አዲስ
አበባ፡- በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4 ነጥብ 32 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ
2 ነጥብ 67 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱ ተገለፀ።
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙ ኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደገለፁት፤ ቅናሽ የታየበት ምክንያት፤ የምርት አቅርቦትና ጥራት ችግር፣ የሕገወጥ ንግድ መበራከት፣ የዓለም ገበያ ዋጋ መዋዠቅ፣ የኃይል አቅርቦት እጥረት እና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መከሰት ናቸው።
ለአገሪቱ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ ድርሻ ያለው የቡና ምርት በበጀት ዓመቱ የዕቅዱን 70 በመቶ ቢያሳካም፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የዘጠኝ በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። የዕቅዱን ስምንት በመቶ ብቻ ያሳካው የወርቅ ምርት ከፍተኛ ማሽቆልቆል የታየበት ተብሎ ተመዝግቧል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በንፅፅር የተሻለ ገቢ የተገኘው በግብርና ምርቶች ላይ ነው። የጥራጥሬ እህሎች፣ ሰሊጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘበት የቅባት እህሎች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከ75 እስከ 90 በመቶ የተሻለ ገቢ ያስገኙ ናቸው። የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና መጠጥ ምርቶች፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች የዕቅዳቸውን ከ50 እስከ 74 በመቶ በማሳካት በመካከለኛ ደረጃ የተቀመጡ ናቸው።
የግብርና ምርቶች ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት ሲገባቸው ከዕቅድ በታች መሆናቸውን የገለፁት አቶ ወንድሙ፤ በግብርና ምርቶች ላይ የጥራት ችግር እንደነበር ተናግረዋል። በግብርና ምርቶች ላይ የግብዓት አጠቃቀም ችግር እና ልማዳዊ አሠራር የአርሶ አደሩን ምርት ጥራት እንዳይኖር አድርጎታል። የተጓተተ የግብይት ሥርዓት መኖሩ ለሕገ ወጥ ንግድና ለምርት ብክነት አጋልጧል።
‹‹የዓለም ገበያ መዋዠቅ አንዱ ችግር ነው›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አገራት የሚፈልጉት የጥራት አይነት የተለያየ መሆኑም ለወጪ ንግዱ መሰናክል መሆኑን ገልፀዋል። በአውሮፓ የሚፈለገው የምርት ጥራትና በአሜሪካ ከሚፈለገው የምርት ጥራት የተለየ መሆኑን አመልክተዋል። የሁሉንም ፍላጎት ማሟላት ስለማይቻል የገበያ መዋዠቅ ያጋጥማል ብለዋል።
በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት ባለፈው ዓመት ያጋጠሙ ችግሮች እንዳይደገሙ እንደሚሠራ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በግብርና ላይ የታየውን የተሻለ አፈፃፀም ማስቀጠልና ሕገወጥ ንግድን መቆጣጠር ለበጀት ዓመቱ የተያዙ ዕቅዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2012 ዓ.ም የበጀት ዓመት 4 ነጥብ 69 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል። ከእነዚህም ውስጥ 70 ነጥብ 8 በመቶ ከግብርና ዘርፍ፣ 21 ነጥብ 7 በመቶ ከማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ 5 ነጥብ 7 በመቶ ከማዕድን ዘርፍ፣ 1 ነጥብ 8 በመቶ ከኤሌክትሪክ አግልግሎትና ሌሎች ምርቶች ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል።
ዋለልኝ አየለ