ኃይል ነው። በድንጋይ ከሰል ላይ በሀገር ውስጥ ከተሠራ በእርግጠኝነት ከውጭ የሚመጣውን ብዙ ፋብሪካዎች የሚጠቀሙትን ለነዳጅ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል። ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልገውን የሀገሪቷን ነዳጅ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በድንጋይ ከሰል መተካት ይቻላል።
በሀገሪቱ የሚገኙት የድንጋይ ከሰል ባሕርያት ጥልቅ መሆኑን በመጠቆም፤ የካበተ ልምድና እውቀት ባላቸው ባለሙያዎች ጥናት ሊደርግበት እንደሚገባ እየተጠቆመ ይገኛል። በተለይ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት፤ በሀገር ውስጥ ያለው የድንጋይ ከሰል የካሎሪ መጠንና የማቃጠል አቅም የሚፈለገውን ያህል መሆኑን መለየት ተገቢ ነው። ብረትን ማቅለጥ የሚያስችል ከፍተኛ የማቃጠል አቅም ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ይባላል።
ይሁንና በሀገሪቱ ያለው የድንጋይ ከሰል ክምችት በብዛቱ ብቻ ሳይሆን አቀማመጡና ሂደቱ ከሌሎች ሀገራት የተለየ ስለመሆኑ ይነገራል። በተለይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ውፍረቱ በራሱ ተፈጥሮ የሰጠው መልካም የሚባል አቀማመጥ ያለው ነው።
እንዲሁም መረጃዎች እንዳመላከቱት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የድንጋይ ከሰል ዓይነቶች አሉ። በዓይነትም የተለያዩ ሲሆኑ፤ በዋናነት ‹‹ሰብ ቢትመስ›› እና ‹‹ቢትመስ›› የሚባሉ የድንጋይ ከሰል ዓይነቶች በብዛት በሀገር ውስጥ ይገኛሉ። ‹‹ቢትመስ›› የተሰኘው የድንጋይ ከሰል ዓይነት የማቃጠል አቅም አምስት ሺህ ካሎሪ ወይም ከስድስት ሺህ ካሎሪ የማይበልጥ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ከአምስት ሺ ካሎሪ በላይ የማቃጠል ከፍተኛ አቅም ያለውን የድንጋይ ከሰል የሚጠቀም ኢንዱስትሪ የለም።
ከውጭ የሚገባው ‹‹አንትራሳይት›› የሚባለው የድንጋይ ከሰል ዓይነት የማቃጠል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ከሰባት ሺ ካሎሪ በላይ ነው። ይሁን እንጂ ሰባት ሺህና ከእዚያ በላይ ካሎሪ የማቃጠል አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል የሚጠቀም ኢንዱስትሪ በጣም ግዙፍ መሆን አለበት። በእዚህም ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋቀረ ኢንዱስትሪ አለመኖሩ እየተነገረ ነው።
አሁን ላይ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉት የሴራሚክና የሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች ናቸው። እነርሱም ከ5ሺ በላይ ካሎሪ የማቃጠል አቅም ያለው የድንጋይ ከሰል አይፈልጉም። ስለሆነም በሀገር ውስጥ ያለውን የኃይል አቅርቦት ማሟላት የሚችል የድንጋይ ከሰል ማግኘት እንደሚቻል መረጃው ያሳያል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በተለይ የሲሚንቶና ሌሎች ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በኃይል አማራጭነት ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሲመጣላቸው የቆየውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው።
በተሠሩ ሥራዎች የሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ምንጭነት እንደዋና ግብዓት የሚጠቀሙት የድንጋይ ከሰል አሁን ላይ 63 በመቶ በሀገር ውስጥ በማምረት መሸፈን ተችሏል። በእዚህም ምርቱን በሀገር ውስጥ በመተካት ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ወጪን ማዳን የተቻለ መሆኑን ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታሉ።
በድንጋይ ከሰል ምርት ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ የመተካት ሂደት ላይ እየሠሩ ካሉ ተቋማት መካከል፤ የማዕድን ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት አንዱ ነው። ኢንስቲትዩቱ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታቸው ጉልህ የሆኑና ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለመተካት እንዲቻል በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል።
በመሆኑም በ2016 በጀት ዓመት የማዕድን ሚኒስቴር ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል ለመተካት የስትራቴጂክ ሰነድ በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንዲሠራ በማድረጉ ረቂቅ ሰነዱ ተዘጋጅቷል። በእዚህም የድንጋይ ከሰል የአመራረት ሂደትን በማስተካከል እና እሴት በመጨመር እንዲሁም ሌሎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል አቅም እንዳለ አመላክቷል።
ስትራቴጂውን ለማዘጋጀት የድንጋይ ከሰል በሚገኝባቸው ክልሎች (በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡቡ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ) ባለሙያዎች በማሰማራት እያንዳንዱን አካባቢዎች የድንጋይ ከሰል ናሙናዎች በማየት የድንጋይ ከሰል የኮሎሪ ኃይል መጠን ተለክቷል። ከናሙናዎቹ የተገኘው ውጤትም እንደሚያመላክተው፤ በሀገር ውስጥ ከውጭ ከሚገባው በላይ የካሎሪ መጠን ያለው ከፍተኛ ኃይል ያለው የድንጋይ ከሰል መገኘቱን የኢንስቲትዩቱ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በስትራቴጂው የድንጋይ ከሰል የአመራረት ሂደቱን በማስተካከል፤ እሴት በመጨመር እና ሌሎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመፍታት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚመጣውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችል አቅም እንዳለ ተመላክቷል።
ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ በማስቀረት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር፤ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከተሟላ በኋላ በቀሪዎቹ ጊዜያት ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ እንደሚሠራ ተጠቁሟል።
እንደ ሀገር የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስ ጥ ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ ነው። በማህበር ተደራጅተው የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ካሉት ማህበራት በተጨማሪ በከፍተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ኩባንያዎች የድንጋይ ከሰል ወደ ማምረት እየገቡ ናቸው።
ሌሎች ኩባንያዎችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የሚያደርግ ሥራም እየተሠራ ነው። ወደ ሥራ የገቡት የድንጋይ ከሰል እያመረቱ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ የሚመረተውን የድንጋይ ከሰል እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተለይ በሀገር ደረጃ የብረት፣ የወረቀትና የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እና ሌሎች አዳዲስ ፋብሪካዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለባቸው ይናገራሉ። ይህንን ችግር በቀላሉ ለመቅረፍ መጀመሪያ የድንጋይ ከሰል ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘዴዎችን መቀየስ ያስፈልጋል። ለእዚህም አንዳንድ ፋብሪካዎች ቴክኖሎጂዎቻቸውን በመቀየር አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮች መጠቀም ይጠበቅባቸዋል።
በሌላ በኩል በድንጋይ ከሰል ላይ የሚነሱ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት፤ በከፍተኛ ደረጃ የድንጋይ ከሰል የሚያጥቡ ፋብሪካዎች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል። እነዚህ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል ላይ የሚነሱ የጥራት መጓደል ችግሮች በመቅረፍ የታጠበና ጥራቱን የጠበቀ የድንጋይ ከሰል ሲሚንቶ፣ ለብረት፣ ለወረቀት፣ ለሴራሚክ፣ ለጂፕሰም እና ለሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓትነት እያቀረቡ ይገኛል።
በስትራቴጂው እንደተመላክተው፤ ከድንጋይ ከሰል ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር በመቅረፍ በአምስት ዓመት ውስጥ ከውጭ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል ለማስቀረት እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። ስትራቴጂው መልካም መሆኑን ተከትሎ መሬት ወርዶ ውጤት እንዲያመጣ እየተጠየቀ ይገኛል። ይህ የተባለበት አንደኛው ምክንያት ሀገሪቱ በርካታ የድንጋይ ከሰል ክምችት እያላት ከውጭ በከፍተኛ ዶላር ማስመጣት የለባትም። ማዕድኑን በማምረት የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ይቻላል በሚል መነሻ ነው።
የድንጋይ ከሰል አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት ይቻላል የሚለው ደግሞ ሌላኛው መነሻ ነው። በስትራቴጂው የድንጋይ ከሰልን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ከመተካት እና የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት በተጨማሪ በቀጣይ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት ይቻላል በሚል መነሻም እየተገለጸ ይገኛል።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያመላክቱት፤ በሀገሪቱ የድንጋይ ከሰል የማውጣት ሂደት ላይ ከፍተኛ የእውቀት ክፍተት አለ። መንግሥት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የእውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት እና ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር ማስተካከል ጥረት ማድረግ አለበት። ይህ ካልሆነ የምርት ብክነት ይከሰታል።
ትርፋማና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አይቻልም። አቅራቢዎች እንዲዳከሙ ያደርጋል። በተጨማሪ ወደፊት ዘርፉን ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ከባድ ያደርገዋል። ስለዚህ የድንጋይ ከሰል ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ማዕድኑ የማውጣት ሂደት እና የመሳሰሉት እያንዳንዳቸውን እንቅስቃሴዎች በእውቀት መምራት መቻል ያስፈ ልጋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች፤ ለእዚህም እንደ ሀገር የድንጋይ ከሰል ዘርፍ ልማት ከባህላዊ አሠራር ወጥቶ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የማዕድን ልማት ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ። ይህንን በመቀየር ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራ በድንጋይ ከሰል በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትልቅ እምርታ ማምጣት እንደሚቻል አመላክተዋል።
በወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም