
አዲስ አበባ ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት 110 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ኃላፊ ጥላሁን ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፕሮግራም አማካኝነት፤ የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየሠራ ይገኛል። በ2017 በጀት ዓመት በሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ከዋናው ግሪድ 140 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እቅድ በመያዝ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ አገልግሎቱ ባከናወናቸው በርካታ ተግባራት 110 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን አመልክተው፤ በቀጣዮቹ በሁለት ወራት 30 የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ብለዋል ።
አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ በዋናው ግሪድ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው 140 የገጠር ቀበሌዎችን በተጨማሪ፤ ከዋናው የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያ (ግሪድ) ርቀው የሚኖሩ አካባቢዎችን በሶላር የኃይል አማራጭ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የማድረግ ሥራዎችም እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ በጀት ዓመት በተሠራው ሥራ ከኦፍ ግሪድ ደግሞ አምስት የገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል።
“አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ከማሸጋገሩ በተጓዳኝ፤ በአካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ የእርሻ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የውሃ ተቋማትና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ጥላሁን፤ በሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፕሮግራም አማካኝነት፤ የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ በማድረግ ሥራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን አንስተዋል።
የመጀመሪያው ችግር የበጀት እጥረት መሆኑን ጠቅሰው፤ በፕሮግራሙ የተያዘው በጀት ሁለት ቢሊዮን ብር በጀት ሲሆን፤ ይህም 100 የገጠር ቀበሌዎችን ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ሆኖም ተቋሙ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን በመውሰድ በዚሁ በጀት 140 የገጠር ቀበሌዎችን ተደራሽ ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱንና የበጀት እጥረት ማጋጠሙን አብራርተዋል ።
ሌላው መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ በገጠር ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን እየዘረጋ ቢሆንም፤ ኅብረተሰቡ ቆጣሪ አስገብቶ ከባህላዊ የኃይል አማራጭ ወደ ኤሌክትሪክ የኃይል አማራጭ ለመሸጋገር የፍላጎት ማጣት መኖሩን አንስተዋል። የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ከተዘረጋ በኋላ ኅብረተሰቡ ካልተጠቀመበት ከፍተኛ የሀገር እና የሕዝብ ሀብት እንደሚባክን አስገንዝበዋል።
በገጠር ቀበሌዎቹ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ከማድረጉ ባሻገር ኅብረተሰቡ ቆጣሪ አስገብቶ ባህላዊ የኃይል አማራጮችን በመተው ወደ ኤሌክትሪክ አማራጭ እንዲገባ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከአገልግሎቱ ጋር አብረው የሚሠሩ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2025 ከዋናው የኃይል ቋት ወይም ግሪድ 65 በመቶ፤ ቀሪው 35 በመቶ ደግሞ ከኃይል ቋቱ ውጪ ተግባራዊ በሚደረጉ የኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ዕውን ለማድረግ የ’ብርሃን ለሁሉ’ ፕሮግራም ሥራ ላይ በማዋል እየሠራ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል ።
በዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም