‹‹የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት ቀይሯል›› – ያስሚን ወሃበረቢ

– ያስሚን ወሃበረቢ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ

መንግሥት ሐምሌ 22 ቀን 2016 ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷን ይፋ ካደረገበት ወቅት ጀምሮ በርካታ በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል:: አንዳንዶቹ አስተያየቶችም በማክሮ ኢኮኖሚው ምክንያት መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የፈተና ወቅት እንደሚሆንም በድፍረት የተናገሩ ነበሩ:: ሆኖም ባለፉት 10 ወራት የታየው አፈጻጸም ግን የተባሉትን ስጋቶች ያስወገደ እና ኢትዮጵያም የመረጠችው መንገድ ትክክለኛ እንደሆነ ያሳየ ነው:: የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የማክሮ ኢኮኖሚው አፈጻጸም እንደ ሀገር ይዟቸው የመጣው ትሩፋቶች እና ስጋቶችን በማስመልከት ከንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ያስሚን ወሃበረቢ ጋር የተደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል::

አዲስ ዘመን :- ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ካደረገች በኋላ ለንግዱ ዘርፍ እንቅስቃሴ ምን ምቹ ሀኔታ ተፈጥሯል ?

ወ/ሮ ያስሚን:- ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል:: የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሁለተኛው ምዕራፍ በተሟላ ሁኔታ እየተተገበረ ይገኛል:: በተለይም በንግዱ ዘርፍ በአጠቃላይ የተካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ እና በአኅጉራዊ ደረጃ የሚኖራትን የንግድ ውህደት የሚያጠናክር ሁኔታ ፈጥሯል::

ከዚህ በፊት የሚደረጉ ሙከራዎች ብዙ ጥያቄዎች እየተነሳባቸው በአባልነት ደረጃ በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅትም ጭምር አባል በመሆን ለመሳተፍ አዝጋሚ ሁኔታዎች ነበሩ:: አሁን ግን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ብዙ ጥያቄዎችን መልሷል:: በአኅጉራዊ ደረጃ ባሉ የንግድ ቀጣናዎች ላይ የሚኖረን እንቅስቃሴ በእዛው ደረጃ እያደገ መጥቷል::

ከዚህ መካከል በቅርቡ በኢትዮጵያ የተካሄደው 21 አባላት ያሉትና ኢትዮጵያ አባል የሆነችበትን የምስራቃዊና ደቡባዊ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ማንሳት ይቻላል:: ሰሞኑን በአዲስ አበባ 2ኛው የኮሜሳ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል፤ በመቀጠልም 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ነጋዴ ሴቶች ፌደሬሽን የንግድ ትርኢት እና የንግድ ሳምንት ተስተናግዷል። በአጠቃላይ ወደ 600 ሚሊዮን ሕዝብ እነዚህን አባል ሀገራትን ያካተተ፣ ወደ 260 ቢሊዮን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያቀፈ ገበያ ነው:: በስሩ 14 የሚደርሱ ተቋማት የያዘ ነው::

በመቀጠልም ሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የሴት ነጋዴዎች ፌዴሬሽን ከንግድና ቀጣናዎች ትስስር ሚኒስቴርና በቅርቡ በአዲስ መልክ ከተቋቋመው የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማሕበር ጋር በመሆን አካሂዷል:: በንግድ ትርኢቱ ላይ የታደሙ የአባል ሀገራቱ ተወካዮች በፈጠራ የሰሯቸውን ምርቶች፣ አበርክቶዎችና አገልግሎቶች ጭምር በማቅረብ የሚያስተዋውቁበት የንግድ ትርኢት ላይ ከ100 በላይ ከውጭ ሀገር የመጡ፤ 100 የሚጠጉ ደግሞ ከሀገር አቀፍ ደረጃ የተውጣጡ ነጋዴ ሴቶች ተሳትፈዋል:: ጎን ለጎንም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የቢዝነስ ኮንፍረንሶች ተካሂደዋል:: የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ሃሳቦች፣ ተሞክሮዎች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ለማምጣት በሚያስችል ልክ ከተለያዩ አባል ሀገራት ጋር የልምድ ልውውጥ ተደርጓል::

አዲስ ዘመን፡- ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሴቶች ምን ያህል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው?

ወ/ሮ ያስሚን:- ሴቶች እንደሚታወቀው በቢዝነሱ ሰፊ ድርሻ አላቸው:: ነገር ግን በትላልቅ ቢዝነሶች በማደግ ከተጠቃሚነት አኳያ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥሟቸዋል:: አንዳንዶቹ ብዙ የሞከሯቸው የፈጠራ ሥራዎች ይኖሯቸዋል:: ነገር ግን በመደበኛ ንግድ አሳድጎ ለውጤት የመብቃትና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ ችግሮች አሉ::

የእውቀት ማነስ፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የገበያ ችግር አለባቸው:: የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በኩልም ብዙ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል:: ችግሮቹን በሚፈታ መልኩ ኮሜሳ ሊደግፍ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ እንደ ኢትዮጵያ በቆዳ ዘርፍ በርካታ ልምድና ተሞክሮ የሚቀመርበት መስመር ለማመቻቸት እንዲሁም በሌላ ዘርፍም ለኢትዮጵያ የሚሆን የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት እርስ በርስ ለመማማር ተችሏል::

ከኮሜሳ ተቋም መሰረቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ያደረገው አንዱ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዮት ነው:: ኢንስቲትዩት ከሚሠራው ሥራ አኳያ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ሴት ነጋዴዎችን ወደሌላ አፍሪካ ሀገራት በመውሰድ ልምዳቸውን ለማካፈል ያመቻቻል:: በኢትዮጵያ በሴት አምራቾች በዓለም አቀፍ ገበያ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉ የቆዳ ምርቶች መመረት ጀምረዋል:: መርሃ ግብሮቹ በአፍሪካ፣ በኮሜሳ ገበያዎች እንዲገቡ የሚያግዝ እድል ይፈጥራል:: ከአፍሪካ ባሻገር በአሜሪካም በአውሮፓም ገበያ የጀማመሩ አሉ:: ትግበራው ሰፍቶ ለሀገር ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ የሴቶች ሚና እንዲጎላ፣ የገበያ መዳረሻ እንዲስፋፋ፣ የእርስ በርስ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ያስቻለም ነው::

ንግድ እየዘመነ መጥቷል:: መንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግብይት (ኢ-ኮሜርስ) አይነት የዲጂታል መርሃ ግብር ውስጥ በርካታ ተቋማትን አካትቶ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስተባባሪነት እየተሠራ ይገኛል::

ሴት ነጋዴዎችም አምርተው ሰፊ የመሸጫ ቦታ ሳይጠይቃቸው በኤሌትሮኒክስ ግብይት ማካሄድ እንዲችሉ ውይይት እየተደረገ ነው:: ሴቶች ኤሌክትሮኒክ ግብይቱ ላይ እንዲገቡ አንዱ የሪፎርሙ እቅድ አካል ሆኖም እየተሠራ ነው:: በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምቹ ሁኔታዎችን እያመጣ፣ የሴቶችንም ተጠቃሚነት እያሰፈነ ነው::

አዲስ ዘመን :- በሚከፈቱ አኅጉራዊ ገበያዎች የኢትዮጵያ ነጋዴዎች እንዴት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ? ኢትዮጵያ የሌሎች ሀገራት ምርት ያጥለቀልቃል የሚል ስጋትም ይነሳል እንዴት ይመለከቱታል ?

ወ/ሮ ያስሚን:– ኢትዮጵያ የአፍሪካ አኅጉር ነጻ ንግድ ቀጠናን አልተቀላቀለችም:: የታሪፍ ማሻሻያውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጽድቆታል:: ማሻሻያውን መሰረት በማድረግም የእቃ ንግድን እናስጀምራለን:: በተሻለ አዋጭነት የአፍሪካ ገበያ ላይ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ቅድሚያ አግኝተው ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲሸጡ የሚያደርግ በመሆኑ ሰፊ የሆነ እድልን ይፈጥራል:: በዋጋም ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል::

ታሪፍ ዜሮ የሆነባቸው በጣም በርካታ ምርቶች ናቸው:: ዜሮ የሆነ ነገር ላይ ሌላ ሀገር በመሄድ የተሻለ ተወዳዳሪ በመሆን ገበያው እየሰፋ እንዲሄድ ያስችላል:: ይህ ታሳቢ ተደርጎም በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናው ላይ የአፍሪካ ሴት ነጋዴዎች ፌዴሬሽን የተዘጋጀው መድረክም ትኩረትም በቱሪዝም፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በማእድን ላይ ያተኮረ ነበር::

የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናውን የአፍሪካ ሴቶች እንዴት መጠቀም አለባቸው ከሚለው ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል:: በመተግበርም በኩል የበርካታ ተቋማትን ቅንጅት ይፈልጋል:: እነዚህ ተቋማትን በአንድ ላይ የያዘ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚመራው የብሄራዊ አስተግባሪ ኮሚቴም ተቋቁሟል:: ኮሚቴው በርካታ ተቋማት በስሩ ይዟል:: ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ግብርና ባለስልጣን፣ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽ ባለስልጣን እንዲሁም የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ተካትቷል::

በማንኛውም ጊዜ ነገሮች ሲነሱ ኃላፊነት የያዘ ተቋም መመለስ ስላለበት በዚህ ደረጃ ለማስተግበር ዝግጅት ተደርጓል:: ገበያው በመከፈቱ ብቻ ሀገራችን ትጠቀማለች ማለት አይደለም:: የሚሸጥ እቃ መኖር አለበት:: ለዚህም የግሉ ዘርፍ ባለሃብቱ እድሉን ተገንዝቦ ሊሠራበት ይገባል:: የሌላ ሀገር ሸቀጥ ያጥለቀልቀናል የሚሉ ስጋቶች ይነሳሉ:: ነገር ግን ኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት ላይ ሰፊ ሥራ እየሠራች ነው:: በግብርና ምርትና ምርታማነት እመርታዊ ለውጥ አለ:: በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም በቅርቡ በተካሄደው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ብዙ ነገሮች እየተሠሩ መሆኑን አሳይቷል:: በዚህ ምልከታ የውጭ ሀገራትም ተመሳሳይ ስጋት አላቸው የራሳቸውን ጥናትም አጥንተው ‹‹የእኛ ገበያ በኢትዮጵያ ምርት ይጥለቀለቃል›› የሚል ስጋትም በእነርሱ በኩል ይነሳል:: ይሄንን ውጤታማ እንዲሆን የግሉ ዘርፍ ሚና ሊኖረው ይገባል::

አስፈላጊው ምርት፣ ለተፈላጊው የገበያ መዳረሻ በተፈላጊው ጥራት እና በተፈለገው ደረጃ በዋጋም ተመጣጣኝ ሆኖ ለመድረስ እንዲቻል ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል:: በዚህ ተግባር ከግሉ ባለሃብት ላኪዎች ጋር ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው:: ሌሎች ያልደረስንባቸው ገበያዎች ላይ ለመግባት ግንዛቤ ፈጥሮ የሚፈጠረውን የገበያ አማራጭ ራሳቸው እንዲጠቀሙና ሀገርንም እንዲጠቅሙ፣ ኢትዮጵያም በኢኮኖሚ እንድትበለጽግ ያስችላል::

በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና፣ የምስራቃዊና ደቡባዊ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል በመሆን፤ ከዛም ከፍ ሲል የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየተደረገ ያለው ርብርብ ውጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል:: በእነዚህ የገበያ መዳረሻዎች ተወዳዳሪ በመሆን ምርቶችን በማቅረብ የገቢ ንግዱን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት የሚፈለገውን ብልጽግና እውን ለማድረግ ትልቅ ሥራ ይጠይቃል:: በዚህ ረገድ ጅምር ሥራዎች አሉ፤ የማክሮ ኢኮኖሚው ሪፎርሙ ጥሩ ውጤት እያሳየ ይገኛል::

አዲስ ዘመን :- በዋና ዋና ዘርፎች በተያዘው በጀት ዓመት የሚኒስቴሩ አፈጻጸም ግምገማ ምን ውጤት ያሳያል ?

ወ/ሮ ያስሚን:- በዋናነት የንግድ ሥርዓቱን ከማሳለጥ እና የወጪና ገቢ ንግዱን ከመቆጣጠር አኳያ፣ የጥራት ቁጥጥር ላይ ሚኒስቴሩ መሰረት አድርጎ የሚሠራቸው ሰፊ ሥራዎች አሉ:: በየሩብ ዓመቱ ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ የዘርፍ ጉባኤ በማድረግ አፈጻጸሙን ከፌዴራል፣ ክልል እና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የሚገመገምበት ሥርዓት አለ::

የዘጠኝ ወራትን አፈጻጸም ተመልክተናል:: አጠቃላይ አፈጻጸሙ በጥሩ ደረጃ ተገምግሟል:: በተለይ ከወጪ ንግድ አኳያ ከፍተኛ አፈጻጸም የተገኘበት ነው:: የተሟላ የሪፎርም ማሻሻያው ያስገኘው ውጤት መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጥ ችለናል:: በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ ለማስገባት የታቀደው አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ይገኛል በሚል ነበር:: በዘጠኝ ወራት ብቻ የዓመቱን አፈጻጸም ማለፍ ተችሏል:: በዘጠኝ ወራት ለማስገባት ታቅዶ የነበረው ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ነበር:: አሁን አምስት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር አፈጻጸም የተመዘገበበት ነው::

ይህ በሙሉ ዓመት አፈጻጸምም ታይቶ የማይታወቅ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤትም ጭምር ነው:: ሆኖም ግን ይህ አፈጻጸም እንደ ኢትዮጵያ ለማደግ ካለን ፍላጎት አንጻር ገና ስለሆነ እዛ ላይ ለመድረስ በተገኘው ውጤት መርካት ብቻ አይገባም:: ከእቅዱ 150 በመቶ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ የ108 በመቶ አፈጻጸም ያለው የላቀ አፈጻጸም ተመዝግቧል:: ይህም እቅዱን እንድንከልስ አድርጎናል:: በዘጠኝ ወራት ከእቅድ በላይ ተመዝግቧል፤ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ላቅ ያለ አፈጻጸም ይጠበቃል::

ለአፈጻጸሙ ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ያስቻሉት በማእድን፣ በቡና፣ በጥራጥሬ፣ በአበባ፣ በቁም እንስሳት እና በቅባት እህሎች ናቸው:: ከእነዚህ መካከል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚከታተላቸው ደግሞ የተወሰኑትን ምርቶች ነው:: ጥራጥሬ፣ ቅባት እህል፣ ቁም እንስሳት፣ ጫት፣ እጣንና ሙጫ፣ ብርዕና አገዳ ሰብሎችን ጨምሮ የወጪ ንግዱን ክትትል እናደርጋለን:: እነዚህ ወደ 667 ሚሊዮን ዶላር የተገኘባቸው ምርቶች ናቸው:: በዚህ ውስጥ የቅባት እህል ትልቁን ድርሻ ይይዛል:: 258 ሚሊዮን ዶላር የተገኘው ከቅባት እህል ነው:: በተመሳሳይ በጥራጥሬ ደግሞ 228 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል:: ከጫት ምርት ወደ 90 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቁም እንስሳት የተገኘው ደግሞ 41 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል:: በቀሪ ጊዜ በሚደረገው ክትትል እና ድጋፍ አፈጻጸሙ ከፍ እንዲል ይደረጋል::

አዲስ ዘመን:- ሚኒስቴሩ የገበያ አድማስን ከማስፋት አኳያ ምን እየሠራ ነው ?

ወ/ሮ ያስሚን:- ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ አባል ለመሆን እያደረገች ያለው ጥረት አሁን መልኩን ቀይሮ በሚታይ ደረጃ ውጤት እያመጣ ይገኛል:: በአባል ሀገራትም ጭምር ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አባል ለመሆን ዝግጁ መሆኗን ምስክርነት እየተሰጠ ነው:: ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲከናወን የነበረው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን የንግድ ሥርዓት በመቀየሩ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተደረገው ሪፎርም ጭምር አጋዥ ሁኔታን ፈጥሯል::

በዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በሀገራት በሁለትዮሽ ደረጃ የሚደረጉ ድርድሮችም ላይ ሰፊ የሰነድ ዝግጅቶች አሉ:: ኢትዮጵያ የምትፈጽማቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ዋና ተደራዳሪ የሆኑበትና በርካታ ኃላፊዎች የተካተቱበት፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተመራ ቀጥሏል::

እ.አ.አ በ2026 መጋቢት ወር በካሜሮን ዋና ከተማ ያውንዴ የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል:: በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያ አባልነቷ እንዲረጋገጥ አስፈላጊውን ድርድርና የሰነድ ዝግጅት በማድረግ በድርድሩም የበላይነትን በመያዝ የሚጠናቀቅበት ሂደት ላይ እንገኛለን::

በአፍሪካ አኅጉር ነጻ ንግድ ቀጣናም ኢትዮጵያ መሥራች ሀገር መሆኗ ይታወቃል:: የአፍሪካን ትልቁን ገበያ ደግሞ ተጠቃሚ ለመሆን ለኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ ሆኖ እንዲሰፋ ከሚያደርጉት መካከል አባልነታችንን ወደትግበራ የሚያሸጋግረው የእቃ ንግድም፣ በአገልግሎት ዘርፍም ያለው ነው:: የእቃ ንግድን ለማስጀመር ያቀረብነው የታሪፍ እፎይታ ተቀባይነት አግኝቷል:: በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲጸድቅና ሲታተም ትግበራው ይጀመራል:: በመሆኑም በአፍሪካ ገበያ ላይ የሀገራችን ምርቶች በተሻለ ታሪፍ ዜሮ ሆኖላቸው፤ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ደግሞ ዝቅተኛ ታሪፍ እየተጣለባቸው ተወዳዳሪ ሆነው ይገባሉ:: ለዚህ ዝግጅት ተደርጓል:: ነጋዴው ማሕበረሰቡም ይህ እድል መከፈቱን አውቆ እንዲዘጋጅ እየተሠራ ይገኛል:: ሂደቱንም የሚመራ የብሄራዊ አስተግባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል::

የአፍሪካ አኅጉር ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራው በተሟላ ሁኔታ ሲጀመር በአፍሪካ አኅጉር ውሰጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የንግድ ልውውጥን በተሻለ ደረጃ እያሳደገ ሀገራቱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ይፈጥራል:: ሌሎች አኅጉራት ላይ ያለው እርስ በርሳቸው የንግድ ልውውጥ በተሻለ አፈጻጸም ላይ የደረሰ ነው::

ለዚህ ኢትዮጵያ ቁልፍ ቦታ ላይ ናት፣ በትራንስፖርት በኩልም የተሻለ ፍሰት አለ:: የባቡር መሰረተ ልማትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎትም ይህንን በማስተሳሰር የኢትዮጵያን ምርቶች በማድረስ እና ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡትን ከማሳለጥ አኳያ ሚናቸውን እንደሚወጡ እንተማመናለን::

አዲስ ዘመን:- የአውሮፓ ሕብረት እአአ ከ2026 ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ያወጣው የአውሮፓ ሕብረት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ ምርት ደንብ ላይ ምን ዝግጅት እየተደረገ ነው?

ወ/ሮ ያስሚን:- የአውሮፓ ሕብረት ከደን ጭፍጨፋ/ ምንጠራ ነጻ ምርት የሚል ሕግ አውጥቷል:: ሕጉ የሕብረቱ አባል ሀገራት ካላቸው ፖሊሲ አኳያ ደኖች እንዲጠበቁና እንዳይጨፈጨፉ ማደግን ታሳቢ ያደረገ ነው:: ብዙ የደን ጭፍጨፋ ካለባቸው አካባቢዎች የሚወጡ ምርቶችን አንቀበልም የሚል ክልከላ ያለው ነው:: ሕጉን እንዲከበር እየተሠራ ነው:: በተለይ ቡና ምርት ላይ ትኩረት ተደርጓል:: የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴርና ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመሆን አስፈላጊው ዝግጅት እያደረገ ነው::

በዚህ ሥራ እንደ ሀገር ጥሩ አጋጣሚ የሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ላለፉት ስድስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የአረንጓዴ ልማት የሀገርን የደን ሽፋን እንዲሰፋ ያስቻለ ነው:: በግል ግምገማም ሆነ በተሠሩ ጥናቶች መሰረት እንደ ሀገር ያን ያህል የደን ጭፍጨፋ አለ ብዬ አላምንም:: ይሄ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ሥራም እየተሠራ ነው::

ምርት የሚወጣባቸው አካባቢዎች ላይ ሥራዎች መሠራት አለባቸው:: ለዚህም መረጃዎቹ ተደራጅተው፣ ሲስተም ኖሮ ይሄ ምርት ከዚህ አካባቢ የተገኘ ነው የሚለውን ከማመላከት ባሻገር የደን ሽፋኑ መጨመሩ የሚረጋገጥበት ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል:: ገዥና ተቀባይ ሀገራት የሚያስቀምጧቸውን መስፈርቶች እንደየጊዜው ተመልክቶ ራስን ከሁኔታው ጋር እያላመዱ መቀጠል ያስፈልጋል:: አማራጭ ገበያዎቹንም በዛው ልክ እያሰፉ መቀጠል ይገባል::

አዲስ ዘመን :- የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ተግባሩ ምንድን ነው ? ሥርዓቱ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ እና ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት አንጻር ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል ?

ወ/ሮ ያስሚን:- እንደሀገር የአርሶ አደሩ የግብዓተ አጠቃቀም ሲታይ ውስን ነው:: ቀጥታ ከምርትና ምርታማነት ጋር ይገናኛል:: ይሄ ከአርሶ አደሩ የገንዘብ አቅም ጋር ይያያዛል:: በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ለመጠቀም ደግሞ ማስያዣን ይጠይቃል:: ማስያዣ ደግሞ በዋናነት እንደ መሬት ይዞታ፣ መኪና ከመሳሰሉ ቋሚ ንብረቶች ጋር ይያያዛል::

ለግብዓት የተወሰደ ብድርም ቶሎ መመለስ ስለሚኖርበት አርሶ አደሩ በጫና ውስጥ ሆኖ ለምርቱ ገበያ ሲያፈላልግ አንዳንዴም በማሳ ላይ ጭምር ሲሸጥ ይስተዋላል:: የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ይህንን ችግር ለማስተካከል ለረጅም ጊዜ ሲተገበር የነበረ አዋጅም የወጣለት ነው:: ሆኖም ያን ያህል ተግባርና ውጤት ያልታየበት ነበር::

የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓትን ለማጠናከር እና አሠራሩን በሀገር አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለማስፋፋት ታስቦ በቅርቡ የተጀመረው ፕሮጀክት በተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ይደረግለታል:: ትግበራው ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንባታው ከፍ ያለ፣ አርሶ አደሩ ለግብዓት ለሚያወጣውን ወጪ ተመጣጣኝ ገቢ እንዲያገኝ ያስችላል:: መርሃ ግብሩ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ “ቅንጅት ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት” (አግራ) ፕሮጀክትና የኢንተርናሽናል ፋይናንሽያል ኮርፖሬሽን ድጋፍ ይደረግለታል::

አጠቃላይ እንደ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 372/1996 ወጥቶ እና አዋጁን ተከትሎ የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት ወደ ሥራ ከተገባ ቆይቷል:: ወደተግባር ተገብቶ ብዙ እንቅስቃሴዎች የታዩበት ያለፉት አምስት ዓመታት ነው:: በትግበራውም በዋናነት ለመፍታት የተሞከረው አርሶ አደሩ ለግብርና ምርቱ የሚገዛቸው የተለያዩ ምርቶችን ነው:: ለነዚህ ግብአቶችም የተለያዩ ወጪዎችን ያወጣል:: ምርት በሚደርስበት ሰዓት እነዛን ወጪዎች በተለያየ መልኩ ተበድሮ የሚያገኛቸው ስለሆኑ ቶሎ መክፈልም ይጠበቅበታል::

አርሶ አደሩ ቶሎ ምርቱን ወደገንዘብ ቀይሮ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማግኘት ስላለበት ጫና ውስጥ መውደቁ አይቀርም:: በዚህ ጫና ውስጥ ምርቱን በማሳ ላይ እያለ ጭምር የሚሸጥበት ሁኔታ ይፈጠራል:: ይሄ ደግሞ ወጪውን ሸፍኖ የተወሰነ ትርፍ የሚያገኝበትን ዋጋ ሳይሆን ያላግባብ የሚጥልበት ጭምር ነበር:: ይሄንን የአርሶ አደሩን ችግር ለማስተካከል የተገኘው መንገድ አርሶ አደሩ በመጋዘን ውስጥ ምርቱን ቢያስቀምጥ ያስቀመጠውን በደረሰኝ ወደፋይናንስ ተቋማት በመሄድ ብድር ቢጠይቅበት ነገ የተሻለ ገበያ ሲያገኝ ምርቱን ሸጦ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት ይዘረጋል የሚል ነው:: ከዚያም በላይ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርም ሆነ ሌሎች የሚያስፈልጉትን ግብአቶችን ለማሟላት ያስችለዋል:: ይህ ሲሆን ደግሞ ምርት እና ምርታማነት እያደገ መሄዱ የማይቀር ነው:: የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት መተግበር ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ፣ አርሶ አደሩ በግብርና ላይ ለግብአት የሚያወጣው ተመጣጣኝ እና ገቢ የሚያገኝበት ሆኖ እንዲሠራ ያበረታታል::

የደረሰኝ ሥርዓት ከዚህ በተጨማሪም ከምርት ጋር የሚፈጠርን ብክነት ይቀንሳል:: ከድህረ ምርት በኋላ እንደሀገር 30 በመቶ የሚደርስ ምርት ይባክናል:: ነገር ግን ምርቱ ዘመናዊ በሆኑ መጋዘኖች ባግባቡ ቢቀመጥ ከድህረ ምርት ጋር የተያያዙ ብክነቶችን መቀነስ ይቻላል:: በመሆኑም ተግባራዊ በተደረገው አሠራር ምርቱ ባግባቡ በመጋዘን እንዲቀመጥ በማድረግ በድህረ ምርት ይባክን የነበረው ምርት እንዲቀንስ እና አስፈላጊው ጥራት እንዲጠበቅ ያስችላል:: በዚህ ምክንያትም አርሶ አደሩ ምርቱን ከመዝራት፣ ምርጥ ዘር ከመጠቀም አንስቶ የግብርና ሂደት ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲያካሂድ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል:: ምርቱ የየት አካባቢ እንደሆነ ለማወቅና ለመከታተል የሚያሥችል ሥርዓትንም ይዘረጋል::

ይህ ተግባር መንግሥት በራሱ ብቻ የሚሠራው አይደለም:: ኦፕሬተር ሆነው መጋዘን ኖሯቸው ከአርሶ አደሩም ሆነ ከተለያዩ ማኅበራት ጭምር ምርት እየተቀበሉ በመጋዘን የሚያስቀምጡበት ነው:: በተቀመጠው ምርት ልክ በተቆረጠው ደረሰኝም ከባንክ ብድር የሚያገኙበት ሥርዓት ላይ የሚሳተፉ ማኅበራት፣ የመንግሥት ኢንተርፕራይዞች፣ የግል ዘርፍ አሉ:: በዋናነት የግል ዘርፉ ወደዚህ ተግባር እንዲገባ ይፈለጋል:: ምክንያቱም ሁሉንም መንግሥት አይሠራውም:: መጋዘኑን ኦፕሬት የሚያደርጉ አንቀሳቃሾች ደግሞ ፍቃድ የሚሰጣቸው በንግድና ቀጣናዊ ትስስር የተለያዩ መሥፈርቶችን አሟልተው ነው:: ተግባሩም በምርቱ አስፈላጊው ጥራት እንዲጠበቅ ያደርጋል:: ጥራቱን ያልጠበቀ ምርትም ወደ መጋዘኑ መግባት አይችልም::

በለውጡ ትኩረት ተደርጎ የሚሠራበት የግሉ ዘርፍ ሚና እንዲኖረው ማስቻል ነው:: በአሁኑ ወቅት በመጋዘን ኦፕሬተርነት እየተሳተፉ ያሉት አራት ሲሆኑ፤ አንዱ ማኅበር፣ አንዱ የመንግሥት፣ ሁለቱ ደግሞ የግል ዘርፍ ናቸው:: በቀጣይም ዘመናዊ መጋዘኖችን እንዲገነቡ ይጠበቃል:: በተለይ የግል ዘርፉ ይህንን ግንዛቤ ይዞ በቀጣይም ከዚህ ባለፈ በስፋት በመገንባት ተጠቃሚ እንዲሆን እና የመጋዘን እጥረቱንም እንዲቀንስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል:: ምርት ባለባቸው አካባቢዎች እንዲስፋፋ የግል ዘርፉ በኢኮኖሚው አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ትኩረት ይሰጣል::

የፋይናንስ ተቋማትን በሚመለከት ደግሞ የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ነው:: የባንኩ ትልቁና አንዱ ተልዕኮ የፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ነው:: የፋይናንስ አካታችነትን በማስፈን ሂደት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::

አርሶ አደሩ በባንክ ሥርዓቱ ውስጥ ቋሚ ንብረትን ለብድር እንደማስያዣ እንዲያቀርብ የሚቀርብለት ጥያቄ ተጽእኖ ያሳድራል:: ለብድር ማስያዣ የሚጠየቀውን ለማሟላት ንብረትም ጥሪትም የለውም:: በዚህ ደረጃ አለው ቢባል እንኳ አርሶ አደሩ ያለው ሃብት መሬት ነው:: የመሬት ፖሊሲ ደግሞ ይህንን አይፈቅድም:: በመሆኑም አርሶ አደሩ ምርቱን አስይዞ እንዲበደር ከማድረግ አኳያ አስቻይ ሕጎች እየወጡ ወደ ሥራ እየገቡ ነው:: በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሰረት የዋስትና መብት አዋጅ ቁጥር 1147/2011 በአብነት መጥቀስ ይቻላል::

አዋጁ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ በተንቀሳቃሽ ንብረት ዋስትና መበደር የሚያስችል መመሪያ ወጥቷል። መመሪያው ባንኮች በዓመት ውስጥ ከሚያበድሩት ገንዘብ አምስት በመቶውን ለአርሶ አደሮችና ለአርብቶ አደሮች ጭምር በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር ዓይነት እንዲያውሉ ያስገድዳል። ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ ዘርፉን የፋይናንስ ተቋማት እንዲደግፉት ለማድረግ ብዙ ሥራ ተሠርቷል::

ለእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት እንደ ጅማሬ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ አምስት ባንኮች ይሳተፉበታል:: አማራ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክም በሂደት ላይ ነው:: በቀጣይ እስከ 15 የሚደርሱ ባንኮች እንዲሳተፉ በማድረግ እየሰፋ እንዲሄድ ይደረጋል:: ባንኮች የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሰጣቸው ተልዕኮ አለ::

በመሆኑም በዚህ የእቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓት ላይ የሚሰጡትን ብድር ሰፋ አድርገው በማቀድ የሚጠየቁ አስፈላጊ መስፈርቶችን አርሶ አደሩም ሆነ ማኅበራት፣ አምራቾች፣ አቀነባባሪዎች፣ መሰረታዊ ድርጅቶች በየደረጃው የሚገኙ ሁሉ መስፈርቱን ከማሟላት አኳያ ግንዛቤ እንዲፈጠር፣ እውቀቱን አግኝተው እንዲጠቀሙና እንዲታገዙም ማድረግ ይገባል::

በዚህ ሥርዓት ባለፉት አምስት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተይዞ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል:: ከተሰጠው ብድር አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብሩ ዘንድሮ የተሠጠ ነው:: ተግባሩ በሚቀጥሉት ዓመታት እየሰፋና እያደገ የሚሄድ መሆኑን ያሳያል:: ለዚህም ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው::

አዲስ ዘመን :- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ !

ወ/ሮ ያስሚን:- እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ !

በዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You