
አዲስ አበባ፡– ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች 23 ሚሊዮን ዜጎችን ከተረጅነት ማውጣት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለፉት ሰባት ዓመታት የመንግሥት ሥራ እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በ2013 ዓ.ም 27 ሚሊዮን ተረጂዎች ነበሩ። አሁን ላይ 23 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎችን ከተረጅነት ነጻ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያን የሚያህል ለሌሎች መትረፍ የምትችል ሀገር አንዳንዴ ከሷ ካነሱ ሀገራትም ጭምር መለመኗ አሳፋሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሴፍቲኔት መርሃ-ግብር ለመታቀፍ ጥሪታቸውን የሚሸጡ ዜጎች መኖራቸው በጥናት ጭምር ተረጋግጧል። በከተሞች ልጆችን ተከራይቶ እንደሚለምነው ሁሉ ልጆች እየቀያየሩ ስንዴ የሚረዱ ውስን ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በዚህ አደገኛ የሥነ-ልቦና ስብራት ከመሸማቀቅ ይልቅ እንደ ክብርና ጌጥ መቁጠራችን፣ ደፍረን ልንተግብረው የማይገባውን ጉዳይ በነፃነት በአደባባይ ማድረጋችን ትልቁ ስብራታችን ነው ብለዋል።
እንደ ሥራ ማስኬጃ በጀት የተረጂውን ቁጥር ጨምረው በሌለ ተረጂ ያገኙትን ስንዴ የሚሸጡ አመራሮች መኖራቸውንም አብራርተዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በመጀመሪያ አካባቢ የሚረዱ ሰዎች ማታ ነጠላ ተሸፋፍነው ተደብቀው ርዳታ ይወስዱ ነበር። አሳፋሪ ስለነበረ ኋላ ላይ ሲነጋጋ ጀመሩ። አሁን ቀን ላይ ብቻ ሳይሆን ለምን ዘገየ ልክ እንደ ደመወዝ፤ ርዳታ ይምጣ እንጂ፤ ኪሎ ይጨመር እንጂ የሚለው ጉዳይ እንደ መብት በገሃድ የሚነገር፣ የሚሠራ ጉዳይ ሆነ።
አንዳንዱ አካባቢ በተለምዶ እኛ ሀገር አባት ለልጁ ሌላውን ሰው ልጅ ሲጠይቅ የሚጠየቁ ጥያቄዎች ነበሩ። ሥራ አለው ወይ፤ ባህሪው፣ ገቢው ይባላል። አንዳድ አካባቢ ሴፍቲኔት ታቅፏል ወይ የሚልም ጥያቄ መመዘኛ ሆኗል። ሰው ልጁን ለመስጠት ባልየው በሴፍቲኔት የታቀፈ ከሆነ ሊሰጥ አልያ ደግሞ ሊከለክል ማለት ነው። ይህም ስብራቱና የባህል ውድቀቱ የደረሰብትን ደረጃ የሚያመላክት እንደሆነ ገልጸዋል።
ልጆቻችን በታሪክ እንጂ በተግባር ይህን ስብራት ማየት የለባቸውም ያሉት ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ተረጂነትን ማውረስ፣ ልመናንንም ለልጆቻችን ማሸጋገር የለብንም። ከተረጂነት መውጣት ብቻ ሳይሆን ረጂ ለመሆን በትልቁ ማሰብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
ፖለቲካን የሚያተረማምሰው እና ሕዝቡን የሚያወናብደው የልመና እና ርዳታ ገንዘብ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የሚመጣው ርዳታ ሲነገር ብዙ ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም ትልቁ ትርፉ ስብራት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ያለንን አቅም የሚገታ፣ ሌሎች በውስጥ ጉዳያችን ገብተው የሚፈተፍቱበት አደገኛ ስብራት መቆም እንዳለበትም አመላክተዋል።
ችግሩን ከመሠረቱ ለመቅረፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ርዳታን በማቆም ተረጂን ለመቀነስ የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጦ የሚሠራ ቡድን መደራጀቱን ጠቅሰው፤ ሕዝቡ ከተባበረ፣ አቅማችንን አስተባብረን አሁን በጀመርነው አካሄድ ከሠራን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ከሌሎች ርዳታ እንላቀቃለን ብለዋል።
እስካሁን የተገኙ ውጤቶች እቅዱ ሊሳካ እንደሚችል የሚያመላክቱ መሆናቸውን አንስተው፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛዋ ስንዴ አምራች ሀገር ሆናለች። አንደኛ መሆን ብቻ ሳይሆን በአህጉሪቱ ሁለተኛ ስንዴ አምራች የሆነችውን ግብጽን በሦስት እጥፍ እንደምትበልጥም አብራርተዋል።
ባለፉት ዓመታት ስንዴ ከውጭ ለማስገባት አንድ ቢሊዮን ዶላር ይወጣ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ስንዴ ከውጭ አላስገባንም ብለዋል።
ፈጣሪም ዝናቡን በወቅቱ በመለገስ ለጥረታችን ምላሽ እየሰጠን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የተሰጠንን መጠበቅ ከቻልን እና ጠንክረን ከሠራን ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በተግባር መታየቱንም አስገንዝበዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም