አሁን አሁን እየተደጋገመ በሚፈጠ ረው መድረክ የማቀብለው ብቻ ሳይሆን የምቀበለው ነገር ለእኔም ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር፤ እውቀት እየጨመረልኝም በመምጣቱ መቀባበል መደጋገፍም ነውና ተደስቻለሁ፤ መተባበር መግዘፍም ነውና እንዲህ መሰሉን መድረክ ለሃሳቦች መንሸራሸር ለመልካም ውጤት ማመላከቻነት ይረዳልና እጅግ ጥሩ ነው። ስለዚህ መሰል የፅሑፍና የንግግር መድረኮች፣ እንዲበራከቱ ማበረታታት የተገባ ነው።
አንድ ነገር ልጨምርና ወደ ዋናው ሃሳቤ ልውሰዳችሁ። ባለፈው ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በተገኙበት በተደረገው የበጎ ፍቃድ አስፈላጊነት ውይይት ላይ፣ ትንሹን ልጄን መድረኩ ላይ ይዤው ወጥቼ ነበር። ያንን አጋጣሚ የተጠቀምኩት በሁለት ምክንያት ነው፤ አንደኛው ምክንያቴ ልጄ…(ልጃችን) በእውነተኛና መልካም ጉዳይ ላይ በሰው ፊት መቆምን እንዲለምድ ላደፋፍረው ስለፈለግኩ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያቴ ብዙዎቻችን ልጆቻችንን «ልጅ ልጅ» ለሚል ነገር ብቻ የምንጋብዛቸው በመሆኑ የትልልቆች ስብሰባን ትልቅነትም እንዲያየውና በልቡ ከትቦ እንዲያስቀምጠው ስለፈለግሁ፤ አስቤበት ያደረግኩት ነው። በተጨማሪም በዚህ አሳሳቢ ጊዜ የልጆቻችን የወደፊት ዕጣ ነገርም ስለሚያሳስበኝ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዲያድግም አደራ ለማለት ነው ።
ኢትዮጵያ ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ፣ ዋላይ (fluid like) ነው፤ አንድ ሰሞን የሰከነ ሲመስል እየደፈረሰ፣ የረጋ ሲመስል እየተናጠ፣ ወዴትነታችን ግራ እያጋባ ነው። ይሁንናም ምንም እንኳን ግራ አጋቢ ሁኔታ ላይ ብንሆንም፤ ጭጋጋማው መሬት ነገሮችን አጥርተን እንዳናይ ቢጋርደንም፣ ፍርሃት አዛማች ነገሮች እዚህና እዚያ እንደ አስቀያሚ የቆርቆሮ ከበሮ ቢንኳኩም በሀገራችን ተስፋ አንቆርጥም።
አንድ ሰሞን የማላስታውሰው ሰዓሊ፣ የሣለው አንድ ስዕል ላይ እናት ከጣደችው ምድጃ ያበሰለችውን ቂጣ ወደአንዱ ልጅ ሳህን አውጥታ ስታስቀምጥ የሁለቱም ልጆቿ እጅ ወደቂጣው ተወርውሮ ሲመጣ ቂጣው ተመልሶ ወደዓመዱ ሲወድቅ እናት በድንጋጤ አፏን ስትይዝ የሚያሳይ ነው። ሌላ ቂጣ ይሁን ሙልሙል ምጣዱ ላይ አለ ፣ግን… አልተነካም ፤ ወይም ከምጣዱ አልወጣም ፤ (በነገራችን ላይ ስዕሉ እናት ይልና መልክ ያልለየ ምስል ነው የተቀመጠው፣ የቸገራቸው እናቶች ሁሉ ወኪል ናት) ሰዓሊው፣ እናቲቱ መጨነቋን ነው ያጎላው።
የዚህ ምስል ሥም ሰዓሊው «ኢትዮጵያ» ቢላት አሁን ተመኘሁ። እናት ኢትዮጵያ፣ በልጆቿ አለመተሳሰብ ወደማያስፈልግ ጠርዝ የተገፋች፣ ባለመስማማታቸው የደነገጠች፣ ያለውን አፍርሰው የሚመጣውን ለመብላት እንኳን ከቀልባቸው ጋር ያልሆኑ ልጆች፣ የወለደችን እናት የሚያሳይ ምስል ነው፤ ወደ አእምሮዬ የመጣው።
ሥዕልና ህልም እንደተርጓሚው ነው፤ የሚፈታው የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ባምንም እሳቱም፣ ዱቄቱም፤ ቂጣውም፣ ሃሳቡም፣ ምጣዱም፣ ምድሪቱም ለሁላችንም የምትበቃ ሆና እንዳትበቃ የምንጣላ፤ እንዳትበጀን የምንባጅ እየመሰለኝ ከመጣ ቆይቷል።
አፈናና ጭቆና በበረታበት ዘመን ድምጻቸው እጅግም ያልተሰሙ አካላት የነፃነት አየር በሚነፍስበት በዚህ ወቅት አየሩን በጥላቻ ትንፋግ ሞልተውት እዚህና እዚያ እያፈናቀሉና እያቃጠሉ ነው፤ የሚታዩት። እውን ነፃነትን የሚሸከም፣ ፍቅርን የሚያንሸራሽር ልብ አጥተንና አቅቶን ነው፤ ወይስ ስላልፈለግን ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ።
በኢትዮጵያ ምድር ያለውን የጥላቻ እሳት የሚለኩሱት ሰዎች ነበልባሉ ወደእነርሱ የሚደርስ አይምሰላቸው እንጂ ጊዜ ምስክር ነው፤ የሚንቀለቀል ሰደድ ይገጥማቸዋል። የሚገርመው «ነፍሰ ገዳይ ሰው በቅድሚያ የገደለው ራሱን ነው» የሚል ብሂል ቀድሞም አለ፤ ምነው ከተባለ ለራሱ ክብር ያለው ሰው ሌላውን አያዋርድም፤ ለራሱ ፍቅር ያለው ሰው ሌላውን ለመጥላት ልበ ብርቱ አይሆንምና። ጥላቻ ያለበት ሰው ሌላውን ከመጥላቱ በፊት ራሱን በሌሎች እንደተጠላ አድርጎ የሚቆጥር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ከላይ ያነሳኋቸው የጥላቻና ጭካኔ ሃሳቦች ምንጭ በራስ እምነት ከማጣት፣ መልካም ሃሳብ ካለማስተናገድ፣ ተስፋ ከመቁረጥና በሕይወትና ተያያዥ ነገሮች ላይ አማናዊነት ከማጣት መንጭቶ የሚፈፀም የፍርሃት እርምጃ ነው። በአጭሩ ሰውን፣ የሚያስፈራራ ሰው ራሱ አደገኛ ፈሪ ነው፤ ፈሪ ደግሞ ጨካኝ ነው። በተቃራኒው ጀግና ርህሩህና ለጣለው ጠላቱ አዛኝ ነው።
እኛ በከፊል ወይም ከከፊል በበለጠ ያጣን የሚመስለኝ የርህራሄና የፍቅር ጀግንነት ነው። ፍቅር በልባችን ኖሮ መላዋ ምድር በደስታ ስትጠበን የሚሰማን መልካም እውነት፣ መገለጫው እርሱ ነው። ፍቅር፣ አእምሯችን ከእርሱ በስተቀር ሌላ እንዳናስብ አድርጎ ዥዋዥዌ ሲያጫውተንና እኛም በዚህ አየር ውስጥ መኖራችን ሲመቸን በፍቅር ውስጥ አለን ማለት ነው።
ፍቅር ነገን አለመፍራት ነው፤ ፍቅር ተስፋን መታመን ነው፤ ፍቅር በየዋህነት እምነትን ለሌላ ሰጥቶ በራስ ውስጥ ጥቅልል ብሎ መተኛት ነው።
ስለዚህም ፍቅርን በልቡ የሰነቀ፣ የሚመኘው ነገር እንግዳ ቢመስልም አንዳች ጥሩ ነገር ጠብ እንዲልለት የሚፈልግ ሰው ተምሳሌት ሲሆን ተስፋ እንኳን የሌለበት በሚመስል ምድረ በዳ ላይ ችግኝ ተተክሎ ደን እንደሚሆን ማሰብ የሚችል ሰፊ- ልብ ያለው ነው፤ ለዚህም ብርቱ እምነት ማዳበር ይችላል፤ ምክንያቱም ለአካባቢው፣ ለሀገሩ፣ ለሕዝቡና ለራሱ ፍቅር አለውና።
ፍቅር የሌላቸው ሰዎች በጎ ህልም የላቸውም፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚራመዱ ናቸውና ሜዳውን ሲረግጡ እንኳን ገደል ነው፤ ብለው ይፈራሉ፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች ከሌሎች ህብረት ማድረግን አይወዱም፤ ፍቅር የሌላቸው ሰዎች አቋራጭ መንገድን ለድላቸው መግቢያነት ይመርጣሉ። ስለዚህ አቋራጩ መንገድ፣ ደም የሚያፋስስና ጥፋት የሚያስከትልም ቢሆን ይመርጡታል እንጂ፤ በትዕግስትና በታሰበበት መንገድ መጓዝን የሰነፍ ሥራ አድርገው ነው፤ የሚያስቡት። ስለዚህ «ሁሉንም ወይም ምንም» ዋና መፈክራቸው ነው። ተስፋ በቆረጠ ሰው ፊት መገኘት ደግሞ ጭዳነት ነው።
በፍቅርና በጥበብ መኖር ከራስ ተርፎ ለሌሎች መኖርን ሲያስከትል በብልሃት መኖርም ኑሮን ያጣፍጣል። ካለበለዚያ በጥበብ አልባና በሰነፎች እጅ ሥልጣን ስትወድቅ ወይም ክፉ መሳፍንት ሥልጣን ሲይዙ የሕዝብ እንባ ይበረክታል፤ ጭንቀትም ይበረታል።
ወደሀገሬ ኢትዮጵያ ይህንን ሃሳብ ሳመጣው በጥበብና ብልሃት የታሸ ህብረት ወደተሻለ ሀገርነት ያሳድገናል ብዬ በጽናት የማምንና ሰሞኑን በጠርዘኛ ሃሳብ አዝማቾች ስለሚናፈሰው ትብብርን አሳንሶ የማየት ዝንባሌ በትንሹ መናገር ይገባኛል፤ ብዬ ስላመንኩ ነው።
ከሀገራችን ነባር የአባቶቻችንና እናቶቻችን፣ አባባሎች ውስጥ «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» «በህብረት ቆመው ብረቱን ሰብረው» «ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ»«ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ» ሲሉ፣ ህብረት ብረትን እንደሚሰብር ፣ አንበሳን እንደሚያስር፣ ምክር ከሰው እንደሚዳብርና ብልሃት ችግርን እንደሚያስቸግርና ይልቅ ወደ ቀላልነት እንደሚያመጣው ምስክሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን አስቸጋሪ ወረራዎች የተቋቋመችው በህብረት፤ በአንድነትና በብልሃት መሆኑን ጠቋሚዎች ናቸው።
ይህ ከመተሳሰብ የሚመነጭ የፍቅር ዘለበት ስሙ፣ ህብረትና አንድነት ነው። ይህ የመነጣጠል ፀርና የመመሰቃቀል መውጊያ ፍቱን መድኃኒት ስሙ፣ አንድነት ይባላል። ይህንን ትተው በነጠላው መቆም ያዋጣናል፤ ለብቻችን ስንሆን ይሞቀናል፤ የሚሉት ወንድሞቻችን ከተመከሩት ሃሳብ ይልቅ፣ ሃሳቡ ለመከሯቸው የሚጠቅም መሆኑን እንዲገነዘቡት ማሳሰብ እንወዳለን።
ወገናቸውን፣ ከ«የትም የመጣ ሰፋሪ» ብለው በሀገሩ የሀገሩ ዜግነት እንዳይሰማውና የማያውቀውን ሀገር እንዲናፍቅ በማድረግ የሚያገኙት ሐሴት ፊታቸው ላይ ለጊዜው በጊዜው ምክንያት ሲንፀባረቅ እያየን ነው። ደስታቸው ምን ያህል እንደሚቆይ ግን ጊዜ ራሱ የሚያሳየን ይሆናል።
የሚገርመው ልዩነትን ሰባኪዎች፣ የልዩነት ሰበካቸው አለማቆሙ ነው። ውጤቱም መልካም አይደለም። ለእነርሱ ማትረፊያው ግጭት እንጂ ሰላም አይደለምና። ለዚህ በቂ ምሳሌ የምትሆነን የሞቃዲሾዋ ሶማሊያ ናት። ከብሔረ- ሶማሌ ወርደው፣ ጎሳው አልበቃ ብሏቸው፣ ከጎሳ ወደ ነገድ፣ ከነገድ ወደቤተሰብ ወርደው በአያት ልጅነት ቆጠራ ጠመንጃ ይማዘዛሉ። ልዩነት እና የልዩነት ሰበብ ማለቂያ የለውም ። (ይህን በወቅቱ ዓለምአቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር «የርዳታ አሰጣጥና ተግዳሮቶቹ» በሚል ባቀረበው መጣጥፍ ላይ ነው።) ስለዚህ ለአያያዝ ፣ «ከዝርዝር ድፍን ብር» እንዲሉ የአራዳ ልጆች ከመበተን አንድነት ያለጥርጥር አዋጪ ነው።
እነዚህ መነጠልን ወይም መበተንን እንደዘይቤ የሚይዙ ኃይሎች፣ ሲመረ መሩ፣ እጅግ ምስጢረኞች፣ ድንገተኛ ጥቃት ፈጻሚዎች (አድመኞች)፣ ራሳቸውን ብቻ የሚያምኑ፣ የሌሎችን ገንቢ ሃሳብ እንኳን ለመስማት የሚፀየፉና ጨካኞች ናቸው። ከመካከላቸው ለዘብ ያለ ሃሳብ ያለው ሰው ከተገኘ ወዮለት ፤ ፍጻሜው አስከፊ ነው። ከሰይፋቸው አያመልጥም ።
በሩዋንዳ በለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ፣ ጽንፈኛዎቹ ሁቱዎች ያደረሱትን ጥቃት ለሚያስብ ባለአእምሮ፣ በዓለም ዙሪያ፣«የተነጣዮች እናታቸው አንድ ናት» የሚያስብል መገረም ይፈጥራል፤ «ብሔር»ም እንደሌላቸው ያስታውቃሉ። ካልመሰላቸው የራሳቸውንም ብሔር አባል ለማጥፋት አያመነቱምና። መንስዔ ነገራቸው ጥላቻቸውን ወደጠርዝ በመግፋትና በኮሚኒኬያቸው በማነሳሳት የሚመኙትን ሥልጣንና ጥቅም ማጋበስ እንጂ ለማንም ነፃነት «ደንታ» የላቸውም።
እንደ እኔ – እንደ እኔ፣ የህብረትና አንድነት ኃይሎች ሁለት ሦስት ሥራዎች በስፋት ሊሰሩ ይገባል ብዬ አስባለሁ። አንደኛ፤ በሚገኙት መድረኮች ሁሉ የህብረትን ጉልበት፣ የአንድነትን ብርታት፤ የአብሮነትን ስምረት አበክረው መናገር ተደማጭ ከሆኑ ሰዎች ይጠበቃል።
ይህም፣ በክረምትም ሆነ በበጋው ትምህርት ወቅት፣ ይህንን ጽንሰ-ሃሳብ የሚያራምዱ ተጋባዦች በትምህርት ቤቶች፣ በውድድር ስፖርት ስታዲየሞች፣ በየአብያተ-ክርስቲያናቱና በመስጊዱ፣ እየቀረቡ እንዲናገሩና ሁላችንም ለሁላችንም አስፈላጊ ቅመሞችና ጠቃሚ አካላት እንደሆንን የሚያስገነዝቡ ዓውዶች ሊፈጠሩ ይገባል።
በተለይ ከትምህርት መጻሕፍት ጋር በአባሪነት የሚነበቡ አጋዥ መጻሕፍት በሁሉም ደረጃዎች፣ ማለትም ከሙዓለ- ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ዓምባ ድረስ እንዲሰራጩ በማድረግና ወርክሾፖች በማዘጋጀት መስራትና ጨለማውን መግፈፍ ጭጋጉንም ማጥራት ይገባል።
በሌላ በኩል ጥላቻንና ቂም ቁርሾን የሚያመለክቱ ሐውልቶችንና አጸዶችን ማስወገድ አንዱ መንገድ ሲሆን፣ ማፍረስና ማፍለስ አይገባም ከተባለም፣ ሐውልቶቹ «የመነጣጠል ዘመን መታሰቢያዎች» ተብለው እንዳለ እንዲቀመጡ ማድረግ ይቻላል። እስከመቼ አንዱ በሌለ ቁስል እየተጠዘጠዘስ እንዲኖር ይደረጋል? ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት ቢያስቡበትና አስተሳሳሪና አግባቢ፣ አፍቃሪና አዋዳጅ መታሰቢያዎች በየስፍራው ቢተኩ መልካም ይሆናል።
ቀደም ሲል በብሔራዊ ቴአትር መድረክ፣ «መፍትሔው ኢትዮጵያዊነት ነው»፣ ብለን ከሚለያየን የሚያኗኑረን፤ ከሚከፋፍለን የሚያጣምረን፣ ከሚበትነን የሚሰበስበን ሃሳብ በብዙ መለኪያ ያይላል፤ ብለን አምነን ነው። እውነት ነው፤ ከመበተን መሰብሰብ ከመነጠል ህብረት የሚያዋጣ መሆኑን እናምናለንና። ጥላቻና መናናቅ የመበተን ወላጆች ሲሆኑ፣ ፍቅርና መከባበር ደግሞ የመሰብሰብ ናቸው። አንድነትን ስለጮህን ብቻ ሳይሆን የምናነግሰው፣ የሕይወታችን ዘይቤ በማድረግና በምንገናኝባቸው የኑሮ መድረኮች ሁሉ፣ የሕይወት ችግኝን በመትከልና የጥላቻ አረምን በመንቀል መጓዝ ከሁላችንም የኢትዮጵያ መልካም ልጆች ሁሉ ይጠበቃል። ለኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ የሚመጥን አዳባሪ ታሪክ በዚህ ትውልድ በመስራት የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ ታሪክ ተጋሪዎች ለመሆንም ነው !!
ከመካከላችን በሃሳብ ሞገድ የበረታ፣ ሌላ አብዲሳ አጋ፣ ሌላ አገኘሁ እንግዳ፣ ሌላ ባልቻ ሳፎ፣ ሌላ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ሌላ ደስታ ዳምጠው፣ ሌላ አሊቶ ሔዋኖ፣ ሌላ ገረሱ ዱኪ፣ ሌላ አቢቹ፣ ሌላ አሉላ አባ ነጋ፣ ሌላ አቡነ ጴጥሮስ፣ ሌላ የአርበኝነትና የቀለም ቀንዶች ማውጣትና ለሀገር በረከት ማብቃት አለብን። የጠቀስናቸው አበውም፣ ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ነፃነትና ለሕዝቡ ሉዓላዊ መብት ታግለው አርፈዋልና አፈሩ አይክበዳቸው። በእኛ የልዩነት ጸብ እነርሱ አይክሰሩብን።
ክፉዎች፣ የጣሉን ሲመስላቸው እየተነሳን፤ የዘረሩን ሲመስላቸው እያንሰራራን ወደፊት እንራመዳለን እንጂማ ተሳልቀውብን አንቀርም፤ በተባበረ ክንዳችን፣ ጠባቡን የገበያ ደረታችንን እያሠፋንና የኢኮኖሚ ደዌያችንን እየፈወስን፣ በህብረት እንጠናከራለን እንጂ፤ እንደሚመኙት ተነጣጥለን ተሸመድምደን አንቀርም። እንነሳለን፤ እንቀጥላለን እንጂ አንቋረጥም፤ አናቋርጥም፤ ችግኞችን በመትከል የልምላሜ ባለቤቶች፤ እኩልነትንና አንድነትን በመዝራት የሰላምና የብልጽግና ጌቶች እንሆናለን!!!
ኢትዮጵያ በቀና አሳቢ ልጆቿ ህብረት ተከብራ ትኖራለች!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ