
– ለመደበኛ ወጪ 1 ትሪሊዮን 183 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ሲመደብ፤
– ለካፒታል ወጪ 415 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንደሆነ ተመላክቷል
አዲስ አበባ ፡- የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር መሆኑ ተጠቆመ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 35ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትን በተመለከተ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፤ 2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ ረቂቅ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ሆኖ ቀርቧል። ከዚህም ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 1 ትሪሊየን 183 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 415 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ 314 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር ሆኖ መቅረቡን ጠቅሰዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከፌዴራል መንግሥት ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች እና ከውጭ ርዳታ በድምሩ 1 ትሪሊየን 510 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ተገምቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዚሁ ውስጥ ከሀገር ውስጥ ገቢ 1ትሪሊየን 228 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ( 81 ነጥብ 3 በመቶ)፣ ከቀጥታ የበጀት ድጋፍ ዕርዳታ 235 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር (15 ነጥብ 6 በመቶ) እና ከፕሮጀክቶች ርዳታ 46 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር (3 ነጥብ 1 በመቶ) ሊገኝ እንደሚችል መታቀዱን ገልጸዋል።
የ416 ነጥብ 8 ቢሊዮን የበጀት ጉድለት እንደሚታይ ጠቁመው፤ የበጀት ጉድለቱን ከቀጥታ በጀት ድጋፍ ብድር፣ ከፕሮጀክት ብድር እና ከሀገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን አመልክተዋል።
ከጠቅላላ የበጀት ጉድለት ውስጥ 228 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ዕዳ ክፍያ የሚውል እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተጣራው የበጀት ጉድለት ከጠቅላላው የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያለው ድርሻ 1 በመቶ እንደሆነ አስረድተዋል።
የተጣራ የሀገር ውስጥ ብድር ድርሻ 0 ነጥብ 9 በመቶ በመሆኑ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ተግባራዊ ከሚደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ጋር ተጣጥሞ ስለሚሄድ በዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ይታመናል ብለዋል።
የካፒታል ወጪ በጀቱም ተግባር ላይ ከሚውልባቸው ጉዳዮች መካከልም ነባር መንገዶችን ማሻሻል፣ የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ማስፈጸም፣ የመስኖ ልማትን ማስፋፋት፣ በቆላማ አካባቢዎች የሚደረጉ ምርምሮች መደገፍ፣ በጦርነት ምክንያት የወደሙ ንብረቶችን እና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ወደነበሩበት መመለስ እንደሆኑ አብራርተዋል።
እንዲሁም ለመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን፣ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ለገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፣ በጤናው ሴክተር ለሥርዓተ ምግብ መሻሻል፣ ለእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት እና ለመንግሥት ቢሮዎች ግንባታ እንደሚውል ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ጥያቄዎች፤ ተጀምረው የቆሙ የመንገድ ፕሮጀክቶን በሙሉ በበጀት ዓመቱ ማጠናቀቅ ይቻላል ወይ? በጀቱ የደመወዝ ጭማሪን ለምን ታሳቢ አላደረገም? ነዳጅን በሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች የሚጣለው አዲስ ታክስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? ካፒታል በጀቱ የጠቅላላውን በጀት 21 በመቶ ብቻ መሆኑ ኅብረተሰቡን ለማገልገል አናሳ አይሆንም ወይ? የሚሉት ይገኙበታል። አቶ አሕመድ በምላሻቸው፤ የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ብቻ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር እንደሚስፈልግና ይህንን በአንዴ መተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆን አመልክተዋል።
የደመወዝ ጭማሪ ከተደረገ ገና አስር ወራትን እንዳስቆጠረ አስታውሰው፤ ጉዳዩን በርጋታ መመልከትና መነጋገር እንደሚያስፈልገው ጠቅሰዋል።
በነዳጅ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ላይ ታክስ የሚጣለው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማበረታታትና ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ እንደሆነም አስረድተዋል። ካፒታል በጀቱ ትንሽ ነው የሚለው አስተያየት ትክክል እንዳልሆነ ጠቁመው፤ መደበኛው በጀት ትልቅ ከካፒታል በጀቱ ጋር ሲነጻጸር ብዙ መስሎ ቢታይም በውስጡ የሚከፈል ብድርና ሌሎች ወጪዎችንም የያዘ እንደሆነ ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የመንግሥት በጀት 1 ነጥብ 43 ትሪሊዮን መሆኑ ይታወሳል።
በኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም