ውድቅት ነው። ከእኩለ ሌሊት በኋላ። በዚህ ሰዓት ብዙዎች በእንቅልፍ ላይ ናቸው። በሮች ጠብቀው ተዘግተዋል። የእግረኞች ዳና አይሰማም። ከወዲያ ወዲህ የሚሉ ውሾች እንደወትሯቸው አካባቢውን ወረው መጯጯህ ጀምረዋል። በመንገዱ አንዳንድ ስፍራዎች ስካር ያናወዛቸው ጠጪዎች እግራቸውን ከወዲያ ወዲህ እያማቱ ይንገላወዳሉ። ከአንዳንዶቹ አንደበት የሚሰማው ቃል በጎነት የለውም። በስድብ የተዋዛው ንግግራቸው ለጆሮ የሚከብድ ነው።
በመንገዱ ግራናቀኝ ለንግድ የተቀመጡ አንዳንዶች የደንበኞቻቸውን እጆች ናፈቀው ዓይኖቻቸውን ያንከራትታሉ። ሁሌም ቢሆን በዚህ ሰዓት ይህን ማድረጉን ለምደውታል። የተቀቀለ እንቁላልና ትኩስ ድንች በሚጥሚጣ ይዘው የመንገድ ዳር ንግዳቸውን ያጦፋሉ። በስካር ሆዳቸው ቦዶ የሚሆን ደንበኞችም እንደተለመደው ከእነሱ ያገኙትን ጎርሰው ወደመጠጣቸው ይመለሳሉ።
በዚያን ምሽት በፒያሳ አካባቢ ከሚገኙት ንግድ ቤቶች በአንዱ ገበያው ከወትሮው ለየት ብሏል። ቡና ቤቱ በደንበኞች ተሞልቶ በሙዚቃ ጩኸት አካባቢውን እየናጠው ነው። በየጥጉ ተቀምጠው ሲጋራቸውን የሚያቦኑ ጠጪዎች በጭስና በሙቀት መሀል ናቸው። ሰዓቱ እየገፋ ቢሆንም ደጋግመው እያዘዙ መጠጣታቸውን ቀጥለዋል።
በርከት ብለው ጨዋታ ከያዙት መሀል ገሚሶቹ በስካር መዳከማቸው ያስታውቃል። በስፍራው የሚስተናገዱትን ሴቶች እየጎነተሉ ጭምር ለማግባባት ይሞክራሉ።አንዳንዶቹ ደግሞ አብረው ለማደር ሂሳብ መደራደር ይዘዋል። በዚህ ስፍራ መግባባትና መከራከር፣መጣላትና መካረር በግልጽ ይስተዋላል።
ደረጀ ቢተው ወደ ቡና ቤቱ የደረሰው ገና በጊዜ ነበር። ከጓደኞቹ ጋር ሲጠጣና ሲገባበዝ ቢያመሽም ቆይታው የበቃው አይመስልም። በላይ በላዩ የሚያዘውን አልኮል ደጋግሞ እየተጎነጨ ነው። አሁን ደግሞ በድንገት ትኩረቱን በሳበው ጉዳይ መብከንከን ጀምሯል።
ቦግ እልም ከሚለው መብራት መሀል ከወዲያ ወዲህ የሚሉት አስተናጋጆች በደማቁ ሙዚቃ እየተወዛወዙ ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ። አንዳንዶቹ በእጃቸው የመጠጥ ብርጭቆ ጨብጠው ሲጋራቸውን ይምጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ በተመደቡበት ጠረጴዛ ላይ ከወንበራቸው ተቀምጠው በሀሳብ ይናውዛሉ።
መልከ ብዙው የምሽት ገጽታ ትካዜን ከቅብጠት፥ ጩኸትን ከዝምታ ቀላቅሎ ያስተናግዳል። ባለአጫጭር ቀሚስ ሴቶች የብዙዎችን ትኩረት ለመሳብ የራሳቸውን ልምድ እየተጠቀሙ ገበያን ለማግኘት ይሞክራሉ።
ደረጀ ሰብሰብ ብለው ሞቅ ያለ ጨዋታ ከያዙት ባልንጀሮች ላይ ዓይኑን ከተከለ ቆይቷል።ጨዋታቸው እንዳልተመቸውም ከሁኔታው ያስታውቃል። ባሻገር እያንጋጠጠ በንዴት የሚያቦነውን ሲጋራ በእግሩ እየደፈጠጠ መልሶ ሌላ ይተረኩሳል።
በሞቅታ ከሚወዛወዙት መሀል ደመቅ ብላ የምትታየው ሴት ዳንስ ከሌሎች ሁሉ ለየት ይላል።በተለይ ደግሞ ከአንደኛው ጋር ያላት ቅርበት ትኩረት የሚስብ ዓይነት ነው። የሁለቱ ሁኔታ ይበልጥ መፈላለጋቸውን ያሳብቃል። ልጅቷ ከመጠጡ እየተጎነጨች ከወጣቱ ጋር ትደንሳለች። እሱም ቢሆን የፍቅር በሚመስል ዓይን እያስተዋላት እንቅስቃሴዋን ይቃኛል።
ደረጀ የሚሆነውን ሁሉ ልቅም አድርጎ ማስተዋል ጀምሯል። ሙዚቃው እየናረ ጨዋታው በደመቀ ቁጥር የግንባሩ ስር ይወጠራል። ጥርሱን እየነከሰና ራሱን ከላይ ታች እያወዛወዘ ዓኖቹን ከጨዋታው መሀል ሰዶ አንገቱን ይመልሳል።
እሱ ልጅቷን ከዚህ ቀደም ያውቃታል። ከማወቅም አልፎ የቅርብ ጓደኞቹ እህት በመሆኗ በየአጋጣሚው ሊያገኛት ሲሞክር ነበር። ይህ ስሜቱ ግን እንዳሰበው ሳይሳካና የሃሳቡን ሳይፈጽም ጊዜያትን አስቆጥሯል።
ደረጀ በዚህ ምሽት ልጅቷን ከዚህ ሰው ጋር እያያት መሆኑ እያበሸቀው ነው። በእርግጥ ኑሮዋ ሴተኛ አዳሪነት ስለመሆኑ ያውቃል። ዛሬም ይሁን ቀድሞ ስለገንዘብ ስትል ገላዋን አሳልፋ እንደምትሰጥ አልጠፋውም። አሁን ላይ የሚያየው ግን የነበረውን እውነት ሁሉ እንዳያምን እያደረገው ነው።
ምሽቱ እየገፋ ነው። ጨዋታውም በሙዚቃ እንደደመቀ ቀጥሏል። የደረጀ ንዴትና ቁጭትም ከነበረው በላይ አይሎ ውስጡ በትኩሳት መጋል ጀምሯል። አሁን ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖታል። ይህን ብሽቀቱን ለማርገብ ደግሞ ከመካከላቸው ገብቶ ሊረብሻቸው እየሻተው ነው። ሃሳቡን ወጥኖ ዳር ከማድረሱ በፊት እግሮቹ የፈጠኑት ደረጀ እጁን ለቦክስ እንደጨበጠ ልጅቷን ጎትቶ ከነበረችበት ለያት። ወዲውም ከእጁ እንዳስገባት ለማሳወቅ ደረቱን ነፍቶ የሚመጣውን ሁሉ ለመጋፈጥ ወደፊት ተንደረደረ።
አብሯት የነበረው ወጣት የሆነውን ባየ ጊዜ በንዴት ጦፈ። በፍጥነት ተንድርድሮም ምርኮውን ሊያስመልስ ተገላገለ፤ ሙከራው ግን በቀላሉ አልተሳካም። በመጣበት ፍጥነት የሚገታ ኃይል ወደነበረበት ሲመልሰው አፍታ አልቆየም። እንዳሰበው መሆን ያለመቻሉ ያበሸቀው ወጣት ኃይልና ጉልበት አክሎ ከእጁ የነጠቀውን ባላንጣ ለመፋለም ወደፊት ተንደረደረ። ሁለቱ አንገት ለአንገት ለመያያዝ ጊዜ አልፈጁም። ግርግሩን ያዩ ከመሀል ሲገቡ ለጊዜው የሁለቱ ጎረምሶች ጠቡ በርዶ ጋብ ያለ መሰለ። ጥቂት ቆይቶ ግን ደረጀ ልጅቷን ይዞ ለመሄድ ሲዘጋጅ ብጥብጡ አይሎ ነገሩ ተባባሰ።
አሁን ከመሀል ገብተው የገላገሉ ሁሉ ወደነበሩበት ተመልሰዋል። ልጅቷን የተነጠቀው ወጣትም ነገሩን ተወት አድርጎ ለመረጋጋት ሞክሯል። ሁኔታውን ያስተዋለው ደረጀ ያሰበው እንደተሰካ ሲረዳ ወጣቷን በስድብ እያዋከበና በጥፊ እያዳፋ ይዟት ለመውጣት ሞከረ። ድርጊቱን ያስተዋሉ በሁኔታው ቢገረሙም እንደቀድሞው መሀል ገብተው መገላገልን አልሞከሩም። እሱም ቢሆን ይህን ማወቁ የልብ ልብ እንዲሰማው አድርጎታል። ከልጅቷ ጋር የነበረው ወጣት ግን ይህን አይቶ መታገስ አልቻለም።ድርጊቱን እንዲያቆምና ከሁኔታው እንዲታቀብ ሊያስገድደው ሞከረ። ደረጀ ግን ምክንያቱን ከቀድሞው ጠብ ጋር አሳቦ ዳግም ለነገር ተዘጋጀ። ይባስ ብሎም ልጅቷን እየደበደበ ሁሉን ሊያደርግ እንደሚችል በገሀድ አሳየው።
የወጣቱ ትዕግስት ተሟጧል። ከሁለቱ ቅራኔ ይልቅ ደረጀ አሁን እየፈጸመው ያለው ድርጊት ይበልጥ አናዶታል። እሱ ሁሌም ቢሆን የሴትን ልጅ ጥቃት አይሻም። አሁን ደግሞ ዓይኑ የሚያሳየውን እውነት አይቶ ማለፍ አልተቻለውም። ደረጀ ወጣቷን ከቡና ቤቱ እያንገላታ ይዟት ሲወጣ ከኋላው እየተከተለ ሊያስጥላት ሞከረ። በሁኔታው እንደማይቻል ሲያውቅ ግን ይበልጥ እንዲሰማው አድርጎ የስድብ ናዳ ያወርድበት ያዘ። ወጣቱ ደጋግሞ የሚናገረው ሁሉ ፈጽሞ ሊያረካው አልቻለም። ጠያፍ ስድቦችን ጭምር እያከለ መሳደቡን ቀጠለ።
ደረጀ ስድቡን በሰማ ቁጥር በልጅቷ ላይ የሚሳርፈውን ጡጫ አበረታ። ለነገሮች ሁሉ ምክንያት መሆኗን እያስታወሰም ወቀሳን ከዱላ አጣምሮ አንገላታት። አሁንም ከበስተኋላው የሚሰማው ስድብ ያለመቆሙ እያናደደው ነው። ዳግመኛ ፊቱን የመለሰው ደረጀ ከወጣቱ ጋር ለመያያዝ ጊዜ አልፈጀም። ሁለቱም በስካር መንፈስ ቢዳከሙም ዳግመኛ ለመታገል የሚተርፍ ጉልበትን አላጡም። አሁን ግን በአጠገባቸው ደርሶ በግልግል የሚለያይ ጠንካራ ሰው አልነበረም።
ወጣቷ በሁለቱ መሀል ዳግመኛ የተፈጠረውን እያስተዋለች ቢሆንም ምንም ለማድረግ አልተቻላትም። ተደባድበው እስኪጨርሱ ከማየት የዘለለም የመገላገሉ ሙከራ አልነበራትም። ደረጀ ድንገት ተንደርድሮ የገጠመው ወጣት እምብዛም አልታገለውም። ጥቂት ቢውተረተርም ባሳረፈበት ከባድ የቦክስ ምት ራሱን መቆጣጠር አልቻለም። ለምላሹ እጁን ለመሰንዘር ሲሞክር መላ ሰውነቱ ዝሎ ጉልበቱ ተሸነፈ። ላለመውደቅ እየጣረ ጠበኛውን ለመያዝ ሞከረ። አልቻለም። ያሰበውን ዳር ከማድረሱ በፊት የኋልዮሽ ወድቆ በቁመቱ ተዘረጋ።
ደረጀ የወጣቱን መውደቅ እንዳየ የሰነዘረውን እጁን ሰብስቦ ወደ ልጅቷ ተመለሰ። አሁን ተቀናቃኝ ይሉት የለውም። የሚሰድብ የሚቃወመውን አሸንፎ ወደፊት እየተራመደ ነው። ከፊቱ ደግሞ ሌላ ግዳይ ይጠብቀዋል። ያሻውን ለመፈጸም የእሱ መመኪያ አሁንም የወንድነት ጉልበቱ ብቻ መሆኑን ተማምኗል።
ወጣቷን ወደ ጨለማው መንገድ ይዟት ሲገባ መደብደቡን አልተወም። አሁን ሴትነቷ በእሱ ቁጥጥር ስር ሆኗል። እንደቀድሞው ለመጮህና እርዳታ ለመጠየቅ ብትሞክር የሚደርስላት አይኖርም። ጨለማውና ጉልበቱ አግዘውት ያሻውን ከፈጸመ በኋላ በነበረችበት ትቷት ወደመንገዱ ሲያመራ ለቅሶና ልመናዋን ከምንም ሳይቆጥር ነበር።
ደረጀ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሊታገለው ከሞከረ ሰው ጋር ተጋጭቶ እንዳሸነፈው ያውቃል። ስለሱም ቢሆን የሚሰማው ቁጭት የለም። በእሱ ዕምነት ሁሉም ከእጁ የወደቁት በራሳቸው ጥፋት በመሆኑ «ይገባቸዋል» ባይ ነው።
ጨለማውን እያሳበረ የሰፈሩን መንገድ ሲጀምር ፈርሀትና ድንጋጤ አልተሰማውም። የእሱ ፍላጎት ከቤቱ ደርሶ ቀሪውን ሌሊት በዕንቅልፍ ማሳለፍ ብቻ ነው። በሩን ከፍቶ አልጋው ላይ ሲጋደም ያደረገውን ሁሉ መለስ ብሎ አሰበው። አሁንም ግን አዕምሮው ጥፋተኛ ያለመሆኑን ሹክ አለው።
ደረጀ ማለዳ ወፍ ሲንጫጫ ከዕንቅልፉ ተነሳ። የትናንቱ የምሽት ቆይታ ያሳደረበት ድካም በወጉ ባይለቀውም ከቤቱ መራቅ ፈልጓል። ጥቂት ተራምዶ ከአንድ ስፍራ ሲደርስ ግን አስደንጋጭ የሚባል ወሬ ለጆሮው ደረሰ። ትናንት ማታ ከእርሱ ጋር የተጣላው ወጣት ከወደቀበት ያለመነሳቱን ሰማ። ሆስፒታል ሳይደርስ ሕይወቱ ማለፉን ተከትሎም ፖሊስ ገዳዩን ለማግኘት መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን ተረዳ።
ደረጀ ጉዳዩን ያወቀው እንደሌሎች ሰዎች ቢሆንም በድንጋጤ እየተዋከበ ወደቤቱ ተመለሰ። አፍታ ሳይቆይም እየተጣደፈ ወጥቶ በድብቅ ከአካባቢው ራቀ። የሆነውን ሁሉ መለስ ብሎ ሲያስበው ወጣቱ ላይ ያሳረፈው ቦክስ ለሞት እንደማያበቃው አመነ። ያም ሆኖ ጉዳዩ ከእሱ እንደያማልፍ ሲገባው ያሰበውን ለማድረግ ወሰነ።
ዱባይ የምትኖረውን እህቱን ደውሎ ያጋጠመውን ሁሉ ነገራት። እህት ከችግሩ ለመዳንና ከአካባቢው ርቆ ለመሄድ ገንዘብ እንደሚስፈልገው ሲነግራት አላንገራገረችም። የጠየቀውን 20 ሺ ብር ፈጥና ላከችለት።
ደረጀ ገንዘቡ ከእጁ እንደገባ ውሎ አላደረም። ወደ ድሬዳዋ ለመሄድ ጓዙን ሸክፎ ለመንገድ ተዘጋጀ። ያለምንም ስጋት ካሰበው ያደረሰው መኪና ከከተማው እንዳገባው ከአንድ ሆቴል አልጋ ተከራይቶ ለቀናት ራሱን ሸሸገ። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ወደ ጂቡቲ የሚያደርሰውን ዕድል አመቻቸ። ቀኑ ደርሶ ጂቡቲ እስኪገባም ከማንም ሳይገናኝ ድምጹን አጥፍቶ ከረመ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ወንጀል መፈጸሙን ካወቀበት ጊዜ አንስቶ ተጠርጣሪውን ለመያዘ ክትትሉን ጀምሯል።ግለሰቡ ያለበት ቦታ ጥቆማ ስለደረሰውም ከድሬዳዋ ፖሊሶች ጋር በትብብር ለመስራት የሚስችለውን ቅንጅት አጠናክሯል። ፖሊስ የፍርድቤት የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ መረጃዎችን ለማግኘት የሚረዱትን አጋሮች በመያዝ ነበር። በምክትል ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የሚመራው ቡድን መረጃዎችን ሰንዶ ወደስፍራው ሲያመራም በተለመደው ፖሊሳዊ ጥንቃቄ ተዘጋጅቶ ነበር።
በኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ጋር በነበረው የትብብር ሂደትም ተፈላጊው ከሀገር ወጥቶ እንዳይሄድ ለማድረግ እገዛው መልካም ሆነ። ፖሊስ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ተጠርጣሪው ድሬዳዋ «መጋላ ጨብቱ›› ከሚባል አካባቢ እንደሚገኝ ደረሰበት። በተገኘው መረጃ ተመርቶና ከስፍራው ደርሶ ክትትሉን የጀመረው ፖሊስ ግለሰቡ ከተባለው ቦታ እንደሌለ በቀናት ቆይታው አረጋገጠ።
በመጨረሻም
አሁን የፖሊስ ድካም ፍሬ መያዝ ጀምራል ተፈላጊው ከአካባቢው ሳይርቅ ወደጂቡቲ ለመሻገር እየተዘጋጀ መሆኑ ተደርሶበታል። የደዋሌና የአዲስአበባ ፖሊሶች ባደረጉት ብርቱ ክትትልና ፍለጋ ግን ተፈላጊው ደረጀ እንዳሰበው ድንበር ሳይሻገር በቁጥጥር ስር ውሎና በካቴና ታሰሮ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደረገ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
መልካምስራ አፈወርቅ