
እንደ ሀገር የክረምቱ ወራት በአንድ በኩል የዝናብ ወቅት እንደመሆናቸው አርሶ አደሩ መሬቱን አርሶ በማለስለስ ዘርና መሬትን አዋድዶ የቀጣይ ዘመን ምርቱን ለማሳደግ ደፋ ቀና የሚልባቸው ናቸው:: በሌላ በኩል፣ ዓመቱን ሙሉ በትምህርት ገበታ ላይ ያሳለፉ ታዳጊዎችና ወጣቶች ከትምህርት ቤቶች ርቀው በየቀያቸው የሚያሳልፉባቸው የእረፍት ጊዜ ነው::
ይሁን እንጂ እነዚህ የክረምት ወራት በየፈርጁ የሚገለጹ አንዱ ለአንዱ የመድረስ የበጎነት ተግባራት የሚፈጸሙባቸው ሌላ ገጽም እንዳላቸው አይዘነጋም:: ይሄ ደግሞ ቀደም ሲልም ክረምቱን ጠብቆ መደጋገፍ፣ መረዳዳት፣ አንዱ አንዱን ማገዝ የተለመደ ተግባር ነው::
አርሶ አደሩ የሚጠምደው በሬ የሌለውን ጎረቤቱን፣ እንደ ችግሩ ልኬት በሬውን በማዋስ አልያም በማቀናጀት አለኝታነቱን ይገልጽለታል:: በሌላም በኩል ከአፈር አዋድዶ ለቀጣይ እንዲበዛለት የሚዘራው ዘር ያጠረው የሰፈሩ አርሶ አደርንም ዘር በማበደር አልያም በመስጠት ነገው ብሩህ እንዲሆንለት የአቅሙን ያግዛል::
ይሄን መሰሉ የወገን ደራሽነት ተግባር ታዲያ በአርሶ አደሩ አምሳል ብቻ የሚታይ አይደለም:: በሌሎች መስኮችና የማህበረሰብ መደቦችም ጭምር የሚገለጥ ነው:: በዚህ ረገድ የሚገለጠው ሀገራዊ እሴት ታዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጥነት ባለውና በተደራጀ መልኩ እንዲመራ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል:: አበረታች እና አብነታዊ የሆነ ውጤትም እየተገኘባቸው ይገኛል::
ምክንያቱም፣ ባልተደራጀና በተበጣጠሰ መልኩ ተይዞ የነበረውን ማህበራዊ ሀብት የበጎነት ሥራ፤ በተደራጀና ዘላቂነት ባለው መልኩ መምራት ከተቻለ እንደ ሀገር የሕዝቦችን የመተባበርና የመተጋገዝ አቅም በመደመር ከችግሮች ልቆ መውጣት የተቻለባቸውን አጋጣሚዎች ማየት ተችሏልና ነው::
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ደግሞ ለዚህ አብይ ማሳያ ነው:: ለምሳሌ፣ እንደ መንግሥታዊ መዋቅር ሲታይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ረገድ በአደረጃጀት የታገዘ ሥራን እያከናወነ ይገኛል።፡ በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በአቧሬ አካባቢ የጀመሩትን የበጎነት ሥራ አብነት በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ላቅ ያለ ውጤት አምጥተዋል::
በዚህ መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርዓያነት በመከተል፣ እንደ ከተማ አስተዳደርም፣ እንደ ሀገርም የተሠሩ ሥራዎች፤ ሺዎችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት አድርገዋል፤ አስር ሺዎችን በልቶ ወደ ማደር አሸጋግረዋል፤ ሺዎችን ከትምህርት ገበታ አገናኝተዋል፤ ሺዎችን የሥራ ባለቤት አድርገዋል:: የእነዚህ ድምር ውጤት ደግሞ ወደ ሚሊዮኖች ተሳታፊነትም፣ ተጠቃሚነትም ተሸጋግሯል::
የወጣቶች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ደግሞ በዚህ በኩል የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል:: ምክንያቱም፣ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ላይ የቆዩ ወጣቶች፤ በክረምቱ ወራት ቤት ከመቀመጥና አልባሌ ቦታ ከመዋል ይልቅ፤ ወገኖቻቸውን ማገዝ በሚችሉባቸው የበጎ ፈቃድ የሥራ መስኮች ላይ መሰማራት የተለመደ ተግባራቸው ሆኗል::
በዚህም ችግኞችን ይተክላሉ፤ ደም ይለግሳሉ፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት ያድሳሉ፣ ይሠራሉ፤ በትምህርት፣ በትራፊክ ቁጥጥር እና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ይሳተፋሉ:: በዚህም በየዓመቱ በቢሊዮን ብሮች የሚገመት አገልግሎትን የሚሰጡ ሲሆን፤ ሚሊዮኖችም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑም ይገኛል::
የዘንድሮው የክረምር ወራትም፣ በዚህ መልኩ እንደሚያልፍ የሚታመን ቢሆንም፤ ይሄ እንዲሆን ከወዲሁ ሁሉም አካል አስፈላጊውን የዝግጅት ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል:: ከዚህ አኳያ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስጀምረዋል:: በወቅቱም “የዚህን ዓመት የክረምት በጎ ፍቃድ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስናስጀምር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ለወጣቶች የክረምቱን ጊዜ በዋዛ እንዳያሳልፉት እመክራለሁ። ዛፍ ብንተክል አፈር እንዳይሸረሸር እናደርጋለን። አቅመ ደካሞችን ብናግዝ፣ ቤታቸውን ብንጠግን ሰፈራቸውን ብናጸዳ ትርጉሙ ትልቅ ነው” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል::
ይሄን መሰል የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባር ደግሞ፣ በከተሞች ብቻ የሚወሰን አይደለም:: በገጠሩም ብቻ የሚገለጥ አይሆንም:: ይልቁንም ሁሉም በየፈርጁ የሚከወን፤ ሁሉም በየመልኩ የሚተሳሰር ሊሆን የተገባ ነው:: ይሄ ሲሆን የገጠሩ ከከተማው፤ የከተማውም ከገጠሩ ይተሳሰራል፤ ይደጋገፋል፤ ይደራረሳል:: በዜጎች ሕይወት ላይም አንዳች ረብ ያለውን ተግባር ለመፈጸም ያስችላል። በመሆኑም ወጣቶች ክረምቱን በበጎ ሥራዎች ላይ እንዲያሳልፍ እና ጊዜውን ለሀገሩም፣ ለወገኑም፣ ለራሱም በሚተርፍ ተግባር ላይ እንዲያውል ከወዲሁ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ይገባል::
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም