አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ2012 በጀት ዓመት ዋጋቸው 150 ቢሊዮን ብር የሚገመት 91 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለጨረታ እያዘጋጀ እንዳለ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ትናንት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን አጠቃላይ ሥራ እና የማሻሻያ ርምጃዎች አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ተቋሙ አሠራሩን እያሻሻለ እንዳለና በ2012 በጀት ዓመትም 91 የመንገድ ፕሮጀክቶችን በጨረታ ለማወዳደር እንደተዘጋጀ ገልፀዋል። ከነዚህም ውስጥ እየተንከባለሉ የመጡ፤ በጀት የተያዘላቸውና እንደ አዲስ የሚጀመሩ መኖራቸውን አስታውቀዋል።
በ1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ብር የኮንትራት ዋጋ በቻይናው ሲሲሲሲ ካምፓኒ ጨረታ አሸናፊነት በባህርዳር ከተማ አባይ ወንዝ ላይ ሊገነባ የታሰበው ዘመናዊ ድልድይም የዚህ ዕቅድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የመንገዶች ባለሥልጣን በአዲስ መልክ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ1989 ዓ.ም ወዲህ ሀገሪቱን በመንገድ ኔት ወርክ በማስተሳሰር በልማትና በኢኮኖሚው ዕድገት ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ ኢንጂነር ሀብታሙ ገልፀዋል።
ቀደም ሲል የነበረው የመንገድ ኔት ወርክም 26 ሺ 550 ኪሎ ሜትር እንደነበር የተናገሩት ኢንጂነሩ፣ በሃያ ዓመታት ውስጥ ወደ 120 ሺ ኪሎ ሜትር ማሳደግ እንደተቻለ የገለፁ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት አንፃር ሲታይ ገና መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ተቋሙ በ2011 ዓ.ም ስልሳ ሦስት በመቶ አፈፃፀም እንደነበረው የገለፁት ዳይሬክተሩ ለአፈፃፀሙ ማነስ የሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ፣ የወሰን ማስከበር ሥራ፣ የግንባታ ግብዓት የማግኘት ችግር፣ የፕሮጀክቶች መብዛት፣ የረዥም ጊዜ ሮድማፕ ያለመኖርና እና የኮንትራክተሩ ትኩረት ማነስን እንደምክንያት ጠቅሰዋል። በዚህም አስራ አንድ ፕሮጀክቶች ወሰን በማስከበር ምክንያት መጓተታቸውን እና ዘጠኝ ፕሮጀክቶችም ባሳዩት ደካማ አፈፃፀም ውላቸውን እንዲያቋርጡ የተደረገ መሆኑን አሳውቀዋል።
መንግሥት ባለፉት ሃያ ዓመታት ለመንገድ መሠረተ ልማት በሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ወጪ እንዳወጣ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በነዚህ ዓመታት ለመንገድ ሥራ ጥቅም ላይ የዋለው ገንዘብም 256 ቢሊዮን ብር እንደሆነና ከዚህ ውስጥ 86 በመቶ በመንግሥት ፋይናንስ የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ ለሀገራችን ባለሀብቶችና ዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንዳለ የገለፁት ኢንጂነር ሀብታሙ፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት በነበረው አፈፃፀም 48 በመቶ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በመንገድ ግንባታ ሥራ እንደተሰማሩና በርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በ2012 ዓ.ም ለጨረታ የተዘጋጁት ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ ሲውሉም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ተቋሙ የተጀመረውን ሪፎርም መሠረት በማድረግም በርካታ የማሻሻያ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በዚህም የሥራ ቦታን ለሠራተኛው ምቹ ማድረግ እንደተቻለና የመንገድ ነክ አዋጆችንና ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት እንቅስቃሴ ላይ እንዳለም ገልፀዋል።
በመጨረሻም መንገድ የሕዝብ ሀብት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ ቦታዎች የመንገድ ሥራውን የሚያደናቅፉ የኅብተሰብ ክፍሎች መኖራውን ገልፀው፣ መንግሥት የመንገድ መሠረተ ልማትን ለማሟላት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሊደግፉ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በ1943 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን አስር ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች፣ ሁለት የማሰልጠኛ ተቋማትና አንድ የምርምር ማዕከልን የያዘና 3 ሺ 37 የሚሆኑ ሠራተኞችን ያቀፈ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2011
ኢያሱ መሰለ