የባሕር በር አስፈላጊነት በንግዱ ማኅበረሰብ ዕይታ

ኢትዮጵያ በዓመት ከአንድ ነጥብ አምስት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ እንደምታወጣ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያሳያሉ። የባሕር በር መኖር ምርቶችን በተፈለገው መንገድ ለመላክ እና ለማስገባት ያለው ጠቀሜታ እጅግ በጣም የጎላ እንደሆነ ይሄው የሀገራችን የገቢ ወጪ ንግድ ሁኔታ እማኝ ነው።

ኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛቷ እና ከፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገቷ አንጻር የወጪ ገቢ ንግዷን ለማሳለጥ የእኔ የምትለው የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት በንግድ ሥራ የተሰማሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፤ ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ በማሰብ ጭምር ሃሳባቸውን ያካፍላሉ።

ኢትዮጵያ በታሪክ የባሕር በር ባለቤት የነበረች ቢሆንም በጥቂት ሰዎች ውሳኔ ነው ላለፉት 30 ዓመታት የባሕር በር አልባ ሆና የዘለቀችው የሚሉት በኮንስትራክሽን እና በሪል እስቴት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩት ኢንጂነር ጀብል ጀማል ናቸው። 130 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ የባሕር በር ሳያገኙ መኖር ከባድ እንደሆነም ይገልጻሉ።

ምክንያቱም 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ወደ ውጭ የምትልከው እና ከውጭ የምታስገባው ምርት እጅግ በጣም ብዙ ነው። በተጨማሪም ከዓለም ጋር የምትሠራ ሀገር እንደመሆኗ የባሕር በር እጅግ በጣም ያስፈልጋታል ሲሉ ያስረዳሉ። በዚህ ረገድ ደግሞ እንደ ዜጋ ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ መወጣት ይጠበቅብናል የሚሉት ነጋዴው ዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ ችግራችንን ሊያይ ይገባል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውልደት ምጣኔ ካለባቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን በመግለጽ፤ የሕዝብ ቁጥሩ አሁን ካለበት በጥቂት ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ሊጨምር ይችላል። ከዚህ አንጻር የባሕር በር ማግኘቱ ሀገር ለሚረከበው ወጣት ዜጋ እጅግ በጣም ኢኮኖሚያዊ፣ የደኅንነት እና ሌሎች ጠቀሜታዎችም እንደሚኖረው ያስረዳሉ።

አሁን ላይ በንግድና በሌሎች ጉዳዮች የዓለም ትስስር የበለጠ ተጠናክሯል የሚሉት ኢንጂነር ጀብል፤ ከንግድ አንጻር በርካታ ነገሮችን በአንዴ ወደ ዓለም ሀገራት ለማጓጓዝ ከአየር ይልቅ የሚመረጠው የባሕር ትራንስፖርት እንደሆነ በመግለጽ፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።

በአውቶሞቲቭ ዘርፍ የተሰማሩት ሌላኛው ነጋዴ አቶ ተስፋዬ ገብረኪዳን በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የባሕር በር አለመኖሩ እስከአሁን ድረስ እንደ ሀገር እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። በመሆኑም መንግሥት በዲፕሎማሲው መንገድ ለማግኘት እያደረገ ያለው ጥረት ሊቀጥል ይገባል።

ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት የባሕር በር መኖሩ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ በተለይ በንግድ ዘርፍ እንደተሰማራ ግለሰብ ምርቶችን እንደ ልብ በማስገባት እና በማስወጣት የንግዱን ዘርፍ ለማነቃቃት ሚናው የጎላ በመሆኑ፤ የባሕር በር ማግኘቱ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

እሳቸው እንደሚናገሩት፤ በጣም በርካታ ምርቶች በመርከብ ይጓጓዛሉ፤ ከዚህ አንጻር ደግሞ አሁን ምርቶችን ለማስገባት እና ለማስወጣት እየተጠቀምን ያለነው የጎረቤት ሀገራትን ወደብ ነው። እንደ ሀገር የራሳችን የባሕር በር እንዲኖረን መንግሥት የጀመረውን እንቅስቃሴ ቢቀጥልበት መልካምና ወሳኝ ነው ብለዋል።

በባሕር በር ጉዳይ የአሁኑ ትውልድ ፍላጎት እና ተነሳሽነት እንዳለው የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፤ የዛሬው ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገር አዘጋጅቶ ማለፍ ቢችል መጪው ትውልድ እንዳይቸገር ይረዳል ሲሉ ይጠቁማሉ።

የባሕር በር ከማግኘት አንጻር እንደ ሕዝብ ያለውን ችግር ለዓለም ማኅበረሰብ በግልጽ ማስረዳትም ያስፈልጋል። በመንግሥት በኩልም አሁን የተጀመረውን ሥራ ተከታትሎ በዲፕሎማሲ ጥበብ ማስፈጸም ተገቢ ነው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የባሕር በር ነበራት፤ ነገር ግን አሁን ላይ የላትም። ያ ለምን ሆነ ብሎ መወቃቀስ አሁን ላይ እንደ ሀገር የሚጠቅም ነገር አይደለም የሚሉት የአልሙኒየም አስመጪው አቶ አረጋዊ ገብሬ በበኩላቸው፤ ከዘመኑ ጋር መራመድ እንደሚገባ እና ወደፊትን የባሕር በር ለማግኘት ሁለንተናዊ ሥራ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

የባሕር በር አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ ምንም ጥያቄ የለውም ነገር ግን ለማግኘት የሚደረገው እንቅስቃሴ በሰጥቶ መቀበል መርሕ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲያልፍ ማድረግ ይገባል ይላሉ።

መንግሥት በተገቢው መንገድ የባሕር በር ባለቤት ከሆኑ ሀገራት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ላይ የሚደረስበት ሁኔታ ቢፈጠር ለሀገራችን ትልቅ ጥቅም አለው የሚሉት አቶ አረጋዊ፤ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ሀገራትም በምስጢራዊ መንገድ የባሕር በር ችግራቸውን እየፈቱ ነው። እንደ ሀገር ከእነዚህ ሀገራት ትምህርት በመውሰድ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ማስፈጸም ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ይገልጻሉ።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You