
አዲስ አበባ፦ በሶማሌ ክልል ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ ከ144 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የኢነርጂ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ መሐሙድ አሕመድ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ቢሮው በሶማሌ ክልል ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ ነው።
በሶማሌ ክልል ዳራቶሌ ከተማ፣ ሂግሉሌ ከተማ፣ ቦቆማልዮ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ሁለት ከተሞች የሚኖሩ የክልሉ ነዋሪዎች ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኙ ነው። በቅርቡ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባገኘችው ቦቆማልዮ ከተማ ብቻ ሰባት ሺህ ቤቶች ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ችለዋል ብለዋል።
በአንድ ቤት ውስጥ በአማካኝ ስድስት ሰዎች እንደሚኖሩ ገልፀው፤ በክልሉ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ ከ144 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል። በአገልግሎቱ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ማዕከሎች፣ የንግድ ተቋማት እና የአስተዳደር ቢሮዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስታውቀዋል ።
እንደ አቶ መሐሙድ ገለፃ፤ ቢሮው ዋናው የኃይል ቋት በማይደርስባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል።
“ከነዚህም መካከል በኅዳር ወር 2017 ዓ.ም የተመረቀውና በሶማሌ ክልል በሊበን ዞን በቦቆልማዮ ከተማ የተገነባው ማመንጫ የሚጠቀስ ነው። ይህም በሀገሪቱ ትልቁ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ነው። ሁለት ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም አለውም” ብለዋል።
አምስት ሺህ 292 ሶላር ፓኔሎች ተገጥመውለታል። የአንዱ ሶላር ፓኔል ኃይል የማመንጨት አቅም 380 ዋት መሆኑን ገልጸው፤ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የ21 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር፣ የሁለት ነጥብ አምስት ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም፤ የአምስት ትራንስፎርመሮች ተከላ መከናወኑን አስታውቀዋል ።
አገልግሎት ከጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ 500 ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አድርጓል ያሉት አቶ መሐሙድ፤ በአገልግሎቱ አሁን ላይ ሰባት ሺህ ቤቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። በቀጣይ ከ36 ሺህ በላይ ቤቶች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም