
‹‹አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት!›› የሚል ሀገርኛ ብሂል አለ:: ፈዛዛ እና ቸልተኛ የሆነ ሰው ማንም ይደፋፈረዋል ለማለት ነው፤ ምንም አያደርገንም ብለው በመተማመን ወይም ብንወስድበትም አያየንም በማለት የያዘውን ጭብጦ(ስንቅ) ይቀሙታል ለማለት ነው:: ንቁ እና ጠንቃቃን ግን ማንም አይደፋፈረውም::
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ ልክ እንደዚህ ነው:: ኢትዮጵያ አያያዟን አለማሳመሯ ወደብ አልባ አድርጓታል:: ለመሆኑ ኢትዮጵያ ንቁ በነበረችበት ወቅት ምን ነበር? ኢትዮጵያ ከዓለም ልዕለ ኃያላን ሀገራት ጋር ተሟግታ፣ ኤርትራን እንዴት የራሷ እንዳደረገች 80 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን እናስታውስ::
በወቅቱ ኢትዮጵያ እንደነ አክሊሉ ሀብተወልድ አይነት እሳት የላሱ ሀገር ወዳድ ተሟጋች ዜጎች ነበሯት:: 2ኛው የዓለም ጦርነት እንደተጠናቀቀ ‹‹ኤርትራን ምን እናድርጋት?›› ሲሉ አራቱ የጦርነቱ አሸናፊ ልዕለ ኃያላን ሀገራት(እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ሩሲያ) መከሩ:: ይህ ሲሆን ኤርትራ ላይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ፍላጎቶች ነበሩ::
በወቅቱ በነበሩት ብልህ የሀገር መሪ፣ በወቅቱ በነበሩት ቆራጥ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ጥበበኛ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ ኤርትራን በፌዴሬሽን የራሷ አደረገች:: ከአምባሳደር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› መጽሐፍ ላይ ይቺን አጋጣሚ እንጥቀስ::
ዕለተ ቅዳሜ ኅዳር 23 ቀን 1943 ዓ.ም 60 የተባበሩት መንግሥታት አባል ሀገራት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ሊወስኑ ተሰይመዋል:: እጅግ ብዙ ሴራ እና አሻጥር የነበረበትን ክርክር ሲያሸንፉ የቆዩት ጥበበኛው አክሊሉ ሀብተወልድ በተጠንቀቅ እያዳመጡ ነው::
“በዚህች ወሳኝ ቀን አንድ ስህተት ተሠራ:: የኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃድ ለሚቃወሙ ኃይሎች የሚወግን የተዛባ መረጃ ሲነገር አክሊሉ ሀብተወልድ ዕድል ሳይሰጣቸው ጣልቃ ገቡ:: አክሊሉ ሀብተወልድ ትዕግስተኛ ነበሩና ‹‹ዝም በል! የአሠራር ደንብ ጥሰሃል›› ሲባሉ ወደ ልመና እና መለማመጥ ገቡ::
የተዛባውን መረጃ ለማረም ሰነድ አውጥተው ‹‹እግዜር ያሳያችሁ!›› ብለው ለታዳሚው ሁሉ ሲናገሩ የብዙዎች ልብ ከአክሊሉ በኩል ሆነ:: እነሆ በዚያች ቀን ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሃደች:: በሂደት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሃደች:: ኤርትራ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ አንድ ክፍል ሆና ቆየች::
በ1983 ዓ.ም ሥልጣን የያዘው የኢህአዴግ መንግሥት ግን ‹‹ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት›› ሲል ከባዕዳን ሀገራት የከፋ ትርክት ማንበር ጀመረ:: የሕወሓት ታጋይ እና የኢህአዴግ ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ (አቦይ ስብሃት) የኤርትራን መገንጠል ‹‹ሻዕቢያ ‹አልቀበለውም› ቢል እንኳን እኛ እሺ አንልም›› ብለዋል::
ይሄ ማለት ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብለው ያምኑ ነበር ማለት ነው:: በዚህ ሁኔታ ኤርትራ ተገነጠለች:: ይሄ የመጀመሪያው ስህተት ሆነ:: ሁለተኛውና የባሰው ስህተት፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላም ቢሆን ኢትዮጵያ በአሰብ በኩል የባሕር በር ባለቤት መሆን ትችል ነበር::
ምክንያቱም ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ጊዜ እንኳን ሳይቀር አሰብ የኢትዮጵያ ክፍል ነበረች:: በሌላ በኩል የቅኝ ግዛት ውሎች ተሰርዘዋል:: ‹‹አሰብ የማናት?›› ከሚለው የያዕቆብ ኃይለማርያም(ዶ/ር) መጽሐፍ ገጽ 95 ላይ እነዚህን ነጥቦች እናገኛቸዋለን::
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የፈረመቻቸውን ውሎች በመጣሷ ውሉ በራሷ በጣሊያን ተጥሷል:: ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሸናፊዎቹ ሀገራት ከጣሊያን እና ከኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት የሰላም ውል አንቀፅ 23 ላይ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመቻቸው ውሎች ተሰርዘዋል::
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 1952 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ በውሳኔ ቁጥር 390(v) ኤርትራን በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ሲያስተሳስር ቀደም ሲል የነበሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውሎችን ሰርዟል:: እነዚህ ውሎች በኢትዮጵያ በነጋሪት ጋዜጣ ትዕዛዝ ቁጥር 6/1952 ተሰርዘዋል::
በነገራችን ላይ የቅኝ ግዛት ውሎችን እንኳን እንውሰድ ቢባል፤ በ1881 ዓ.ም ኢትዮጵያና ጣሊያን ሲዋዋሉ በአንቀጽ 4 ደብረ ቢዛይን ገዳምን ጨምሮ ምጽዋ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲሆን ተወስኗል::
በቅኝ ግዛት ውሎች እንኳን ሳይቀር ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ነበረች ማለት ነው:: ይሄ ሁሉ በቂ ምክንያት ባለበት ሁኔታ ኢህአዴግ የባሕር በር አልፈልግም ብሎ አሳልፎ ሰጠ:: ‹‹አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት›› ነውና ከዚያ በኋላ የባሕር በር ጉዳይ ተዳፍኖ ቆዬ!
ለመሆኑ የባሕር በርን ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ ምን ጥቅም አለው? የኢትዮጵያን ሕዝብ እና የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም ያሳያል:: በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ አጀንዳ መሆኑ ዓለም በጉዳዩ ዙሪያ ቆም ብሎ ዳግም እንዲያስብ ይረዳል::
የዓለም ልዕለ ኃያላን ሀገራት ያኔ ኤርትራ ከናት ሀገሯ ጋር በኮንፈደሬሽን እንድትዋሃድ ሲፈቅዱ በየዋህነት አይደለም፤ የኢትዮጵያን መንግሥትና ሕዝብ አቋም ስላወቁ ነው:: የዓድዋንም ሆነ የአምስት ዓመቱን የኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትብብር፣ የኢትዮጵያን መንግሥት አቋም… ስላወቁ ነው:: አባቶቻችን እንኳን የባሕር በር ሙሉ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ያዋሃዱት ቆራጥ አቋም በማሳየት ነበር::
የአሁኑ ትውልድ ቢዘገይም የባሕር በር ጥያቄን አንስቷል :: ኢትዮጵያ ያኔም ሆነ አሁን ሀገር ልውረር አላለችም:: በተፈጥሮም፣ በታሪክም፣ በሕግም የራሷ የነበረውን የባሕር በር ማግኘት አለብኝ ነው ያለችው::
ወደ አጀንዳው እንመለስ::
የባሕር በር ጉዳይ የሕዝባችን አጀንዳ ከሆነ ውሎ አድሯል ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃም ክብደት እያገኘ ነው። ይህንን የሕዝባችንን የፍትህ ጥያቄ ለመቀልበስ አሁን ላይ የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ ነው። ሀገርል ከመረበሽ ጀምሮ እስከ ማፍረስ የሚደርሱ ሴራዎች እየተጎነጎኑ ነው ።
ይህም ሆኖ ግን መንግሥትም ሆነ መላው ሕዝብ የባሕር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝበው ፤ ጥያቄውን ከፍ ባለ ድምጽ እያሰሙ ነው። አጀንዳውም የመላው ሕዝባችን ሆኗል ። የባሕር በር ጉዳይ ከሶስት አስርት መፋዘዝ በኋላ ትንሳኤ አግኝቷል።
የዓባይ ጉዳይ የአብዱል ፈታህ አልሲሲ ወይም የመሀመድ ሙርሲ ወይም የሆስኒ ሙባረክ ወይም የአንዋር ሳዳት… ጉዳይ ሳይሆን የግብጽ ሕዝብ ጉዳይ እንደሆነው ሁሉ:: የባሕር በር ጥያቄ ዘላቂ የሕዝብ ጥያቄ ሆኗል ።
ሀገራት በፕሮፖጋንዳ እና ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ነገሮችን የሕዝብ ሲያደርጉ፤ ኢትዮጵያ ግን የራሷ የሆኑትን ነገሮች እንኳን ትነጠቃለች:: የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ዛሬ ላይ ያስተዋሉት እውነታ ይሄ ነው::
የሀገር ፍቅር ማለት በሁኔታዎች ላይ የሚመሰረት(Conditional) ከሆነ የሀገር ፍቅር ሊባል አይችልም፤ ሀገርንም ሊያድን እና ሊያሳድግ አይችልም:: በሁኔታዎች ላይ የሚመሠረት የሀገር ፍቅር የሚኖረው ከሌላ ሀገር ጋር በሚኖር ግንኙነት ነው:: ለራስ ሀገር ሲሆን ግን በሁኔታዎች ላይ የማይመሰረት(unconditional) የሀገር ፍቅር መሆን አለበት::
በሁኔታዎች ላይ የማይመሠረት ማለት ከ80 ዓመታት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አቋም ማለት ነው:: እነ አክሊሉ ሀብተወልድ ምንም እንኳን የሥርዓቱ አገልጋዮች ቢሆኑም በአጼ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ላይ ግን ተቃውሞ ነበራቸው:: ይሠሩ የነበረው ግን ለዘላቂ ሀገር እንጂ ለወቅቱ መንግሥት በሚል አልነበረም::
ለባላባት እየገበረ፣ ከሦስት እጅ አንድ እጅ ብቻ እያገኘ ይኖር የነበረው ገባር ማህበረሰብ ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ‹‹ይሄን መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ልገላገለው›› አላለም:: ምክንያቱም ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ እንጂ የአንድ ንጉሥ ወይም መንግሥት ጉዳይ አልነበረም::
ዘለዓለም የምትኖረው፤ ለልጅ ልጆቿ የምትተርፈው ኢትዮጵያ እንጂ ቢበዛ ከ100 ዓመት በላይ የማይኖሩት ተፈሪ መኮንን (አጼ ኃይለሥላሴ) አልነበሩም!
ይህ የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው:: በቀጥታ ከሉዓላዊነት ጋር የሚገናኝ ጉዳይ ነው:: በተለይም እንደ አፍሪካ፣ በተለይም እንደ ምሥራቅ አፍሪካ፣ በተለይም እንደ አፍሪካ ቀንድ ሲሆን ደግሞ የበለጠ የሉዓላዊነት ጉዳይ ይሆናል::
አንዲት አውሮፓዊት ሀገር የባሕር በር ባይኖራት ምናልባትም ብዙ የደህንነት ስጋት ላይኖርባት ይችላል:: አፍሪካ ውስጥ ያለች ሀገር የራሷ የባሕር በር የላትም ማለት ግን የማንም መጫወቻ ትሆናለች ማለት ነው::
የምትገዛውን የጦር መሣሪያም ሆነ ሌሎች የደህንነት ዕቃዎች በሌሎች ሀገራት በኩል አልፎ ይሆናል ማለት ነው:: ይህ እንግዲህ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ትተነው ቢያንስ እንደ ሀገር በሉዓላዊነት እንኳን ለመቀጠል ማለት ነው::
የባሕር በር አጀንዳ የመሆኑ እውነታ የሚጠቅመው በብዙ መንገድ ነው:: በጉዳዩ ላይ የነቃ ትውልድ ለመፍጠር:: ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሆነ የቀጣናው ሀገራት በጉዳዩ ላይ ጊዜ ወስደው እንዲያስቡ ያስችላል:: ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ የነበሯትን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሕጋዊ መብቶች ለማስተዋወቅ ጭምር ይረዳል:: ይህ ደግሞ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ አቅም ይሆናል።
በሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም