አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች የሆኑት አዴፓና ህወሓት ያሉባቸውን አለመግባባቶች ተቀራርበው በመፍታት የታገሉለትን አላማ እውን ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ሁለቱ ፓርቲዎች የታገሉበት ዋና አላማ ለህዝባቸው ልማት፣ ሰላምና፣ ዴሞክራሲን ለማምጣት ቢሆንም ይህ አላማ በተሟላ መንገድ በሁለቱ ህዝቦች ላይ አልተሳካም። በመሆኑም አላማቸው እስካልተሳካ፣ በጉዞ ሂደት ላይ አስካለ ድረስ በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት በመፍታት ተጨማሪ የጋራ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል ስላለው አለመግባባት ተጠይቀው «ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዴፓና ህወሓት በመግለጫ መነጋገር ከጀመሩ በኋላ ወዴት እያመራን ነው የሚል ሥጋት እንደተነሳ እኔም አውቃለሁ» በማለት ገልፀዋል።
አያይዘውም አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ማንኛውንም እርምጃ ሲወስድ እንደ መስፈርት መያዝ ያለበት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች መኖራቸውን አመልክተው፤ የመጀመሪያው ፖለቲካል ሞራሊቲና ፖለቲካል እሴት መሆኑን ጠቁመዋል። ይህን እርምጃም በመውሰዱ ከፖለቲካል እሴት አንፃር ምን ልማትና ምን ጥፋት ሊያመጣ ይችላል ብሎ ማሰብ የሚጠበቅበት መሆኑን አስረድተዋል። በሁለተኛ ደረጃም ሊመጣ የሚችለውን ውጤት ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድም የህወሓት መግለጫ፣ ድርጊትና ማንኛውም እንቅስቃሴ ለትግራይ ህዝብ ከዚያም አልፎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር የሚመዘን መሆኑን አብራርተዋል። «አዴፓም የሚያወጣቸው ማንኛውም መግለጫዎች ለአማራ ህዝብ ከዚያም አልፎ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንፃር ይመዘናል። ከዚህ አንፃር የመግለጫ ምልልሱን እራሱን አስችሎ ማየት ይኖርብናል። እንደ ባህሪይ ግን ብዙ አዲስ ባህሪይ አይደለም» በማለት ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም አዴፓ እና ህወሓት በመግለጫና በይፋ አይነጋገሩ እንጂ ከዚህ በባሰ በዝርዝርና ጠንከር ባለ መንገድ በመድረኮቻቸው ይነጋገሩ እንደነበር ያመለከቱት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ አሁን አጠቃላይ የፖለቲካ አውዱ በመቀየሩ ማንኛውም ነገር መነገር ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ መምጣቱን አስገንዝብዋል። «አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ አላማ የራሱ ሀሳብ አለው። ያን ፍላጎቱና ያ ሀሳቡን ለማሳካት አጋር ሊሆን የሚችል ሀሳቡን ተጋርቶ ወደፊት ድጋፍ ሊሰጠው የሚችል አጋር ይፈልጋል» ብለዋል። በዚህም ህወሓትና አዴፓ ከዚያም ደኢህዴን በኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲዎች ሁሉ በላይ በትብብር በወንድማማችነት ስሜት አብረው መታገላቸውን አስታውሰዋል።
«እንኳን ፖለቲካ ውስጥ በሌላ መስክም ስንሳተፍ እንደዚ አይነት ንትርኮች ያጋጥማሉ። አንዳንዴ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግሮቻቸውን ደብቀው ይነጋገራሉ። ለህዝብ ቢገለጥ እምብዛም ጥቅም የሌለው ከሆነ አንዳንዴ ደግሞ በአቋማቸው ህዝባቸውን ለማሰለፍና ለማስከተል ግልፅ ያደርጋሉ። የፓርቲዎቹ መግለጫ በዚያ መንገድ ባይሆን ይመረጥ ነበር» በማለት ተናግረዋል። እነዚህ ንትርኮች በሰለጠነ መንገድ በድርድርና በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝብዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በህወሓትና በአዴፓ መካከል የተፈጠረውን ምልልስ እንዴት እንፍታው ብለው መፍትሄ አምጪ ንግግር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ሌሎች የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ለሁለቱ ፓርቲዎች መድረክ ፈጥሮ ሀሳቦቻቸውን እንዲያንሸራሽሩና እያንዳንዱ ቡድን ላይ የታየውን ጥፋት እራሱ ሂስ ማድረግ እንዲችል ዕድል መፍጠር ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ከተቻለም ይበልጥ መቀራረቡ ይመጣል፤ መፍትሄ ማስቀመጥ ከተቻለም በህዝቦች መካከልም ሆነ በፓርቲዎች መካከል ያሉ ልዩነቶች ይፈታሉ። ይህንን ማድርግ ካልተቻለ ግን ጉዳዩ እየተካረረ ይመጣል።
ማህሌት አብዱል