ወልቂጤ:- ለበርበሬ ሥር አበስብስ በሽታ መፍትሄ ማጣታቸው ለኪሣራ እንደዳረጋቸው የጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ አርሶአደሮች ተናገሩ። የደቡብ ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን በበኩሉ አርሶአደሮቹ ለኪሣራ የተዳረጉት የተሰጣቸውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ባለማድረጋቸው እንደሆነ አስታውቋል።
አርሶአደር እውነቱ ሙላቱ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ አቡኮ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ በዚህ የመኸር ወቅት የዘሩት 2 ነጥብ 3 ሄክታር የበርበሬ ማሣ በበርበሬ ሥር አበስብስ በሽታ ተጠቅቶ ከጥቅም ውጭ እየሆነ መምጣቱን ያስረዳሉ። አርሶአደሩ ይህ በሽታ ከአስር ዓመታት በፊት የተከሰተ ቢሆንም እስከዛሬ ድረስ መፍትሄ አለመገኘቱንና በሽታው በተከሰተ ወቅት ለከፍተኛ ኪሣራ እየተዳረጉ መሆኑንም ይገልፃሉ።
አርሶአደር እውነቱ ለዚህ የበርበሬ ማሣ ሦስት ጊዜ ማዳበሪያ የተጠቀሙ ሲሆን፣ ለአራት ዙር የአረም ሥራም ሠርተዋል፤ በዚህም ከ50 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ወጪ እንዳወጡም ይናገራሉ፤ ይሁን እንጂ ማሳው በሥር አበስብስ በሽታ በመጠቃቱ ከጥቅም ውጭ ስለሆነባቸውና በማሳው አንዴ ከተከሰተ በአጭር ጊዜ ሁሉንም የሚያዳርስ በመሆኑ መሬቱን ገልብጠው ሽምብራ ለመዝራት ማቀዳቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል።
ሌላው የቀበሌው አርሶአደር ቤኛ ሰቦቃ፣ በሽታው የበርበሬ ሰብላቸውን እያወደመና ለኪሣራ እየዳረጋቸው ሲሆን በተደጋጋሚ ለወረዳው አሳውቀው ‘ከአቅማችን በላይ ነው’ በሚል መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል። በሽታው አንዴ ከጀመረ ሁሉንም ማሣ ማውደሙ ደግሞ አስከፊ ያደርገዋል ያሉ ሲሆን፣ ለአንድ ኪሎ ዘር እስከ 200 ብር እንደሚያወጡ በመጥቀስ ለሠራተኛ፣ ለማዳበሪያ እና መሰል ወጪዎች ገንዘባቸውን አፍስሰው ውጤት እንደሚያጡ ገልፀዋል።
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተውም የበርበሬ ማሣው ፍሬ መያዝ የጀመረ ቢሆንም እየደረቀና እየጠወለገ መሆኑን አስተውሏል።
ስለጉዳዩ የአበሽጌ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ እያሱ ፋንታሁን እንደነገሩን ፣በሽታው ለበርካታ ዓመታት የአርሶአደሩን ልፋት መና እያስቀረና ለኪሣራ እየዳረገ መሆኑ ቢታወቅም መፍትሄ ግን አለመገኘቱን ያስረዳሉ።
ማሣው በበሽታው ሲጠቃ መጠውለግ የሚጀምር ሲሆን በሽታው በፍጥነት ከሥሩ ጀምሮ ወደላይ በመዛመት ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ እና በየዓመቱ ግማሽ ያህል የበርበሬ ምርትን እያሳጣ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ እያሱ፣ ለድጋፍ ወደ ቀበሌዎች ሲወጡ አርሶአደሩ በምሬት የሚገልፅላቸው ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
በባለሙያ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት በመቸገራቸውና ከአቅም በላይ በመሆኑ በተደጋጋሚ ለበላይ አመራሮች ቢያሳውቁም የከፍተኛ አመራሩ ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት አቶ እያሱ በዚህ ችግር ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለበሽታው መድሃኒት ባለመገኘቱ የተነሳ በሽታው ሲከሰት አርሶአደሩ በዘልማድ የተለያዩ ኬሚካሎችን ወደመጠቀም ተሸጋግሯል፤ ሆኖም ውጤት አልተገኘበትም ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም መምሪያ ሃላፊ አቶ ያዕቆብ ግርማ በበኩላቸው ለዚህ በሽታ መዛመት አንደኛው መንስኤ ከምርምር ማዕከላትና ዘር አባዢ ተቋማት የሚወጡ የበርበሬ ምርጥ ዘርም ይሁን የተሻሻሉ ዝርያዎች አለመኖራቸውና አርሶአደሩ በእጁ ያሉትን ዘሮች እያዘዋወረ መጠቀሙ እንደሆነ ገልፀው ዞኑ ጉዳዩን ለበላይ አካላት አሳውቋል፤ ለአርሶአደሩም ክትትል እያደረገ ነው ያሉ ሲሆን የበርበሬ ሥር አበስብስ በሽታ በዞኑ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነው የማረቆ በርበሬ ከምርት መውጣቱንና መጥፋቱን የተናገሩት አቶ ያዕቆብ፣ ለዚህም ክትትል ማጣቱና ለአርሶአደሩ የተለየ አቅርቦት አለመኖሩን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በዚህ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችንና የምርምር ማዕከላትን ጠርተው በግብርና ሥራ ዙሪያ ባሉ ችግሮች ውይይት መደረጉን የተናገሩት ሃላፊው፣ በተለይም በበርበሬ ዙሪያ ምርምር የሚያደርገው መልካሣ የግብርና ምርምር ማዕከል ጋር ሥራዎች ቢሠሩም የተለየ መፍትሄ ያቀረበ አካል አለመኖሩን ጠቁመው፣ ዞኑ ሃላፊነቱን ተወጥቷልም ብለዋል።
የደቡብ ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ጉዳዩን አስመልክቶ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ምላሽ ፣የበርበሬ ሥር አበስብስ በሽታ አዲስ አለመሆኑንና ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተከሰተ አስታውሰው መቋቋም የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።
በሽታውን ለመከላከልም ለአርሶአደሩ የምክር አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን፣ ምክረሐሳቡን የተገበሩት ውጤት እንዳገኙበት የተናገሩት አቶ መስፍን ከማንኛውም ቦታ ዘር እንዳይጠቀሙ ፣ይልቁንስ ከዘር አምራችና አባዥ አርሶአደሮች እንዲጠቀሙ፣ እንዲሁም የሚጠቀሙትን ዘር ‘አክሮን ስታር’ በተሰኘና አገር ውስጥ በሚገኝ መድሃኒት አሽተው እንዲጠቀሙ በፌደራልና ክልል የምርምር አካላት ጋር በተዘጋጀ ፖኬጅ ምክር ቢሰጥም ሐሳቡን ያልተገበሩ አርሶአደሮች ችግር ገጥሟቸዋል፤ የተገበሩት ግን ችግሩን መቋቋም ችለዋል ብለዋል።
ከበርበሬ ምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘ በምርምር የተገኙ አዳዲስ ዝርያዎች ችግሩን መቅረፍ እንደሚችሉ ተስፋ የተጣለባቸው ሲሆን & apos;ማረቆ ፋና & apos; የተሰኘ ዝርያ የተሻለ ውጤት እያስገኘ በመሆኑ ይህንን ዝርያ አርሶአደሩ እንዲጠቀም ይደረጋል፤ ጎን ለጎንም ምክረ ሐሳቡን እንዲተገብሩ የክትትልና ድጋፍ ሥራ በስፋት እንደሚሠራ አቶ መስፍን ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን በ2011 የምርት ዘመን 6 ሺህ 357 ሄክታር የበርበሬ ማሣ ለማዘጋጀት ታቅዶ 5 ሺህ 27 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን በተለይም አበሽጌ፣ ቀቤና፣ ምስቃንና ማረቆ በተባሉ ወረዳዎች በስፋት ይመረታል።
ድልነሳ ምንውየለት