ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የግሉ ዘርፍ ድርሻ የማይተካ ነው

– ሚድሮክ ሰባት የሻይ ቅጠል  ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፦ ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ የግሉ ዘርፍ ድርሻ የማይተካ ነው ሲሉ የሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ ገለጹ። ሚድሮክ 40 ሺህ አምራቾችን ማፍራት የሚችል ሰባት የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ሊገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አቶ ጀማል አሕመድ ኢፕድ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ስለኢትዮጵያ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል በመፍጠር የግሉ ዘርፍ ድርሻ ከፍተኛ ነው። የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል።

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለ74 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል ያሉት አቶ ጀማል፤ ነገር ግን ይህም በቂ ባለመሆኑ ለብዙኃኑ የሥራ ዕድል መፈጠር አለበት። ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ የግሉ ዘርፍ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ አተኩሮ ሲሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ጀማል፤ የግሉ ዘርፍ ስጋት የሌላቸው የከተማ ኢንቨስትመንቶች ማለትም ንግድና ሪል ስቴት ላይ ያተኩራል። አሁን ላይ ብዙ ሰዎች ነጋዴ መሆን እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

ነገር ግን ንግድ በርካታ የሥራ ዕድል አይፈጥርም፤ የሀገር ኢኮኖሚንም በከፍተኛ ሁኔታ አያሳድግም ያሉት አቶ ጀማል፤ በኢትዮጵያ በአገልግሎት ዘርፍ የሚሳተፈውም ተዋንያን ከፍተኛ ነው። የአቅርቦት ሠንሠለቱ ላይ የሚሳተፉ ሰዎችን አምራች እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገባል ነው ያሉት።

እዚህ ላይ የግሉ ዘርፍ አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚችል ጠቁመው፤ ነገር ግን ብቻውን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት አይችልም። የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል።

ለአብነት በኮንትሮባንድ የሚመጣ ንግድ ሌላ ሀገር ተመርቶ ታክስ ሳይከፈልበት ሀገር ውስጥ የሚመጣ መሆኑን አንስተው፤ በኮንትሮባንድ የሚገባው እቃ ከታክስ ውጪ ሀገር ውስጥ ቢመረት ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል። መንግሥት የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪን ማበረታታት አለበት ስንል ኢኮኖሚውን ከሕገ ወጥ ንግድ ለመከላከል እና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ጀማል ገለጻ፤ ሌላው ሚድሮክ በጅማና በኢሉባቦር አራት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ አንድ ሺህ አርሶ አደሮችን አደራጅቶ ከፍተኛ የሻይ ቅጠል ምርት እያመረተ ይገኛል። ከሚመረተው ምርት 20 በመቶ ለውጭ ገበያ ያቀርባል።

ነገር ግን በአካባቢው ከ150 ሺህ አርሶ አደሮች በላይ በቆሎ እያመረቱ በትንሽ ገቢ በድህነት እየኖሩ ይገኛሉ ያሉት አቶ ጀማል፤ የሻይ ምርትን ለማሳደግና ገቢን ለመጨመር የኦሮሚያ ክልል በ30 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ምርት ለማምረት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ሚድሮክ የሙያ እገዛ፣ የችግኝ አቅርቦት እና ሌሎች ቴክኒካል ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ያሉት አቶ ጀማል፤ ሚድሮክ ከእርሻ መሬቱ በ20 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ ሰባት ግዙፍ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ቢያንስ ከ40 ሺህ በላይ ሻይ ቅጠል አምራቾችን ማፍራት እንደሚቻል አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለወጣቶች የስብዕናና የክህሎት ሥልጠና መስጠት እንደሚገባ ተናግረው፤ ወጣቱ ሥራ ወዳድና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆን የስብዕና ግንባታ ሥልጠናዎች መስጠት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የግሉ ዘርፍ በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል። የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የሀገሪቱን የምርት እድገት ለመጨመር ወሳኝ ነው። በዚህ ዙሪያ በተለይ በወተት ምርት ላይ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You