ለቅድመ ልጅነት ትምህርት ትኩረት መስጠት ማኅበራዊ ክህሎትን ማሳደግ ነው

አዲስ አበባ፡– ለቅድመ ልጅነት ትምህርት ትኩረት መስጠት ማኅበራዊ ክህሎትንና በልጆች መካከል የመማር ፍቅርን ለማጎልበት እንደሚረዳ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ገለፀ።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ሂክማ ከይረዲን ዓለም አቀፍ የሕጻናት የጫወታ ትምህርትን አስመልክቶ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደገለፁት፤ በቅድመ ልጅነት ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ፈጠራን፣ ማኅበራዊ ክህሎትንና፣ በልጆች መካከል የመማር ፍቅርን ለማጎልበት የሚረዳ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ጨዋታን መሠረት ያደረገ ትምህርት የትምህርትን ጥራት ለማሻሻል ይረዳል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ኢትዮጵያም ይህንን በመገንዘብ የትምህርት ተደራሽነትን፣ ጥራት እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል ።

በቅድመ ልጅነት ትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለአጠቃላይ የትምህርት ሂደት ጠንካራ መሠረት የሚጥል ነው፤ ኢትዮጵያም ይህንን በመገንዘብ የትምህርት ተደራሽነትን እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራች ነው ብለዋል ።

የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጨዋታን መሠረት ያደረገ ትምህርት ሲታይ ቀላል እና በእንቅስቃሴ ብቻ የሚገለፅ ቢመስልም፤ ትምህርትን ለመቅሰም እንዲሁም ለአዕምሯዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

በተለይ ከአምስት እስከ ስድስት ዓመት ለሚገኙ ለሕፃናት ማኅበራዊ እና አካላዊ ክህሎትን የሚያላብስ እንደሆነም ገልፀዋል። ትምህርታዊ ጨዋታ ሕፃናት ችግርን እንዴት በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል የሚማሩበት ሂደት እንደሆነም አስታውቀዋል።

ትምህርታዊ ጨዋታ ትኩረትን ለመሰብሰብ እና የማስታወስ ችሎታን ለማሳደግ በተለይ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እና ምክንያታዊነትን ለመላበስ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ጨዋታን መሠረት ያደረገ ትምህርት የቆየ ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን በርካታ ሕፃናት በተለያየ ምክንያት ዕድሉን ሳያገኙ መቆየታቸውን አስታውቀዋል

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ድህነት መሆኑን አመልክተው፤ ችግሩን በመፍታት ሕፃናት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው ብለዋል።

ውይይቱ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው።

በሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You