
አዲስ አበባ፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ይበልጥ ለማጠናከር ከሀገር ውስጥ ዕድሎች በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ዕድሎችን በማደን መጠቀም ይገባል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የውጭ ጉዳይ እና የኢኮኖሚ ሴክተሮች ቅንጅታዊ ጉዞ ለተቃና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት ውይይት ሲካሄድ እንዳሉት፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ጉዳይ ዋና ምሰሶ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ይበልጥ ለማጠናከር ከሀገር ውስጥ ዕድሎች በተጨማሪ በውጭ የሚገኙ ዕድሎችን በማደን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች ባለችበት ወቅት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ከውጭ ዓለም ጋር በጥብቅ ለማስተሳሰር ስለሚያስችል በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ኢንቨስትመንትና ንግድን ማስፋት ይገባል ያሉት አምባሳደር ሀደራ፤ ዲፕሎማቶች የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በውል ተገንዝበው ለሌሎች ማስረዳትና የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስገንዝበው፤ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅሞች ከውጭው ዓለም ጋር በማስተሳሰር ንግድና ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ወደፊት ማሻገር የምንችለው በቅንጅት መጓዝ ስንችል ነው ያሉት አምባሳደር ሀደራ፤ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር ሴክተር ዘለል የባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ያለመ የዲፕሎማሲ መመሪያ መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት ያደረገው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ለኢንቨስትመንት ዘርፍ አዲስ ዕድልን መፍጠሩን ተናግረዋል።
ማሻሻያው በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በርካታ የውጭ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብም በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አመልክተው፤ ካለው ሀገራዊ አቅም አንጻር ግን አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የጋራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ሀገራት እየሠሩ ያሉ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን ለመሳብ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች እንደምትገኝ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የተመዘገቡ ውጤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ለውጥ በልኩ ተገንዝቦ ለሌሎች በማስረዳት በኩል እጥረቶች ይስተዋላሉ። በመሆኑም ለኢኮኖሚ ዲፕማሲ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አቅም ለማሳደግ መሥራት ይገባል ብለዋል።
መድረኩ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና በኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም