ከሠላማዊና ከሕጋዊ ትግል ውጭ የሚከናወኑ ተግባራት ከሕገ መንግሥቱና ከምርጫ ሥርዓቱ ያፈነገጡ በመሆናቸው ለሀገር ፈተና ሲሆኑ ይስተዋላል። እነዚህን ማለፍ ደግሞ ቀይ መስመሩን ማለፍ በመሆኑም መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለፖለቲካ ምህዳሩ ሲባል የሚታየው ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነት ‹‹መንግሥት ተዳክሟል›› በሚል የተሳሳተ አካሄድ ፅንፈኝነቱ እንዳይገነግን ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይሞግታሉ።
የአንድን አገር የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን ብቸኛው መንገድ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ነው። “ይህም አካሄድ ወንድም በወንድሙ ላይ እጁን ሳያነሳ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ብቻ ነው አማራጩ” የሚሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሰላማዊ ትግል ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ዋስትና ነው። ምክንያቱም በአንድ አገር የሚካሄደው ትግል ሰላማዊ ከሆነ ሀገር የተረጋጋ ይሆናል ህዝቡም የዕለት ሥራውን ያለሥጋት ያከናውናል።
ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በአገሪቱ መሣሪያ ታጥቀው ትግል የሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ባይባልም በሰላማዊ መድረክ ውስጥ ሆነው ከሰላማዊ የትግል መንፈስ ባፈነገጠ መልኩ የሚንቀሳቀሱና ለመቻቻል፣ ለመግባባትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንቅፋት የሆኑ ፓርቲዎች አሉ ባይ ናቸው። በዚህ የተነሳም በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል የሚያደርጉት ሳይሆኑ ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ትኩረት እያገኙ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች በፖለቲካ መድረኩ ጭምር የበለጠ ተጠቃሚ እየሆኑም ነው፡፡
“ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል ውጭ በኃይል ወይም በጉልበት ፖለቲካ መጓዝ አሁንም ያልተቀየረ ባህላችን ነው” የሚሉት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ናቸው። በጥቅሉ ሕገ መንግሥታዊነትና በምርጫ ሥርዓት መጓዝ መቻል አገሪቱ አሁን ከገባችበት አጣብቂኝ ለመውጣት ቁልፍ ሚና ስላለው፤ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው ሂደት ተቀባይነት ያለው እና ለወደፊት ፖለቲካውን የሚያጎለብት በመሆኑ በአጽንኦት ሊሠራበት የሚገባ መሆኑንም ያመላክታሉ።
አቶ ልደቱ ‹‹በሰላማዊና በህጋዊ ትግል ውስጥ ያለው ኃይል ቦታና ተሰሚነት ሲያጣ፤ በአንፃሩ በሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ስም ፅንፈኛነት እየተጠናከረ ሄዶ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፤ የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል እስከ መንጠቅ ሊደርስም ይችላል፤ ይህን በተግባር ያየነው አደጋ ነው›› ይላሉ፡፡ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ያሳስባሉ። በመሆኑም አሁን በአገሪቱ የሚታዩት ችግሮች ከሰላማዊና ከህጋዊ ትግል በስተጀርባ የሚከናወን ከመሆኑ ባለፈ መንግሥትም ጉዳዩን እሹሩሩ ከማለት ወጥቶ የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንዳለበት ያስገነዝባሉ።
ከሰላማዊና ከህጋዊ ትግል ጀርባ የሀሳብ ልዩነቱ በተለይ በዜግነት ፖለቲካና በብሔር ፖለቲካ መካከል ያለው መካረር ፖለቲካው ውጥረት ውስጥ እንዲገባና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዳይጓዝ በማድረጉ አገሪቱ ቅርቃር ውስጥ እየከተታት ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው፤ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም የሚያስማማ የጋራ ስምምነት መኖር እንዳለበት ይገልፃሉ። በተለይም በመሰረታዊ ሕገ መንግሥታዊ እና ከምርጫ ሥርዓት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚገባ መሆኑንም ያሰምሩበታል። የሚታዩት አደጋዎች ሥልጣንን የመያዝ ጉዳይ በሕግ እና በሰላማዊ መንገድ ካልሆነ ለሀገር ፈተና እየሆነ ህዝብን ሥጋትና ፈተና ውስጥ እያስገባ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ አቶ ናትናኤል አባባል ዛሬ ዛሬ ሕገ መንግሥታዊነት እና የምርጫ ሥርዓትን አስጠብቆ መጓዝ ለኢህአዴግ ብቻ የተተወ ጉዳይ ይመስላል። ይሁን እንጂ ፓርቲዎች ከፅንፈኝነት ርቀው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ትግል እንደሚያደርጉ የገቡትን ቃል ሊተገብሩ ይገባል ይላሉ።
አቶ ናትናኤል ‹‹አሁን መጣ የምንለው ለውጥ ሁሉንም የአገሪቱን ችግሮች በአንድ ጀንበር የሚቀርፍ አይደለም። በሂደት የሚፈቱ ናቸው፤ መጀመሪያ የተረጋጋና የሰከነ ፖለቲካ በሰለጠነ መንገድ እየተካሄደ መለወጥ ያለባቸውን እና ያላየናቸውንም በመወያየት ልንፈታ እንጂ ፅንፈኛ የሆነው አካል ተነስቶ የበላይ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም” ይላሉ። ምክንቱም ይህ አካሄድ ለአገር አደገኛ ስለሆነ ነው።
“አንዳንድ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥታዊና የምርጫ ሕጉን ተከትለው እየተጓዙ አይደሉም” ሲሉ የፕሮፌሰሩን ሐሳብ የሚያጠናክሩት አቶ ልደቱ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት አክራሪና ፅንፈኛ መሆን ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ አደገኛ መሆኑን ይጠቁማሉ። ፅንፈኝነቱ በዋናነት ከብሔርተኝነት አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። ይህ አስተሳሰብ በተፈጥሮው ወደ ቅራኔ እና ግጭት ከመውሰዱ ባለፈ ኢ- ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ አገሪቱን ወደ መረጋጋት የሚወስድ አይደለም።
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማመን ፖለቲካችን ይሻሻላል ብሎ ተስፋ ከማድረግ ውጭ ኢህአዴግን እንደ ኢህአዴግ ማመን የሚቻልበት ሁኔታ የለም። መንግሥትነትን በሃይል ለመያዝ የሚታሰበው እብደት ቀርቶ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ማካሄድ አለብን። ከሰላማዊና ከህጋዊ ትግል ውጭ የሚስተዋለው ቀይ መስመር የማለፍ ገመናችን አልተለወጠም።›› በማለት ፕሮፌሰሩ ከረር ያለ ትችታቸውን ይሰነዝራሉ።
ፖለቲካው ላይም ብሔራዊ መግባባት ያልተፈጠረ መሆኑን የሚያመላክቱት ፕሮፌሰር መረራ፣ ሁሉም የራሱን ህልም ይዞ በመጋለብ ላይ ነው ይላሉ። በዚህም አገሪቱ መንታ መንገድ ላይ በመሆኗ ሁሉንም ሊያገናኝ የሚችልና ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ አስተሳሰብ ሊፈጥር የሚችል እንዲሁም የመጣው ለውጥ በምን መንገድ መመራት እንደሚገባው የሚገልፅ ፍኖተ ካርታ ሊኖር ግድ ይላል።
ፅንፈኛ ሃይሎች ነጥብ ማስቆጠር የሚፈልጉት በሰላማዊና በህጋዊ ትግል የሚጓዙትን ዋጋ እና ክብር በማሳጣት ሚናቸውን አሳንሶ በማቅረብ እንደ አድርባይ፣ ፈሪ እና ተለጣፊ አድርጎ በማቅረብ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ልደቱ ናቸው። በዚህም የራስን ተወዳጅነት እና ተቀባይነት ለማስፈን የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውን የሚጠቁሙት አቶ ልደቱ፣ ይህም በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚጓዙ ፓርቲዎች ብዙ ማህበራዊ መሰረት እንዳኖራቸውና ፈተና ውስጥ እንዲገቡ እያደረጋቸው መሆኑን ያስገነዝባሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ‹‹በተሳሳተ አመክንዮ ፅንፈኞችን በመደገፍ ብዙ የሚገኝ ጥቅም አለ ተብሎ አይታሰብም። በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊነት፤ የሕግ የበላይነት እንዲሁም የሐሳብ የበላይነት ካልሰፈነ፤ በምክንያት የሚያምኑ ፓርቲዎች አክብሮትና ቦታ ካላገኙና ህብረተሰቡ ፅንፈኝነትን መጠየፍ ካልቻለ በመጪው ጊዜ የአገራችንን ፈተናዎች ስለሚያበዛው የምንበታተንበትን ጊዜ ያቀርበዋል›› በማለት ያስጠነቅቃሉ።
አቶ ናትናኤል አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች በተጠና ሁኔታ ፅንፈኛ ሆነው ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል ባፈነገጠ ሁኔታ እየሠሩ ነው ብለዋል። ይህም ከሕጋዊና ከሰላማዊ ትግል ውጭ ያሉ ፅንፈኛ አካሄዶችን መንግሥት በሃይል እንዲያስታግስ የሚያስገድድ በመሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲጠብ ያስገድዳል።
ፕሮፌሰር መረራ መፍትሄ ያሉትንም መንግሥት ሁለት ስትራቴጂ ቢከተል ጥሩ ነው። አንደኛው አገሪቷን ወደ ብሔራዊ መግባባትና እርቅ መውሰድ፤ ሁለተኛው ሠራዊቱ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ አገራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት በማለት ጠቁመዋል።
አቶ ናትናኤል በበኩላቸው ማህበረሰቡ ከሰላማዊና ከሕጋዊ ትግል ውጭ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎችን መቃወምና መታገል የሚገባው መሆኑን ያመላክታሉ። የፖለቲካ ኃይሎቹም በሰላማዊ መንገድ ትግል ለማድረግ በገቡት ቃል መሰረት እንዲጓዙ ህዝቡ ሳይታክት ሊያስታውሳቸው የሚገባ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
አስተያየት ሰጪዎቹ ያለውን የለውጥ ዕድል በአግባቡ መያዝ ካልቻልን ወደማንወጣው አዘቅት ውስጥ እንገባለን ሲሉ ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ። ወቅቱ የፖለቲካ ኃይሎች በኃላፊነት የሚንቀሳቀሱበት ሊሆን ግድ ነው። አለበለዚያ ሥልጣንን በምርጫ የማግኘት ዕድል ቀርቶ ሥርዓት አልበኝነት እንዳይነግስም ሌላው ሥጋታቸው ነው።
ሀብታሙ ስጦታው