አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አጠቃቀም ችግር እንጂ የቦታ እጥረት ባለመኖሩ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ተገቢ የመሬት አጠቃቀም ማኔጅመንት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ እንደገለፁት፤ የአዲስ አበባ ከተማ አሁንም ብዙ ያልተሠራባቸው ቦታዎች አሉ። የመዲናዋ ይዞታ የተገደበ ቢሆንም በአግባቡ ከተጠቀሙበት የሚበቃ መሬት በመኖሩ የከተማ ማኔጅመንትን ተጠቅሞ መዲናዋን መልሶ መገንባት ከተቻለ ለነዋሪዋ ምቹ ማድረግ ይቻላል።
«አዲስ አበባ ሦስት መልክ ያላት ከተማ ነች። በአንድ በኩል ነባር፣ አሮጌ ቤቶች ያሉበት እና ለእንቅስቃሴ የማያመቹ የተጨናነቁ መንደሮችን ይዛለች» ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አዳዲስ መንደሮች እና አዳዲስ ግንባታዎች ያሉበት ቦታዎች እንደሚገኙ አስታውሰዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አሮጌዎቹንም ይሁን በመልሶ ማልማት የተገነቡትን የያዙ መንደሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ሁሉንም አካባቢዎች ባማከለ ሁኔታ ወደላይ የምታድግ፣ በርካታ ህንፃዎች ያሏት፣ የከተማ ግብርናን ያቀፈች እና ፅዱ ወንዞች ያሏት ከተማ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝብዋል። ከተማዋ ለነዋሪዎቿ በሚመች መልኩ እና የትራፊክ ፍሰቱም ባልተጨናነቀ መልኩ በመገንባት ሁሉን አቀፍ ዘመናዊ ከተማ /ስማርት ሲቲ/ እንድትሆን መዋቀር እንደሚገባም አመልክተዋል::
እንደ ኢንጂነር እንዳወቅ ገለፃ፤ <<ስማርት ሲቲ>> የሚባለው በትንሽ ቦታ ተጠቅሞ ህንፃዎችን ወደጎን ሳይሆን ወደላይ በማሳደግ በአንድ ቦታ በርካታ አገልግሎቶች የሚሰጡበት እንዲሁም በተጓዳኝ አረንጓዴ ልማት እና የከተማ ግብርናን የሚተገበርበት ነው። በተጨማሪ የትራፊክ ፍሰቱ ህብረተሰቡን በማይረብሽ መልኩ በዘመናዊ ማኔጅመንት ከሆነ፣ እያንዳንዱን መሬት ለተገቢው ጥቅም ማዋል ከተቻለ መዲናዋን ለነዋሪው ምቹ ማድረግ ይቻላል።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በከተማ መሬት አስተዳደር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ስናፍቅሽ ገዛህኝ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ አዲስ አበባ ላይ ለነዋሪው የሚሆን በቂ መሬት ቢኖርም ለነዋሪው እንዳይበቃ ያደረገው ከፕላን ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ነው። ከተማዋ መሬት ቢኖርም የተጠና እና የታቀደ ፕላን የላትም። በሌላ በኩል ከገጠር ወደከተማ የሚፈልሰው ህዝብ እና የመሬት ወረራ እንዲሁም ፍትሃዊ ያልሆነ የመሬት ሀብት ክፍፍል ለችግሩ አስተዋጽኦ አላቸው። የተለያዩ ቦታዎችን በአንድ ሰው ከተያዙ ለይቶ ለሌላውም ማዳረስ ይገባል። በዋናነትም የመሬት ችግሩን ለመፍታት ግን የተጠና ፕላን በመተግበር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ህንፃዎች ላይ ማተኮር ይጠበቃል።
አንድ ህንፃ ሲገነባ ከምድር በታች ያለውን ለተሽከርካሪ ማቆሚያ ማድረግ፣ የመጀመሪያ ወለሎችን ደግሞ ለንግድ ሥራ በማዋል የህንፃዎች የመጨረሻ ሁለት እና ሦስት ወለሎችን ደግሞ ለመኖሪያነት መጠቀም እንደሚገባም ኃላፊዋ አስገንዝበዋል። ከህንፃዎቹ ጋር ለኑሮ ምቹ የሆኑ አረንጓዴ ልማቶችን እና የመሬት አጠቃቀም በማሻሻል <<ስማርት>> ከተማ የተሰኙትን የአውሮፓውያን አይነት ከተሞች መፍጠር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም