ከቀረጥ ነጻ መደብሮች መከፈት ከተማዋን በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ተመራጭ ያደርጋታል

አዲስ አበባ፡- ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ከቀረጥ ነጻ የምግብ መደብር መከፈቱ አዲስ አበባን ተመራጭ የዲፕሎማሲ ከተማ እንደሚያደርጋት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት አስታወቀ፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ (ኢ ሲ ኤ) ግቢ ከቀረጥ ነጻ የምግብ መደብሮች ከትናንት በስቲያ ሥራ ባስጀመሩበት ወቅት የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ራሄል ጌታቸው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በመንግሥት በኩል ቱሪዝምን ከመደገፍ አኳያ በመዲናዋ እና በሌሎች አካባቢዎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ከእዚህ አንጻር ከቀረጥ ነጻ የምግብ መደብሮች መከፈታቸው የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ በሀገሩም ሆነ በሌሎች ሀገራት የለመዳቸው ግብዓቶች ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ ሳይቸገር እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ ይህም አዲስ አበባ ደረጃዋን የጠበቀች ከተማ ከማድረጉም በተጨማሪ፤ ተመራጭ የዲፕሎማሲ ከተማ ያደርጋታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወይዘሮ ራሄል እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ እንደመሆኗ ብዛት ያላቸው የዲፕሎማቶች ይኖሩባታል፡፡ዲፕሎማቶች ደግሞ ቀን ተቀን በሚከውኑት ተግባር የሥራ እድል ከመፍጠር  እና ገቢ ከማስገኘት አንጻር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

ተቋሙ ላለፉት 60 ዓመታት የኢትዮጵያ ባሕል እና እሴት ከማስተዋወቅ ጀምሮ ከታክስ ነጻ ምርቶችን ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ሲያቀርብ መቆየቱን ያነሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከእዚህ ቀደም ከታክስ ነጻ ምርቶችን አየር መንገድ በተከፈቱ መደብሮች እያቀረበ ይገኛል፤ በተከፈቱ ሱቆችም ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን እንዲያገኙ የተፈቀደላቸው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

ከቀረጥ ነጻ የምግብ መደብሩ ከተለያዩ ሀገራት ልምዶች በመውሰድ የተከፈተ እንደሆነ ጠቁመው፤ ኢ ሲ ኤ ግቢ መደብሮቹ እንዲከፈቱ የተመረጠበት ምክንያት በተለያዩ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግቢው ተመራጭ መሆኑን በማረጋገጥ ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የኢንተርናሽናል ዲፕሎማቲክ ሳፕላይስ (አይዲኤስ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ፓትሪክ ዶየል በበኩላቸው፤ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በ85 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ላይ ለዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ከቀረጥ ነጻ የተለያዩ ምርቶችን ያቀርባል፡፡

ነጻ የምግብ መደብሮቹን ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች ለመክፈት በመስከረም ወር ከኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ጋር ውይይት ማድረጋቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መደብሮቹን ለመክፈት በጋራ ትልቅ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ፓትሪክ ዶየል እንደተናገሩት፤ በመደብሩ የሚቀርቡ እቃዎች ትክክለኛ እና ዋጋቸው ተመጣጣኝ ስለሆነ የዲፕሎማሲውን ማህበረሰብ በጥሩ ሁኔታ ለማገልገል እና ሕይወታቸውን ቀላል ለማድረግ ያስችላል፡፡ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You