የመረዳዳትና የአብሮነት ተምሳሌት የሆነው የአረፋ በዓል

በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ዋነኛው ነው። 1446ኛው የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል በአዲስ አበባ ስታዲየም ሶላት እና ተክቢራን ጨምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ትናንት በድምቀት ተከብሯል።

ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተገኙት ኡስታዝ አሕመድ ሐጂ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የኢድ አል-አድሃ በዓል በሚከበርበት ዕለት ሕዝበ ሙስሊሙ ወደ ሜዳ በመውጣት የኢድ ሰላት ያከናውናል። ከዚህ መልስም የዕርድ ተግባር ያከናውናል።

በዕለቱ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ለሚፈጸመው የዕርድ ተግባርም የዕምነቱ ተከታይ እንደ አቅሙ በሬ፣ በግ እና ፍየል እንደሆነ ጠቁመው፤ ዕርዱ ከተፈጸመ በኋላም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ለቤተሰብ፣ አንድ ሦስተኛው ለጎረቤትና ለዘመድ እንዲሁም አንድ ሦስተኛው ለድሆች የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም በበዓሉ ሥጋ አጥተው ተርበው የሚውሉ እንዳይኖሩ የሚከናወን መሆኑን ይገልጻሉ።

ሙስሊሞች የመስዋዕትነት በዓሉን አረፋ ዕርድ በመፈጸም፣ በጋራ በመጸለይ እና ከፈጣሪ ምሕረትን የሚያስገኙ በጎ ተግባራትን በማከናወን ያሳልፉታል ያሉት ኡስታዝ አሕመድ፤ በዓሉ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና በመረዳዳት የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ይህም በቤተሰብና በጎረቤት መካከል እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ ደስታ እንዲኖር እና መተሳሰብ እንዲጠናከር ያደርጋል ያሉት ኡስታዝ አሕመድ፤ የአረፋ በዓል ሕዝበ ሙስሊሙ የመረዳዳት ባህሉን የሚያጠናክርበት፣ አቅመ ደካሞችን የሚያግዝበት ታላቅ በዓል መሆኑን ነው የገለጹት።

በዓሉን ለማክበር ከጅማ አዲስ አበባ የመጡት ኡስታዝ ሰይድ አደመ በበኩላቸው፤ የበዓሉ ማኅበራዊ ፋይዳ የላቀ ነው። በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዕምነቱ ተከታዮች ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ እንደ መልካም ዕድል የሚጠቀሙበት በዓል መሆኑን ገልፀዋል።

እንዲሁም በተጣሉ ሰዎች መካከል እርቅና ሰላም እንዲወርድ በማስቻል ረገድም የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ትልቅ ኃይል እንዳለው የገለፁት ኡስታዝ ሰይድ፤ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ ልጅና ወላጆች፣ ጎረቤታሞች እንዲሁም በማኅበረሰብ መካከል የተፈጠሩ ያለመግባባቶች ካሉ በአረፋ በዓል ሰሞን ይቅር በመባባል ሰላምን እና እርቅ እንደሚያወርዱ ይናገራሉ።

በዓሉን ስናከብር የእምነቱ አስተምሕሮ በሚያዘው መሠረት አቅመ ደካሞችን በማሰብና ያለው ለሌለው በማካፈል በጋራ ልናከብር ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ሚፍታ ኑራ፤ በበዓሉ ወቅትም የእርስ በርስ ትስስርና አንድነትን የሚያጠናክሩ ዕሴቶቻችንን አጉልተን በማሳየት በደስታ ልናሳልፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡ አቶ ሚፍታ፤ የአረፋ በዓልን ሰላም፣ ፍቅር፣ መተሳሰብንና አንድነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እያከበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌሎች እምነት ተከታዮች መካከል በአንድነትና በመተሳሰብ የምናሳይበት በዓል ነው ሲሉ አቶ ሚፍታ ነግረውናል፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You