
አዲስ አበባ፡- የዛሬን ብቻ በማሰብ ነገ እንዳያመልጠን በማስተማር ከመንግሥት ባልተናነሰ የንግዱ ማኅበረሰብም ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከመላው ኢትዮጵያ ከተወጣጡ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ሲወያዩ እንደገለጹት፤ ዘመኑ የአሁንን ተጨባጭ ሁኔታ ማወቅ፣ ያለፉትን ስብራቶች መጠገንና መጪውን መሽቀዳደም የሚጠይቅ ነው። የዛሬን ብቻ በማሰብ ነገ እንዳያመልጠን ለማስተማር ከመንግሥት ባልተናነሰ የንግዱ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
ችግሮቻችን የትናንት እና የነገ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ነገር ግን መንግሥታት የትናንትናውን ችግር ቢፈቱም ነገን መሥራት ካልቻሉ መከራው በሚመጣውም ትውልድ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ትውልዱ የሚረከበውም የተጠገነ ትላንት ነገር ግን ያልተሠራ ነገ ስለሚሆን መከራው ይቀጥላል ሲሉም አመልክተዋል።
መከራችን የትላንት እና የነገ ቢሆንም የእለት የእለቱን ብቻ ከማሰብ በዘለለ ነገን በማሰብ ምክክር ስለማናደርግ ብዙ የመልካም ሥራዎች ጅምሮቻችን ላይ እንቅፋቶች ይበዛሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ሀገር ያሉብን አምስት ዋና ዋና ችግሮች ተገቢው ቦታ እንዳንደርስ እያደረጉን ነው። የወረስነው ድህነትን ለማውረስ የተዘጋጀ ትውልድ መኖሩ ከአምስቱ ችግሮቻችን የመጀመሪያው ነው። ለዚህ በጣም ብዙ ምሳሌዎችን ማንሳት ቢቻልም ለአብነት የወረስነውን ድህነት ለማውረስ ያለን ፍላጎትና መሻት ከፍተኛ መሆኑን በካዛንቺስ በተግባር መታየቱን ገልፀዋል።
የኅብረተሰቡን አኗኗር ለማሻሻል ወደ ተሻለ አካባቢ እንዲሄዱ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መሠረታዊ ጉዳዮች መሟላታቸውን ከማረጋገጥ ይልቅ ሌሎች ስሞችን የመስጠት ልምምዶች ድህነትን ወርሶ ድህነትን የማውረስ ችግር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
ሁለተኛው ችግር እንደሀገር ጠንካራ ተቋም አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠዋት የሰጠውን አገልግሎት ከሰዓት መድገም የሚችል ተቋም አለመኖሩ ለዚህ ችግር ማሳያ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲቪል ሰርቪስ እንቀይር እናሻሽለው ብለን ሥራ ስንጀምር በዘርና በኃይማኖት ስም “ታርጋ” የመለጠፍ ባህል በስፋት ታይቷል ብለዋል።
ከአራሹ ይልቅ ተኳሹን የሚያወድስና ጠዋትና ማታ ጠንክሮ ከሚሠራው ይልቅ ክላሽ አንግቶ የሚሳደበውን ሰው ጀግና የሚል አመለካከት ሌላኛው ሦስተኛው ችግር እንደሆነም አንስተዋል። ጀግና ጠዋትና ማታ ሠርቶ ልጆቹን የሚያሳድግ ሳይሆን ክላሽ አንግቶ ሰውን የሚሳደብ ሰው ነው የሚል የተሳሳተ የአመለካከት ችግር መኖሩንም አብራርተዋል።
ከሚሠራ ሰው ይልቅ ተኳሹን የማወደስ አመለካከት ነጋዴውን እንደ ሥራ ፈጣሪ ሳይሆን እንደሌባና እንደ አጉዳይ እንዲታይ አድርጎታል ብለዋል።
አራተኛው ችግር የስልተ ምርት ችግር ነው። ግብርናን በመጀመር ረጅም ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከእርሻ ጀማሪዎች መካከል ብትሆንም እስካሁን ምርታማ አለመሆኗ፤ የስልተ ምርት ችግር መኖሩ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ የሰው ኃይልን በማብቃትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያለው የስልተ ምርት ችግር መሆኑን ገልጸው፤ ይህን በማለፍ እንዴት ውጤታማ መሆን ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ይበልጥ ማሰብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ከችግሩ ለመውጣትም፤ የተሻለ ውጤታማ መሆን የምንችልባቸው መንገዶችን በማጤን መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አምስተኛው በሀገራችን ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የማገልገል ችግር አንዱ መሆኑንን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ‹‹ሥራ ሠርተው ምን ችግር እንዳለበት የማያውቁ፤ አገልግለው የማያውቁ ሰዎች ስለ ሥራ ይናገራሉ፤ ይህም የማገልገል ችግር ስለመኖሩ አመላካች ነው›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮች ካልተፈቱ ሀገራዊ ችግሮችን መፍታት ከባድ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም