የከበሩ ማዕድናትን እሴት ለመጨመር የሚያስችል የአቅም ግንባታ

ኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን በማዕድን ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል። ከዚህም ባሻገር ያለውን ልምድና ተሞክሮ ተጠቅሞ ከልማቱ ጎን ለጎን በማዕድናት ዙሪያ ግንዛቤን ለማስፋት ያለመ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በተለይ መልኩ በአጠቃላይ የከበሩ ማዕድናት ዙሪያ ስልጠናዎች እየሰጠ ሲሆን፤ እስካሁን በሦስት ዙሮች ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው ስማቸው እንደሚሉት፤ የከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ከሌሎች ማዕድናት መካከል ዋነኛው ነው፡ ፡ ኮርፖሬሽኑም ዘርፉን ማሳደግ ዓላማ አድርጎ ብዙ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። በዋናነት በዘርፉ ለተሰማሩም ሆኑ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አቅም መገንባት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን ይሰጣል።

ሥልጠናው በ2016 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ ዘርፉ ለሕገወጥ ንግድና ለመሳሳሉ ችግሮች እንዳይጋለጥ ግንዛቤን ከመፍጠር ባለፈ ሀገሪቱ ከዘርፋ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ታስቦ የተጀመረ መሆኑን ይገልጻሉ። በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በሚያደርገው ጥረት የሥራ እድል እንዲፈጠርና ዘርፉ እንዲያድግ ያለመ መሆኑን ይናገራሉ።

በሥልጠናው አጠቃላይ የከበሩ ማዕድናትን በተመለከተ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርቶች የተካተቱበት ነው የሚሉት አቶ ይግዛው፤ በከፊል የከበሩና የከበሩ ማዕድናት በቀለም አሊያም በቅርጽ እንዴት መለየት ይቻላል? የሚለውን ለማወቅ የሚያስችለውን ሳይንስ እንዲያውቁት እንደሚያግዝ ይገልጻሉ።

ሥልጠናው ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የከበሩ ማዕድናት አንዱ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ሰዎች እውቀቱ ኖራቸው እንዲሠሩ በማሰብ መሆኑን አመልክተዋል። ለሌሎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል ። ይህም ዘርፉ አድጎ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያስገኛል። የሥራ እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም በዘርፉ የተሰማሩም ሆኑ ሊሰማሩ የሚፈልጉ አቅም መገንባት ይገባል ሲሉ አስገንዘበዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳብራሩት፤ ስልጠናው የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል። አሁን ላይ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ተጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ መላክ እየተሠራበት ይገኛል። የበለጠ ለማሳደግ ደግሞ ዘርፉን በደንብ ማየት አስፈላጊ ነው። ስልጠናም ለውጭ ገበያ የሚላኩ ምርቶችን ያሳድጋል። በሌላ በኩል ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ገቢ እንድታገኝ ያስችላል።

ሥልጠናው ለ15 ቀናት የሚሰጥ ቢሆንም አጠቃላይ የከበሩ ማዕድናት አስመልክቶ ሰልጣኞች ማወቅ ያለባቸው ነገሮች እንዲያውቁ ያግዛል የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ሥልጠናው የተሰጠባቸው ቀናት በቂ ባይሆኑም በመጠኑም ቢሆን ዘርፉን ለማወቅና ለመለየት እንደሚያስችል ይናገራሉ። ዘርፉ ሰፊ ስለሆነ ከዚህ በላይ ጊዜ ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በቀጣይ የሥልጠናውን ጊዜም ሆነ ይዘት ለማስፋት እንዲቻል የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸው አመላክተዋል።

ሥልጠናው እስከ አሁን በሦስት ዙር ለ59 ሰልጠኞች የተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ መካከል ሥልጠናው ከፍለው መውሰድ ለማይችሉት ኮርፖሬሽኑ በነጻ እንዲማሩ ድጋፍ ያደረገ መሆኑን ያመላክታሉ።

ሥልጠናውን የወሰዱ በዘርፉ ተሰማርተው የግል ሥራቸውን በመሥራት ለሌሎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ገልጸው፤ በቀጣይ ኮርፖሬሽኑ በሚሠራቸው ሥራዎች በተለያየ መንገድ በመሳተፍ አብረው መሥራት የሚችሉበት አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ተናግረዋል።

ሥልጠናው ከተጀመረ አጭር ጊዜ ቢሆነውም፤ በዘርፉ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ምን ይመስላል የሚለው ማመልከት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ይግዛው፤ በቀጣይ የሰልጣኞችም ሆነ በዘርፉ ከተሠማሩ እየሠሩ ካሉት አካላት ግብረመልስ በማሰብሰብ ያንን መሠረት አድርጎ የሚሰጠውን ስልጠና በማሳደግ የተሻለ ሥልጠና ለመስጠት ይሠራል ብለዋል።

አሁን ላይ እየተሰጠ ያለው ስልጠና የአጭር ጊዜ ስልጠና መሆኑን በማስታወስ፤ ሰልጣኞች የሚሰጡት አስተያየት በመቀበል መሻሻል ያለባቸው ነገሮች በማሻሻል የስልጠናው ጊዜ በመጨመር ወደ ፊት ሰፊ ጊዜ ተመድቦለት፤ የተጠናከረ ወርክሾፕና ቤተሙከራ /ላብራቶሪ/ ኖሮት በኢንስቲትዩት ደረጃ በስፋት እንዲሰጥ ታቅዷል። ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን በስፋት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ ጅምር ሥራዎች ያሉት ሲሆን፤ ይህንን በማጠናከር የስልጠና ማዕከል አንድ ዘርፍ አድርጎ ኢንዱስትሪውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ይሰራል ። ከዘርፉ የሚገባው ጠቀሜታ ለማግኘት ወርክሾፖችን፣ ቤተሙከራዎችን /ላብራቶሪዎች/ ማዕከላት ማዘጋጀትና ማጠናከር በተሻለ ሁኔታ ስልጠናው መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ስልጠናውን ተመጣጣኝ በሆነ ክፍያ እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ፤ ለሚሰሩም ሆነ ለሰለጠኑ አልያም ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሟልተው በተመጣጣኝ ክፍያ ስልጠናውን ሊወስዱ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ በተያዘው ወር በሦስተኛ ዙር ዘጠኝ ሰልጣኞች ማሰልጠኑም ተገልጧል። ከእነዚህ ሰልጣኞች መካከል አንዱ አቶ አሰፋ ገነቱ ናቸው። በሙያቸው አስጎብኚ ሲሆኑ፤ ከባለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ በአስጎብኚነት እየሠሩ ይገኛሉ። አሁኑ ደግሞ አጠቃላይ የከበሩ ማዕድናትን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ የሚሰጠውን የአጭር ጊዜ ስልጠና ወስደዋል።

አቶ አሰፋ ምንም እንኳን እየሰሩበት ያለ ሞያና የወሰዱበት ስልጠና ባይገናኝም የከበሩት ማዕድናት ለማወቅና ለመለየት ትልቅ ውስጣዊ ፍላጎት ስላደረባቸው ሰልጠናውን መወሰዳቸው ይናገራሉ።

በአስጎብኚነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በሚጎዙበት ወቅት የከበሩ ማዕድናት ጋር የመገናኘትና የመተዋወቅ አጋጣሚ እንደነበራቸው አቶ አሰፋ ያስታወሳሉ። በተለይ ሀገሪቷ ለመጎብኘት ከውጭ ሀገር የሚመጡ ጎብኚዎች ለከበሩ ማዕድናት ያላቸው ውስጣዊ ፍላጎትና አመለካከት ከፍተኛ መሆኑ ገልጸው፤ ይህም እሳቸውም ስለ ማዕድናቱ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲሰፋና የበለጠ እንዲያወቁ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ።

ሀገሪቱ ያላትን የከበሩ ማዕድናት ሀብት አውቆና ለይቶ ለሌሎች ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑ ስለገባቸው ይህንን እውቀት የሚያገኙበት ስልጠና መወሰድ ችለዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የከበሩ ማዕድናት ከሌላ ሀገር ሰዎች ሰምተው ከመረዳት ይልቅ፤ በራስ እውቀት ከማስተዋወቅ ባሻገር፤ ራሳቸውንም ሆነ ሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመስራት ማሰባቸውን ተናግረዋል። ለዚህም ማዕድናቱ በደንብ ለማወቅ የሚያስችል ስልጠና ለመውሰድ ብዙ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው ያሰቡትን ማሳካት መቻላቸውን አንስተዋል።

ስለከበሩ ማዕድናት ለአስራ አምስት ቀናት የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና መውሰዳቸው ተናግረዋል። ስልጠናው ዓለም ላይ ያሉ የከበሩ ማዕድናት ባህርያትና ማዕድናቱን በማስዋብ እሴት መጨመር ስለሚቻልባቸው መንገዶች እና ለጌጣጌጥ እንዲውሉ በማድረግ ዙሪያ እውቀት የሚያስጨብጥ ግንዛቤ ያገኙበት እንደሆነ ይገልጻሉ። ስልጠናው በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ በመሰማራት የከበሩ ማዕድናት በመለየት ማወቅና እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማዋል የሚያስችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ ስልጠናውን ከመጀመሬ በፊት በውስጤ ስለማዕድናቱ የማወቅ ፍላጎት ብቻ ነበረኝ ›› የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ፍላጎት ወደ እውቀት የሚወስድ መንገድ እንጂ በራሱ እውቀት ስላልሆነ ስልጠናው ስለከበሩ ማዕድናት ግንዛቤ እንዲኖራቸውና እንዲረዱት እንዳስቻላቸው አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም የከበሩ ማዕድናት በብዛት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በተለይ በኦፓል ከአውስትራሊያ ቀጥላ የምትታወቅ ሀገር ናት የሚሉት አቶ አሰፋ፤ እነዚህ ማዕድናት ለዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር እሴት በመጨመር የገቢ ምንጭ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

ማዕድናቱ ተፈላጊ ከመሆናቸው የተነሳ በዓለም ገበያ ከፍተኛ ፍላጎት ያለ መሆኑ ቢታወቅም፤ ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በሂደት በማጥናት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ይገልጻሉ። በቀጣይ ስለማዕድናቱ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸውን በመቀጠል፤ ዘርፉን በመቀላቀል ማዕድናቱ ላይ እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ እንዳላቸው አመላክተዋል።

ስለከበሩ ማዕድናት በደንብ ማወቅና መለየት የሚያስችል ስልጠናዎች መሰጠቱ በእጅጉ አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ አሰፋ፤ ይህም በሙያው ያሉ ዜጎች እንዲበረቱና ሥራው እንዲጠናከር ያደርጋል። በተጨማሪ ገበያው ላይ ሕግና ሥርዓት እንዲኖር ያግዛል። በተጨማሪም ሀገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላል። በተለይ ጂኦሎጂና ጂሞሎጂ ትምህርቶች በሥርዓት ትምህርት ውስጥ ተቀርጸው ቢካተቱና ከታች ጀምሮ ትምህርቱ ቢሰጥ ሙያው እንዲያድግ ያደርጋል። በተጨማሪ የዜጎች የኢኮኖሚ እይታ በመቀየር ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ሞያው በሚገባ ካለማደጉ የተነሳ የከበሩ ማዕድናት አብዛኛዎች እሴት ሳይጨመርባቸው ለውጭ ገበያ እየተላኩ መቀጠል የለባቸውም የሚሉት አቶ አሰፋ፤ እሴት ተጨምሮባቸው ውጭ በመላክ ከፍተኛ ምንዛሪን በማስገኘት ሀገሪቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ እየሰጠ ያለውን አይነት ስልጠና ለብዙዎች ሊሰጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ስልጠናው ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባም አንስተዋል።

ሌላኛው ሰልጣኝ ሀና ታደሰ ትባላለች። የጂኦሎጂስት ተማሪ ስትሆን፤ ስለከበሩ ማዕድናት በጂኦሎጂ ትምህርት ካገኘችው እውቀት በተጨማሪ የከበሩ ማዕድናት (ጂኦሞሎጂ) በደንብ ለመለየትና ለማወቅ ያስችላል ያለችውን ስልጠና መውሰዷን ትናገራለች።

በስልጠናው ባሰበችው ልክ ስለማዕድናቱ እንድታውቅና በተግባር የተፈተሸ እውቀት እንዲኖራት ያስቻላት መሆኑን ትገልጻለች። በተለይ ማዕድናቱ ላይ እሴት መጨመርን በተመለከተ ጠለቅ ያለ እውቀት የገበየችበት እንደሆነ አጫውታናለች። በወርክሾፑ ማዕድናቱን በማስዋብ እሴት ጨምሮ ለጌጣጌጥ በሚውሉ መልኩ ሰርቶ ለገበያ የማቅረብ ተግባር እያከናወኑ የተማሩ መሆኑን ታብራራለች።

‹‹ስልጠናው ቀደም ሲል ከነበረኝ እውቀት በላይ ስለማዕድናቱ እንዳውቅና ወደዘርፉ በጥልቀት እንድገባ አስችሎኛል›› የምትለው ሰልጣኝ ሀና፤ የከበሩ ማዕድናት በንድፈ ሀሳብ የተማረችውን ትምህርት በእጅ በመንካት፣ በመዳሰስ፣ በመሥራትና በማስዋብ ጨምር በጌጣጌጥ መልኩ በመሥራት መማሯን ትገልጻለች። ይህ ተጨማሪ እውቀትና ሙያ እንድታገኝ እንደረዳት ገልጻ፤ ተጨማሪ ሌላ ሞያ ማግኘቷ ለወደፊቱ በከበሩ ማዕድናት ላይ ለመሰማራት ትልቅ ተስፋ እንዳላት ያሳያት መሆኑን ታመላክታለች።

በአሁኑ ወቅት በዘርፉ በቂ ባለሙያ ባለመኖሩ በሀገሪቱ የከበሩ ማዕድናት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬ እየተላኩ ይገኛሉ። በዘርፉ በልምድ የሚሰሩም ሆኑ ሌሎች እንደዚህ አይነት ስልጠና ቢያገኙ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር በጌጣጌጥ መልክ ተሰርቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ትገልጻለች። ይህም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላል። ማዕድናት በጥሬው ከመላክ ባለሙያዎች እንዲበዙ በማድረግ እሴት ተጨምሮበት ለገበያ እንዲቀርብ ለማድረግ ያስችላል። በሌላ በኩል ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ይረዳል ትላለች።

‹‹ ቀጣይ በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ ያገኘሁት እውቀት በማስፋፋት በተለይ እሴት መጨመር ላይ ትኩረት አድርጌ እሠራለሁ›› የምትለው ጂኦሎጂስት ሀና፤ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ከመጨመር ባሻገር ለውጭ ገበያ በመላክ በማስተዋወቅ ሀገሪቷ ማግኘት ያለባትን ጠቀሜታ እንድታገኝ ለማድረግ እንደምትሠራ ትገልጻለች። የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን በከበሩ ማዕድናት ዙሪያ የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቅሳ፤ ስልጠናው ያለምንም ክፍያ በነጻ እንድታገኝ ስለረዷት አመስግናለች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You