
አዲስ አበባ፡– በትምህርት ዘርፍ አገልግሎት ላይ የሚውሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በአማራጭነት የሚተገበሩ ሳይሆኑ ለዘርፉ እድገት እጅግ አስፈላጊ ግብዓቶች መሆናቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ ።
ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ‹‹ሪች ፎር ቼንጅ›› ግብረ ሠናይ ድርጅት እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጁት የትምህርት ቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት ፎረም ትናንት ሲጀመር እንደገለጹት፤ የመማር ማስተማር ሥራዎችን የሚያቀላጥፉ ዲጂታል የትምህርት ግብዓቶች የትምህርት ዘርፉን ዘመኑን በሚመጥን ፍጥነት ለመምራት እና እድገቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ ሚና አላቸው። ከዚህ መነሻነትም ቴክኖሎጂዎቹን ማሳደግና በስፋት መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለፃ፣ የትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ዘርፍ የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የተማሪዎችን ብቃት ለማሳደግ፣ ግላዊ የትምህርት ተሞክሮን ለማስፋፋትና ትስስርን ለማጠናከር ያስችላሉ። ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ከኢትዮጵያ ወጣት ኅብረተሰብ የቴክኖሎጂ ፍላጎት ጋር ተደምሮ የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን ከአማራጭነት ወደ አስፈላጊነት አሸጋግሯቸዋል።
የቴክኖሎጂ ውጤቶች የትምህርት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር እቅድ ለማሳካት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የሕግ ማዕቀፎችን በአግባቡ በመቅረጽና ፍትሐዊነት በመተግበር ለትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የትምህርት ዘርፍ ቴክኖሎጂዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሆነም ጠቁመው፤ በዚህም ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማሳደግ፣ የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን ከሕዝብ አገልግሎት ተግባራት ጋር ለማስተሳሰር፣ አካታች የኢኖቬሽን ምኅዳር በመፍጠር ወጣቶችን፣ ሴቶችንና ተጠቃሚ ሳይሆኑ የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም የግልና የመንግሥት አጋርነትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወጣት ቁጥር ያላት ሀገር በመሆኗ ወጣቶችን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ማፋጠን እንደሚገባም በለጠ (ዶ/ር) አሳስበዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት፣ ‹‹የትምህርት ቴክኖሎጂዎች የትምህርት ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ የዘርፉን እድገት ለማፋጠን የሚያስችሉ በመሆናቸው የቅንጦት መሣሪያዎች ሳይሆኑ አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው›› ብለዋል።
ፕሮፌሰር ክንደያ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ዘርፍ አገልግሎት ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለዘርፉ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። ለአብነት ያህልም የፈተና አሰጣጥና ምዘና ሥርዓቱን እንዲዘምን አድርገዋል፤ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ተደራሽነት ለማሳደግ አስችለዋል።
የ‹‹ሪች ፎር ቼንጅ›› የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ መቅድም ጉልላት፣ ድርጅቱ ለማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ ድጋፍ ያደረገላቸው ሥራ ፈጣሪዎች ትምህርትን በቴክኖሎጂ በታገዘ አሠራር በመደገፍ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻሉ ተናግረዋል።
ፎረሙ ስለትምህርት ቴክኖሎጂ ግንዛቤ የሚፈጠርበት፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ያደረገላቸው ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት እና ሥራ ፈጣሪዎቹ ከባለሀብቶችና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት መድረክ እንደሆነ ወይዘሮ መቅድም አስረድተዋል።
በማስተርካርድ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያ የሠራተኛ ልማት ኃላፊ ፍቃዱ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት መካከል የትምህርት ቴክኖሎጂ ልማት አንዱ እንደሆነ ገልጸዋል። የፋውንዴሽኑ የመማር ማስተማር ማዕከል በትምህርት ዘርፍ ዘላቂ ለውጥ መፍጠር የሚያስችል ምቹ የትምህርት ቴክኖሎጂ ምኅዳር ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዚህም ለዘርፉ ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ ለሚችሉ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ፍቃዱ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም