አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ የሚካሄድ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አስታወቁ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት 92 ሺህ የሚደርሱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተጠቁሟል።
ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ትናንት ሲካሄድ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት፤ በቀጣናው ካሉ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት ጎረቤት ሀገራትን በሚጎዳ መልኩ የሚካሄድ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት የሚሰጥ የውጭ ፖሊሲ እየተከተለች ነው። በዚህም አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት ማለት ግን ወዳጆቻችን የጎረቤት ሀገራት ብቻ ናቸው ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግንኙነታችን ቅድሚያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ከዚያም ከቀጣናዊ ቀጥሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትብብርና ትስስሮችን እናጠናክራለን ማለት ነው። ዋናው ጉዳይ እንደ ሀገር ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያስቀደመ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲፕሎማሲው ሥራ ወጥነትን ይጎለዋል በሚል ለቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ ቋሚ ተደርጎ የሚያዘው ሀገራዊና ብሔራዊ ጥቅማችንን ነው። ይህንን ከሚፈልጉ ሀገራት ጋር በጠንካራ ወዳጅነት ለመሥራት ፈቃደኝነቱ አለ። ነገር ግን ወዳጅነት እንዲቀጥል ሲባል ብቻ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸውን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፈን ልንሰጥ አንችልም ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስጠበቅ የምንከተለው ፖሊሲ ያስቀየማቸው ወይንም ቅር ያሰኛቸው ካሉ በዲፕሎማሲ መንገድ ለማስረዳት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፤ ቅር እንዳይላቸው ተብሎ የሚለወጥ ነገር ግን እንደማይኖር አመልክተዋል።
በተጨማሪ ሚኒስትሩ «ለሥራ በተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ ዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጠን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም ከኢትዮጵያ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱ በርካታ ዜጎች አሉ። እነዚህ ዜጎች በጉዞ ላይም ሆነ በደረሱበት ሀገር ሕጋዊ ከለላ ስለማይኖራቸው ችግሮች ያጋጥማቸዋል። እነዚህን ካሉበት ችግር በማውጣት ወደ ሀገራቸው በመመለስ ረገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል ነው ያሉት።
ለምሳሌ በመካከለኛው ምሥራቅ ከምትገኝ አንዲት ሀገር ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች እንዲመለሱ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅትም በየወሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲመለሱ እየተደረገ ይገኛል። በቂ የሚዲያ ሽፋን ባያገኝም ከአፍሪካ ሀገራት ብቻ አንድ ሺህ 600 ዜጎችን ከተለያዩ ቦታዎች ለመመለስ ተችሏል ሲሉ አብራርተዋል።
ይህ ቁጥር ከአጎራባች ሀገራት የተመለሱትን ያላካተተ ነው ያሉት ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፤ በተጨማሪ ከማይናማር ከ600 በላይ ዜጎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደረገ ስምምነት ለሀገራቸው ለማብቃት ተችሏል። በአጠቃላይም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 92 ሺህ የሚደርሱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መቻሉን አብራርተዋል።
ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ቤት ከሚመለሱት ያልተናነሰ ዜጋ ወደ እነዚህ ሀገራት በመቶ ሺዎች ብር ለደላሎችና ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እየከፈለ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ወረዳቸው ሲመለሱ በዚህ ረገድ ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የበኩላቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም